No summary available.
መስከረም 21 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ነጋ ዱፍሳ አመልካች፡- ተሾአብ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጠበቃ አወቀ ውቤ ቀረቡ ተጠሪ፡- የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዐ/ሕግ ኃ/መለኮት አበበ ቀረቡ መዝገቡን ምርመረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፍደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ክርክሩ የይርጋ የጊዜ ገደብ አቆጣጠርን የሚመለከት ነው።
የክርክሩ መነሻ አመልካች ከቱርክ አገር ዘጠና ሶስት ጥቅል (በንድል) የአርማታ ብረት ለማስገባት ታክስና ቀረጥ ከፍያለሁ። በመጀመሪያ ዙር ሰላሣ ስድስት ጥቅል ብረት ጥር 28 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም ተረክቤ ወስጃለሁ። በሁለተኛው ዙር አምሳ አራት ጥቅል ብረት የካቲት 2 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም ወስጃለሁ። በሁለት ዙር ይገባል ተብሎ ከሚጠበቀው ዘጠና ሶስት ጥቅል ሶስት ጥቅል ብረት መጥፋቱ ተረጋግጦ ነሐሴ 21 ቀን 2001 ዓ.ም ደብዳቤ ተፅፎ ዋጋው ከኢንሹራንስ ኩባንያው ተከፍሎኛል።ተጠሪ ድክራላሲዮን እንድበተን መስከረም 3ዐ ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም ጠይቋል። ጥቅምት 11 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም ተጠሪ ማስረጃ ሰጥቶናል። ስለዚህ በስህተት የከፈልኩት ብር 273,5ዐ3.92 (ሁለት መቶ ሰባ ሶስት ሺህ አምስት መቶ ሶስት ብር ከዘጠና ሁለት ሣንቲም) እንዲመልስ ውሣኔ ይሰጠልኝ በማለት የቀረበው ክስ ነው። ተጠሪ በተከሣሽነት ቀርቦ የተለያዩ መከራከሪያዎችን ያቀረበ ሲሆን በዋናነት ዕቃው ወደ አገር ውስጥ ከገባና የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ተፈፅሞበት ዕቃውን ከተረከበ ከስድስት ወር በኋላ ከሣሽ ያቀረበው ጥያቄ በይርጋ ቀሪ ይሆናል በማለት ተከራክሯል።የሥር ፍርድ ቤት አመልካች በሁለት ዙር የሚገባውን ጥቅል ብረት ከተረከበ የካቲት 2 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም ጀምሮ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ጥያቄውን ያላቀረበ ስለሆነ በይርጋ ይታገዳል በማለት ውሣኔ ሰጥቷል። አመልካች ይግባኝ ለፍደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል። የከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኙን በፍታብሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 337 መሰረት ሰርዞታል።
አመልካች ሀምል 12 ቀን 2ዐዐ3 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት አለቀ የሚባለው ዲክላራሲዮን ከተበተነበት ጥቅምት 11 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም ነው። ስለዚህ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሲታሰብ የስድስት ወር ጊዜ ያላለፈ በመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች ክሱ በይርጋ ይታገዳል በማለት የሰጡት ወሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ እንዲሻርልኝ በማለት አመልክቷል። ተጠሪ በበኩሉ መስከረም 22 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም በተፃፈ መልስ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ተፈፀመ የሚባለው አመልካች ዕቃዎችን ተረክቦ የወሰደበት ጊዜ ነው። ዕቃዎቹ የተለቀቁት የካቲት 2 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም ነው። ክስ ያቀረበው የይርጋ የጊዜ ገደብ ካለፈ በኋላ ነው። ስለዚህ የበታች ፍርድ ቤቶች ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ ሰጥቷል። አመልካች መስከረም 3ዐ ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
ግራ ቀኙ በፅሑፍ ካቀረቡት ክርክር በተጨማሪ ችሎቱ የግራ ቀኙን የቃል ክርክር ሚያዚያ 22 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም በዋለው ችሎት ሰምቷል። የቃል ክርክሩ ግልባጭ ተያይዟል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና ግራ ቀኙ በፅሑፍ ያቀረቡት ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች የአመልካች ክስ በይርጋ ይታገዳል በማለት የሰጡት ውሣኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው በዕቃዎች አሰያየም፣ በታሪፍ አመዳደብ፣ በዋጋ አተማመን ወይም በልላ የሒሣብ አሰራር ሥህተት ምክንያት በአብላጫ የተከፈለ የቀረጥና የታክስ ተመላሽ ጥያቄ ሲቀርብ ተጣርቶ በብልጫ የተከፈለው ቀረጥና ታክስ ለከፋዩ ተመላሽ እንደሚሆን በአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀፅ 66 ንዑስ አንቀፅ 1 ገዥነት ያለው መርህ ሆኖ ተደንግጓል። ሆኖም በዚህ መሰረታዊ መርህ መሰረት በብልጫ የተከፈለ የቀረጥና ታክስ ተመላሽ ጥያቄ ላታይ የሚችለው ዕቃው የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት አጠናቅቆ ወደ አገር ከገባበት ወይም ወደ ወጭ አገር ከተላከበት ቀን ጀምሮ በስድስት ወራት ውስጥ ከቀረበ ብቻ እንደሆነ የአዋጁ አንቀፅ 66 ንዑስ አንቀፅ 2 ይደነግጋል። በያዝነው ጉዳይ አመልካችና ተጠሪ የሚከራከሩበት የሕግ ጭብጥ ለይርጋ የጊዜ ገደብ ለመቁጠር “ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ተጠናቀቀ” የሚባለው ምን አይነት ተግባራት ተፈፅመው ሲጠናቀቁ ነው” የሚለው ነው። ይህንን ነጥሎ መወሰን “ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ” ለሚለው ቃል አዋጅ ቁጥር 622/2001 የሰጠውን ትርጓሜ ፣ መመልከት ያስፈልጋል። በአዋጅ አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 17 “ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ማለት ወደ አገር የሚገባ ፣ ወይም ወደ ውጭ አገር የሚላክ ወይም ተላለፊ ዕቃ የጉምሩክ ወደብ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ከጉምሩክ ቁጥጥር ሥር እስከሚወጣ ድረስ የሚከናወን ማናቸውም የጉምሩክ አፈፃፀም ሒደት እንደሆነ ትርጓሜ ተሰጥቶታል። የአዋጁ አንቀፅ 66 ንዑስ አንቀፅ 29 እና በአዋጅ ቁጥር አንቀፅ 2/17/ ድንጋጌዎች መሰረታዊ ጉዳይ አድርገው የሚደነግጉት ዕቃዉ የጉምሩክ ሥርዓት አሟልቶ ወደ አገር የገባበት ወይም ከአገር የወጣበትን ጊዜ ነው።
በያዝነው ጉዳይ አመልካች ተመላሽ ታክስና ቀረጥ ከፍየበታለሁ የሚለው ዘጠና ሶስት ጥቅል /በንድል/ የቶንድኖ ብረት ወደ አገር ውስጥ የሚገባው በሁለት ዙር መሆኑና አመልካች በመጀመሪያው ዙር የተጫነውን ሰላሣ ስድስት ጥቅል /በንድል/ የቶንዲኖ ብረት ጥር 28 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የጉምሩክ ሥርዓት በማሟላት ተረክቦ የወሰደና ወደ አገር ውስጥ ያስገባ መሆኑ አከራካሪ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ አመልካች በሁለተኛው ዙር የመጣለትን ሀምሣ አራት ጥቅል ብረት ፣ መሟላት የሚገባውን ፎርማላቲ በማሟላት የካቲት 2 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱ ተረጋግጧል። አመልካች የሚጠብቀው ህጋዊ ሥርዓት አሟልቶ የያዘው በሶስተኛ ዙር የሚገባ ጭነት /ዕቃ /የለም። አመልካች በሁለተኛው ዙር ውጭ አገር እንዲላክለት ካዘዘው ዕቃ ውስጥ ሶስት ጥቅል ብረት የጠፋ መሆኑ ነሐሴ 12 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የተፃፈ የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል።
በአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀፅ 66/2/ እና አንቀፅ 2/17/ መሰረት አመልካች በሁለተኛው ዙር ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ብረት ከጉምሩክ መጋዘን በማውጣት አስፈላጊ የሆኑ ፎርማላቲዎች አሟልቶ ተረክቦ ወደ አገር ውስጥ ካስገባበት የካቲት 2 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም ጀምሮ አመልካች ትርፍ ቀረጥና ታክስ ከፍየበታለሁ በማለት ተመላሽ ገንዘብ የጠየቀበትን ዕቃ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚፈፀመው የጉምሩክ ሥርዓት ተጠናቅቋል። አመልካች ተመላሽ ሒሣብ ካለው ከዚህ ቀን ጀምሮ ባለው ስድስት ወራት ውስጥ መጠየቅ ሲገባው ፣ ይህ የጊዜ ገደብ ካለፈ በኋላ ጥያቄውን እንዳቀረበ ከሥር ፍርድ ቤት ውሣኔ ተረድተናል። አመልካች የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ተጠናቅቋል መባል የሚገባው ዕቃው ወደ አገር ውስጥ ከገባበት ቀን ሣይሆን ድክላራሲዮን ከተበተነበት ቀን ጀምሮ መሆን ይገባዋል በማለት ያቀረበው ክርክር የአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀፅ 66/2/ እና አንቀፅ 2/17/ ድንጋጌ ይዘት ፣ መንፈስና ዓላማ እንዲሁም ህግ አውጭው አዋጁን ሲያውጅ ያሰባቸውን መሰረታዊ ዓላማዎች ያላገናዘበ በመሆኑ አልተቀበልነውም። ስለሆነም የበታች ፍርድ ቤቶች የአመልካች ጥያቄ በይርጋ የጊዜ ገደብ ያለፈበት ነው በማለት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፍደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ ፀንቷል።
በዚህ ክርክር ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ። መዝገቡ ተዘግቷል። ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.