No summary available.
ጥር 17 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ረታ ቶሎሳ አዳነ ንገሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- እነ አቶ ተሾመ ገበየሁ ከጠበቃ አያው ካሣዬ ጋር ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ ላሻንወርቅ ገበየሁ - ጠበቃ ሚደቅሳ ባየሣ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የወራሽነት ድርሻ ጥያቄን የሚመለከት ነው። ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካቾች ባሁኑ ተጠሪዎች በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው።
የአመልካቾች የስር አቤቱታ ይዘትም ወላጅ አባታቸው አቶ ገበየሁ ወልደአብ እና ወላጅ እናታቸው ወ/ሮ ዘረፋ ኃይለኛ ወራሽ መሆናቸው መረጋገጡን ጠቅሰውና የአባታቸውና የእናታቸው የውርስ ንብረት መለየት ያለበት መሆኑን ገልጸው የውርስ ንብረቱ እንዲጣራ የውርስ አጣሪ እንዲሾምላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚሳይ ነው። ተጠሪዎችም በአመልካች ጥያቄ ተቃውሞ የልላቸው መሆኑን ገልጸው ውርሱ እንዲጣራና የውርስ አጣሪ እንዲሾም የፈለጉ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ በማሳወቃቸው ፍርድ ቤቱን አጣሪውን ሹሞ ውርሱ እንዲጣራ ያደረገ ሲሆን አጣሪውም የውርስ ሪፖርቱን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። ፍርድ ቤቱም በቀረበው የውርስ አጣሪ ሪፖርት ላይ ግራ ቀኙ አስተያየት እንዲያቀርቡ አድርጎ የአሁኑ አመልካቾች የውርስ ሪፖርቱ ላይ ተቃውሞ የልላቸው መሆኑን የገለጹ ሲሆን ተጠሪዎች ግን ሟች ገበየሁ ወልደአብ የተዉት ኑዛዜ ቀድሞ በፍርድ ቤት ክርክር ተደርጎበት ፈራሽ ባልተባለበት ሁኔታ በውርስ አጣሪ መነቀፉ ያላግባብ ነው በማለት አስያየታቸውን የሰጡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ የሟች አቶ ገበየሁ ወልደአብ የውርስ ንብረት ለወራሾች መለየት ያለበት በኑዛዜው መሰረት መሆኑን፣የሟች ወ/ሮ ዘረፋ ኃይለኛ የውርስ ንብረት ግን በሕጉ መሰረት ለወራሾች ላከፋፈል እንደሚገባ ገልጾ የውርስ አጣሪውን ሪፖርት አሻሽሎ አፅድቆታል።በዚህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አመልካቾች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበውም ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ፀንቷል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም አመልካቾች ሟች አቶ ገበየሁ ወልደአብ ባደረጉት ኑዛዜ ተቃውሞ ማቅረብ እንደሚችሉ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ተሰጥቶበት እያለ ኑዛዜው አመልካቾችን በመንግስት ባዶ ይዞታ ላይ ብቻ መብት እንዳላቸው በመግለጽ አመልካቾችን ከውርሱ የነቀለ በመሆኑና የጎዳ መሆኑን ጠቅሰን ተከራክረን የበታች ፍርድ ቤቶች ኑዛዜው ላይ ቀድሞ ክርክር ተደርጎ እስከ ፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ የጸና ስለሆነ የሟቹ ንብረት በኑዛዜው መሰረት ክፍፍል ላደረግበት ይገባል በማለት መወሰናቸው ያላግባብ ነው የሚል ነው።አቤቱታቸው ተመርምሮም የስር ፍርድ ቤቶች ኑዛዜው ሕጋዊ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ ሳያስተናግዱ በኑዛዜው ዙሪያ አጣሪው ያቀረበውን ሪፖርት ውድቅ በማድረግ ብቻ ማለፋቸው በአግባቡ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት የቀረበ ሲሆን ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው በጽሑፍ በሰጡት መልስ የኑዛዜው ሕጋዊነት ቀድሞ ያለቀ መሆኑን ዘርዝረው የበታች ፍርድ ቤቶች ክፍፍሉ የሚፈፀምበት አግባብ በኑዛዜ ነው በማለት መወሰናቸው ተገቢነት ያለው ጭብጥ በመያዝና ህጋዊ ምክንያት በመስጠት ነው ሲሉ ውሳኔው እንዲፀናላቸው ጠይቀዋል።
አመልካቾችም የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልሳቸውን ሰጠተዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካቾች ሰኔ 20 ቀን 1998 ዓ/ም ለአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጠሪ ያስጸደቁትንና ሟች አቶ ገበየሁ ወልደአብ በ24/1986 ዓ/ም ያደረጉት ኑዛዜ እንዲሻርላቸው በርካታ ምክንያቶችን በመጥቀስ የመቃወም አቤቱታ አቅርበው ፍርድ ቤቱም ግራ ቁኙን ከአከራከረ በኋላ አመልካቾች ከአቀረቧቸው በርካታ ምክንያቶች ውስጥ ኑዛዜው የተደረገው ክፍፍል ባልተደረገበት የባልና ሚስት ንብረት በመሆኑ አፈጻጻሙን አስቸጋሪ የሚያደርገው ነው በማለት የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 865(2) ድንጋጌን ጠቅሶ ኑዛዜውን ፈራሽ ነው በማለት በመ/ የወሰነ ሲሆን በዚህ ውሳኔ ተጠሪ ባለመስማማት ይግባኛቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን አከራክሮና ጉዳዩን መርምሮ ኑዛዜው በጋራ ሀብት ላይ መደረጉ ኑዛዜውን እንዳይፈጸም የሚያደርገው ምክንያት ወይም ኑዛዜው በዚህ ምክንያት ውድቅ የሚሆንበት ምክንያት የለም በማለት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሽሮ በመ/ መወሰኑን እንዲሁም ይህ ውሳኔ በአመልካቾች አቤቱታ አቅራቢነት በከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ ከመጽናቱም በላይ የፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ አጣሪ ችሎትም በመ/ በሆነው በጉዳዩ ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም በማለት መዝገቡን መዝጋቱን ነው።እንግዲህ አመልካቾች በኑዛዜው ሕጋዊነት ላይ ክርክር ከማቅረብ የሚከለክል ሁኔታ የለም በማለት በሚከራከሩት የተጠሪ የኑዛዜ ወራሽነት በዚህ መልኩ ከተጠናቀቀ በኋላ በውርስ ንብረት ይጣራልኝ ጊዜ መሆኑን መገንዘብ የምንችለው ጉዳይ ነው።አመልካቾች አሁን ለዚህ ችሎት በሰጡት የመልስ መልስ ላይ ግልጽ በማድረግ የተከራከሩት አሁን ያቀረቡት ክርክር የኑዛዜውን ፎርማላቲ በተመለከተ ሳይሆን ከሟች አባታቸው የውርስ ንብረት የተነቀሉና ከ1/4ኛ በታች ላደርሰን አይገባም በማለት ነው በሚል ነው።የአመልካቾች ክርክር ይህ ከሆነ ኑዛዜው አመልካቾችን ከውርስ ሀብቱ ነቅሐል? ወይስ አልነቀለም?፣ለአመልካቾች የተሰጠው ድርሻስ ከውርስ ንብረቱ ላደርስ ይችል ከነበረው ንብረት ውስጥ ከ1/4ኛ በታች ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነው።
No topics extracted.
በመሰረቱ ኑዛዜ የሕጉን ፎርማላቲ የጠበቀ ነው ተብሎ በፍርድ ቤት መፅደቅ ኑዛዜው መብታቸውን ይነካል በማለት ክርክር የሚያቀርቡ ወገኖች ይህንኑ ክርክራቸውን በዳኝነት አካሉ ከማቅረብ የማይከለከሉ ስለመሆኑን ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠበት ጉዳይ ነው።
አመልካቾች ባሁኑ የክርክር ደረጃ የሟች ኑዛዜ ከውርስ ነቅሎናል በማለት የሚቃወሙ ሲሆን ይህ የክርክር ነጥባቸው ግን በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለተጠሪ የተሰጠውን የኑዛዜ ወራሽነት ለማሰረዝ ተቃውሞ ሲያቀርቡ ሟች አባታችን ኑዛዜ አላደረጉም፣ማድረጋቸውንም አልሰማንም፣ ኑዛዜው በሞቱ በአርባኛው ቀንም አልተነበበም፣ ሟቹ አባታችን ኑዛዜ ያደረጉበት ሀብት በሟች እናታችን የጋራ ሀብት ላይ በመሆኑ ተፈጻሚነት የለውም፣ ኑዛዜው የተደረገው የመንግስት ሀብት በሆነው ባዶ ቦታ ላይ በመሆኑ ሕጉን ይቃረናል በማለት ተከራክረው ፍርድ ቤቱ ሟቹ ባዶ ቦታው ላይ ያላቸውን የይዞታ መብት ለአመልካቾች መናዘዛቸው ሕጉን የሚቃረንበት ሕጋዊ ምክንያት የለም በማለት ውድቅ ያደረገባቸው መሆኑና ኑዛዜው ሕጋዊ ነው ተብሎ እስከ ፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር አጣሪ ችሎት ከመወሰኑ ጋር ተዳምሮ ሲታይ ይህ የውሳኔ ክፍል ለአመልካቾች የተሰጠውን ባዶ ቦታ ተገቢነትን የሚያረጋገጥ ነው። አመልካቾች ይህ ባዶ ቦታ ይዞታ መብት ላተላለፍላቸው ይገባል ተብሎ በፍርድ ከተቋጨ ደግሞ ኑዛዜው ከውርስ ንብረት ነቅሎናል በማለት የሚያቀርቡት ክርክር ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5(1) ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ውጪ ነው። በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1123 መሰረት ከ1/4ኛ በታች ላደርሰን አይገባም በማለት የሚያቀርቡት ክርክርም ቀድሞ ይሰጣቸው የተባለው የይዞታ መብት መጠንና የሟቹን ለተጠሪ ይተላለፍ የተባለውን የውርስ ንብረት ግምት በማነፃጸር በግልፅ ያልቀረበ ከመሆኑም በላይ ቀድሞውንም ቢሆንም የክርክር ነጥብ ለማድረግ እየቻሉ ኑዛዜው ሕጋዊ ነው ተብሎ የመጨረሻ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ማንሳታቸው ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 216 እና 217 ድንጋጌዎች ይዘት፣ መንፈስና አላማ ውጪ ነው። ከላይ በተጠቀሰው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መሰረት በፍርድ ቤት በጸደቀ ኑዛዜ ላይ ተቃውሞ ማቅረብ ይቻላል ተብሎ የተወሰነው ማስረጃውን በመቃወም አቤቱታ አቅርቦ ክርክር ተካሂዶ የመቃወም አቤቱታ በዝርዝር ታይቶ ውድቅ የሆነበትን ወገን ሳይሆን በፍርድ ቤት የፀደቀን ማስረጃ መሰረት አድርጎ የሟችን መብቶች ለመውሰድ ተገቢውን እንቅስቃሴ የሚያደርገው ወራሽ ነው። ከዚህ ውጪ ማስረጃው በተሰጠበት መዝገብ ላይ ተቃውሞ አቅርቦ የተቃውሞ ምክንያቶች በዝርዝር ታይተው ውድቅ ከሆኑና ኑዛዜው ተፈፃሚነት አለው ከተባለ በኋላ በንብረት ክፍፍሉ ጊዜም የቀድሞ የተቃውሞ መሰረት የሆኑትን ነጥቦችንና የተቃውሞ አቤቱታ በቀረበበት ወቅትም የክርክሩ አካል ላሆኑ ይገባቸው የነበሩትን ነጥቦች ሁሉ እንደገና አንስቶ እንዲከራከር ማድረግ ክርክሩ መቋጫ እንዳይኖረው የማድረግ ውጤት ያለው በመሆኑ ከፍትሓ ብሕር ስነ ስርዓት ሕግ አይነተኛ ዓላማ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ተቀባይነት ላሰጠው የሚገባው ጉዳይ አይደለም። ስለሆነም ሟች አቶ ገበየሁ ወልደአብ በህጉ አግባብ ስለማድረጋቸው የተረጋገጠው ኑዛዜ ላከበርላቸው ስለሚገባና ለአመልካቾችም በሕጉ በውርስ ለማስተላልፍ ክልከላ ያልተደረገበትን የይዞታ ቦታ እንዲሰጣቸው የተናዘዙ በመሆኑ አመልካቾች የሚያቀርቡት ክርክር የሕግ መሰረት ያለው ሁኖ አልተገኘም።
በአጠቃላይ አመልካቾች የኑዛዜውን ሕጋዊነት በተመለከተ የመቃወም ማመልከቻ በአቀረቡበት ጊዜ ተከራክረውበት ሟችም በኑዛዜው ላይ ለአመልካቾች ባዶ ቦታ መስጠት የሚችሉ መሆኑ ተጠቅሶ ኑዛዜው ተቀባይነት ከአገኘ በኋላ ከሟች ውርስ ተነቅለናል፣ ከ በታች ላደርሰን አይገባም በማለት የሚያቀርቡት ክርክር ጉዳዩ ቀድሞ ያለቀ ነው በሚል ምክንያት የበታች ፍርድ ቤቶች ማለፋቸው ተገቢ ነው ከሚባል በስተቀር መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት የሚቻል ሁኖ አልተገኘም። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወሰነናል።
ው ሣ ኔ
በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ የካቲት 25 ቀን 2003 ዓ.ም. ተሰጥቶ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ጥር 04 ቀን 2004 ዓ.ም. የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል።
የሟች አቶ ገበየሁ ወልደአብ የውርስ ንብረት ሟቹ በ24/12/1986 ዓ.ም. ባደረጉት ኑዛዜ መሰረት ላከፋፈል ይገባል ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ ነው ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።