No summary available.
ጥቅምት 20 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ደረጀ ማዘንጊያ ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ ፍሬ ህይወት ጴጥሮስ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የደቡብ ክልል የሀዋሣ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የመደበኛ ችሎትና የሀዋሣ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የባልና ሚስት የጋራ ንብረት ክፍያን የሚመለከት ነው።
የክርክሩ መነሻ ተጠሪ ከአመልካች ጋር የነበራቸው ጋብቻ በፍች ከፈረሰ በኋላ ያቀረበችው የጋራ ንብረት ክፍያ ጥያቄ ነው። ተጠሪ ስልሳ ሶስት ንብረቶችን ዘርዝራ ለመካፈል ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ በጋብቻ ውስጥ ያገኙትና ቅድመ ክፍያውን በጋራ የከፍሉት በስሜ የደረሰኝ ኮንደሚኒየም ቤት፣ ለመሸጥ ለመለወጥና ለመካፈል የማይቻል በመሆኑ ቀሪውን የቤቱን እዳ ክፍያ የእኔ ንብረት እንዲሆን ይወሰንልኝ በማለት አመልክታለች። አመልካች በበኩሉ የኮንዶሚንየም ቤቱ በጋብቻ ወቅት የተገኘ የጋራ ንብረት ነው። ቤቱ የጋራ ንብረት እዳውም የጋራ እዳ ሆኖ እንዲወሰንና ቤቱ ተከራይቶ ለመንግስት መከፈል ያለበት እዳ እዲከፈል ይወሰንልኝ በማለት ተከራክሯል። የሥር ፍርድ ቤት ተጠሪ ለኮንዶሚኒየም ቤቱ እስካሁን የተከፈለውን ክፍያ ግማሹን ቤቱን ለማስጌጥ የወጣው ወጭና ፓርቲሽን ለመሥራት የወጣው ወጭ ተሰልቶ ግማሹን ተጠሪ ለአመልካች ከፍላ ቤቱን እንድታሰቀር በማለት ውሣኔ ሰጥቷል።
አመልካች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለሀዋሣ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል።
የከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ አጽንቶታል። አመልካች የሰበር አቤቱታ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት አቅርቧል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የአመልካችን አቤቱታ አልተቀበለውም።
አመልካች ህዳር 12 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ አከራካሪው ኮንዶሚኒየም ቤት በጋብቻ ወቅት ያገኘነው የጋራ ንብረት መሆኑ አልተካደም። በሥር ፍርድ ቤትም ተረጋግጧል። ንብረቱ የጋራ ንብረት ከሆነ የቤተሰብ ህጉን በመከተል እንዲካፈል መወሰን ሲገባው ተጠሪ እንድትወስድ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል። ተጠሪ የካቲት 28 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ ለሰበር አቤቱታው በሰጠችው መልስ ኮንዶሚኒየም ቤቱ ለመሸጥ፣ ለመለወጥና ለመካፈል የማይመች ንብረት ነው። ውሳኔውም ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 85 እና ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ መንግስት ከሚሰራው ስራ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት በመሆኑ የበታች ፍ/ቤቶች ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ ሰጥታለች። አመልካች መጋቢት 25 ቀን 2004 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ግራ ቀኙ ያቀረቡት ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም ለቤቱ የወጣውን ወጪ ግማሹን ለአመልካች በመከፈል ተጠሪ የኮዶሚኒየም ቤቱን እንድትወስድ የበታች ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሳኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነውም አከራካሪው የኮንዶሚኒየም ቤት ተጠሪ በስሟ ያገኘችው ከአመልካች ጋር በትዳር ተሳስራ ስትኖር መሆኑን አላከራከረም። በተጠሪ ስም የተገኘው የኮንዶሚኒየም ቤት የቅድመ ክፍያ በጋብቻ ወቅት ካፈሩት የጋራ ንብረት የተከፈለ መሆኑን እና ቤቱን ለማሳመር እና የቤቱን ፓርቲሽን ለመስራት አመልካችና ተጠሪ በጋብቻ ወቅት ያፈሩትን ገንዘብ የተጠቀሙ መሆኑ በሥር ፍርድ ቤት ተረጋግጧል። ይህም ቤቱ የደቡብ ብሕር ብሕረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 75/96 አንቀጽ 72 መሰረት የባልና የሚስት የጋራ ሀብት እንደሆነ ለመገንዘብ ይቻላል።
የኮንዶሚኒየም ቤቱ እና ለቤቱ ላከፈል የሚገባው እዳ የአመልካች እና የተጠሪ የጋራ ንብረት እና የጋራ እዳ ከሆነ የአመልካች እና የተጠሪ ጋብቻ በፍቺ ሲፈርስ ይሄ የጋራ ንብረት እና ዕዳ የሚካፈልበት ስርዓት በምን መልክ እንደሆነ መመልከቱ አስፈላጊ ነው። በሕግ መንግስቱ የተረጋገጠላቸውን ቤተሰብ የመመስረት መብት በመጠቀም ጋብቻ የፈፀሙ ወንዶች እና ሴቶች በጋብቻው አፈፃፀም፣ በጋብቻ ዘመን እና በፍቺ ጊዜ እኩል መብት ያላቸው ስለመሆኑ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 35 ንዑስ አንቀጽ 1 ተደንግጓል። ከዚህ አንፃር ስንመለከተው ተጠሪ በፍቺ ወቅት የጋራ ንብረት ከአመልካች ጋር ስትካፈል ኮንዶሚኒየም ቤቱን የመውሰድ ልዩ መብት እንዳላት በመግለፅ ያቀረበችው ክርክር የህግ መሰረት ያለው ሆኖ አላገኘነውም።
የኮንዶሚኒየም ቤቱ እንደማንኛውም በጋብቻ ወቅት የተፈራ የጋራ ንብረት ባልና ሚስቱ ስለቤቱና ስለቀሪው ዕዳ አከፋፈል የሚስማሙ ከሆነ በስምምነታቸው መሰረት ሁለቱ የማይስማሙና በአይነት ለመካፈል የሚቻል ከሆነ በአይነት ማካፈል ከላይ የተገለፁት በሁለቱ መንገድ ቤቱን ለመካፈል የማይችል ከሆነ ቤቱ በሀራጅ ተሽጦ የቤቱ ቀሪ ዕዳ ለባንክ ተከፍሎ ቀሪውን ገንዘብ የጋራ ባለሀብት ለሆኑት አመልካችና ተጠሪ እኩል እንዲካፈሉ ማድረግ እንደሚገባ ይህ ሰበር ችሎት በተመሣሣይ ጉዳይ በሰበር መዝገብ ሀምል 8 ቀን 2002 ዓ.ም አስገዳጅ ትርጉም ሰጥቶበታል።
የበታች ፍ/ቤቶች ተጠሪ ለኮንዶማኒየም ቤቱ እስካሁን የወጣውን ወጭ ግማሽ ገንዘበ ለአመልካች ከፍላ ቤቱን እንድታስቀር በማለት የሰጡት ውሣኔ የደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 75/96 አንቀጽ 72 አንቀጽ 1ዐ2 እና አንቀጽ 1ዐ3 ድንጋጌዎችን ይዘት መንፈስና ዓላማ ያላገናዘበ ነው። የበታች ፍርድ ቤቶች ውሣኔ ከህገ መንግስቱ አንቀጽ 35 ንዑስ አንቀጽ 1 ባልና ሚስት በፍች ወቅት እኩል መብት ያላቸው መሆኑን በማረጋገጥ የተደነገገውንና ይህ ሰበር ችሎት በተመሣሣይ ጉዳይ በሰበር መዝገበ የሰጠውን አስገዳጅ የህግ ትርጉም ያልተከተለ ሆኖ አግኝተነዋል። በመሆኑም የሀዋሣ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ሣያርሙ ማሳለፋቸውና ማፅናታቸው ከላይ የጠቀስናቸውን የህግ ድንጋጌዎችና ይህ ሰበር ችሎት በተመሣሣይ ጉዳይ (በሰበር መዝገብ ) የሰጠውን አስገዳጅ ትርጉም ያልተከተለና የአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2 ድንጋጌን የሚጥስ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የሀዋሣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት የሀዋሣ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ስለኮንዶማኒየም ቤቱ የሰጡት የውሣኔ ክፍል ብቻ ተሽሯል።
የኮንዶሚኒየም ቤቱ የአመልካችና የተጠሪ የጋራ ንብረት ነው። አመልካችና ተጠሪ የኮንዶማኒየም ቤቱን እና ቀሪው የባንክ ዕዳ አከፋፈል ስርአት ላይ ከተስማሙ በስምምነታቸው መሰረት ይፈፀም። አመልካችና ተጠሪ ካልተስማሙና ቤቱን በአይነት ለማካፈል የሚቻል ከሆነ አመልካችና ተጠሪ ቤቱን በአይነት ይካፈሉ ዕዳውን ይክፈሉ። ቤቱን ከላይ በተገለፁት ሁለት መንገዶች ለማካፈል የማይቻል ከሆነ በሀራጅ ተሽጦ ቀሪው የባንክ ዕዳ ከተከፈለ በኋላ የሚተርፈውን ገንዘበ አመልካችና ተጠሪ እኩል መካፈል ይገባቸዋል በማለት ወስነናል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
No topics extracted.