No summary available.
መስከረም 22 ቀን 2005ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- የጅጅጋ ገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ነ/ፈጅ አጥሉ ሀብታሙ ተጠሪ፡- አቶ ላሻን ከተማ ገብሬ - ተወካይ መሀመድ ሸህ ዑመር ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የጅጅጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የሱማል ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጡት የቅጣት ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ለጅጅጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ያቀረበው ተጠሪ ነው። ተጠሪ የእኔ ንብረት የሆነችውን የሰልዳ ቁጥር 2-0086 የሆነች ፔጆ መኪና በልባ ተሰርቃ ስናፈላልግ ተከሳሽ/አመልካች/ መኪናዋ ኮንትሮባንድ ዕቃ ጭና ይዣታለሁ በማለት በቁጥጥር ስር አድርጎ ይዟታል። መኪናዋ ተሰርቃ የጠፋች መሆኑን ብገልፅለትም ብር 5ዐ,000 /ሀምሣ ሺህ ብር/ ካልከፈልክ በማለት የያዛት ስለሆነ መኪናየን እንዲለቅ ይወሰንልኝ በማለት ክስ አቅርቧል። አመልካች መኪናዋ የተያዘችው ህዳር 29 ቀን 2002 ዓ.ም. ቀረጥና ግብር ያልተከፈለባቸው የልጆች ነጠላ ጫማ አምስት ካርቶን የልብስ ሣመና እና 68 ካርቶን ፍስታል ጭና ከቀብሪቢያ ወደ ጅጅጋ ስታጓጉዝ አየር ማረፊያ አካባቢ ተይዛለች። ከሳሽ በአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 109 መሰረት እድሉ ተሰጥቶታል። ስለዚህ ክሱ ህጋዊ መሰረትና ምክንያት የልለው በመሆኑ ይዘጋልን በማለት ተከራክሯል። የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ ብር 1ዐ,000 /አስር ሺህ ብር/ ከፍሎ መኪናው ይለቀቅለት በማለት ወስኗል። አመልካች ፍርድ ቤቱ ከስልጣኑ ውጭ ቅጣት ወስኗል በማለት ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርቧል። ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የግራቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በስር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሣኔ አፅንቶታል።
አመልካች የካቲት 12 ቀን 2ዐዐ4ዓ.ም በተፃፈ የሰበር ማመልከቻ ጉዳዩ በአስተዳደራዊ ውሣኔ የሚያልቅ በመሆኑ የቀረበው ክርክር ውድቅ መደረጉ መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት።
አመልካች በአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 109 ንዑስ አንቀጽ 2 በተደነገገው መሰረት መመሪያ አውጥቷል። መኪናዋ ስታጓጉዝ የተገኘችው ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ክልከላ የተደረገበት ዕቃ/ፍስታል/ በመሆኑ በመመሪያው መሰረት ተጠሪ መክፈል የሚገባው ብር 10,000 ሣይሆን ብር 50,000 ነው። ስለዚህ የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች በህግ በተሰጠው ፈቅደ ስልጣን መሰረት ያወጣውን መመሪያ ውድቅ በማድረግ የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት አመልክቷል። ተጠሪ መጋቢት 28 ቀን 2ዐዐ9ዓ.ም በተሰጠ መልስ የበታች ፍርድ ቤቶች ውሣኔ የሰጡት በአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀፅ 109 ንዑስ አንቀፅ 1 ለፍርድ ቤቱ ቅጣት ለማክበድና ለመቅለል ስልጣን የሚሰጥ ፈቃጅነት ያለው ድንጋጌ መሆኑን በማገናዘብና ድንጋጌው እስከ ብር 50,000 በሚደርስ መቀጮ ስለሚል ቅጣቱን ዝቅ አድርጎ መወሰንን ስለማይከለክል ነው በማለት ተከራክሯል። አመልካች ሚያዚያ 29 ቀን 2004ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ የአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀፅ 109 ድንጋጌዎችና አግባብነት ያላቸውን መመሪያዎች መሰረት ያደረገ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው ተጠሪ በአመልካች ቁጥጥር ስር የዋለችው ፔጆ መኪና በልባ ተሰርቃ እንደጠፋችበት ክርክርና ማስረጃ አቅርቧል። በልላ በኩል ንብረትነቷ የተጠሪ የሆነችው መኪና የተያዘችው የጉምሩክ ቀርጥና ታክስ ያልተከፈለበትና ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ በህግ ክልከላ የተደረገበትን ዕቃ ስታጓጉዝ መሆኑን አመልካች በማስረጃ ያረጋገጠ መሆኑን በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሣኔ ተገልጿል። የማጓጓዥያው ባለቤት በተፈፀመው ወንጀል ከራሱ ዕውቀት ወይም ፈቃድ ውጭ መሆኑን ማስረዳት ከቻለ የተፈፀመው ወንጀል ክብደት እየታየ ከብር 10,000 /አስር ሺህ ብር/ እስከ ብር 50,000 /ሀምሣ ሺህ ብር/ ተቀጥቶ ማጓጓዥያው እንደሚመለስለት የአዋጅ አንቀጽ 109 ንዑስ አንቀጽ 1 በመርህ ደረጃ ይደነግጋል። ሆኖም የማጓጓዥያው ባለቤት ከአስር ሺህ እስከ ሀምሣ ሺህ ብር ባለው ሬንጅ ውስጥ ላከፍለው ስለሚገባ መቀጮ ዝርዝር አፈፃፀም የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በሚያወጣው መመሪያ የሚወሰን ስለመሆኑ ድንጋጌው በግልፅ ያስቀምጣል።
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በአዋጁ አንቀጽ 1ዐ9 ንዑስ አንቀጽ 2 በተሰጠው ስልጣን መሰረት መመሪያ ቁጥር 5ዐ/2003 በማውጣት ተግባራዊ አድርጓል። በዚህ መመሪያ አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ማጓጓዥያው የተያዘው ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ የተከለከለ ዕቃ ከሆነ የማጓጓዥያው ኃላፊ ብር 50,000 /ሀምሣ ሺህ ብር/ መቀጮ ከፍሎ መጓጓዥያው የሚለቀቅለት መሆኑ በግልፅ ተደንግጓል። የተጠሪ መኪና ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ክልከላ የተደረገበት ስልሣ ስምንት ካርቶን ፍስታል ይዞ የተገኘ መሆኑ ተረጋግጧል። ስለሆነም ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 622 አንቀጽ 1ዐ9 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ባወጣው መመሪያ ቁጥር 50/2003 አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት በብር 50,000/ ሀምሣ ሺህ ብር/ መቀጮ መቀጣት እንዳለበት በግልፅ ተደንግጎ እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች ተጠሪ ብር 10,000 /አስር ሺህ ብር/ ብቻ መቀጮ እንዲከፍል የሰጡት ውሣኔ በአዋጁ አንቀጽ 1ዐ9 ንዑስ አንቀጽ 2 ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተሰጠውን አስገዳጅነት ያለው መመሪያ የማውጣት ስልጣን የሚጋፋና መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
የጅጅጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የሱማል ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሣኔ ተሻሽሐል።
ተጠሪ ብር 50,000 /ሀምሣ ሺህ ብር/ መቀጮ ከፍሎ መኪናውን ይረከብ በማለት ወስነናል።
በዚህ ፍርድ ቤት የወጣውን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
No topics extracted.