No summary available.
ህዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ተኽላት ይመስል አመልካች፡- አቶ ወርቁ ወ/ፃድቅ - አልቀረቡም ተጠሪ፡- የአቶ ተስፋዬ ወ/ሥላሴ ወራሾች 1.ወ/ሮ ወድ ምዕራቡሽ 2.ወ/ሪት ትርሲት ወ/ሥላሴ 3.ወ/ሪት እህቴ ተስፋዬ ወ/ሥላሴ አልቀረቡም 4.ወ/ሪት ገነት ተስፋዬ ወ/ሥላሴ 5.አቶ ብሩክ ተስፋዬ ወ/ሥላሴ 6.አቶ ብርሃኑ ተስፋዬ ወ/ሥላሴ 7.አቶ ናስፍ ተስፋዬ ወ/ሥላሴ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ በአሁኑ የሰበር አመልካች ከሳሽነት የተጀመረው በፍ/የመ/ደ/ፍርድ ቤት ሲሆን ተጠሪዎች ደግሞ ተከሳሾች ነበሩ። ከሳሽ ሚያዚያ 28 ቀን 2002 ዓ/ም ባቀረቡት ክስ ከ1ኛ ተከሳሽ ባለቤትና ከተራ ቁጥር 2-7 ያሉ ተከሳሾች አውራሽ ጋር የሽርክና ውል የነበረን ሲሆን በውላችን መሰረትም ከመካከላችን አንደኛው ከሞተ መብቱ ለወራሽ እንደማይተላለፍ የተስማማን ሲሆን ተከሳሾች አቶ ተስፋዬ ወ/ሥላሴ ከሞቱ በኋላ በሽርክና ውል መነሻ የተቋቋመውን ድርጅት ተከራይተው የሚሰሩትን ሰዎች (ተከራዮች) በማስለቀቅ ለራሳቸው ለመያዝ በሚያደርጉት ጥረት መግባባት ያልቻልን ስለሆነ በሽርክና ውሉ መሰረት ጉዳዩ በሽምግልና እንዲታይ እንዲታዘዝ ሆኖ በሽምግልና እንዲታይ የማይስማሙ ከሆነ ደግሞ የሽርክና ውሉ ፈርሶ ድርሻችን ተለይቶ እንዲወሰን ሲሉ ጠይቀዋል።
ተጠሪዎች ለክሱ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና በአማራጭ መልስ ያቀረቡ ሲሆን መቃወሚያውም ከዚህ በፊት ከሳሽ በዚሁ ጉዳይ ላይ ክስ አቅርበው የፍ/የመ/ደ/ፍርድ ቤት በመ/ቁ/ 40977 ክስ የማቅረብ መብት የላቸውም ሲል መዝገቡን የዘጋው ስለሆነ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/5 መሰረት በዚያው ጉዳይ እንደገና ክስ ማቅረብ አይችሉም የሚል ሲሆን በአማራጭ ባቀረቡት መልስ ደግሞ በመካከላችን የሽርክና ውል የለም ብለው ተከራክረዋል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የቀረበውን መቃወሚያ በተመለከተ በመዝገብ ተከራካሪ ወገኖች የተለያዩ ከመሆናቸውም ልላ የተያዘው የፍሬ ነገር ጭብጥ አሁን ክስ ከቀረበበት ጉዳይ የተለየ በመሆኑ ተከሳሾች የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/5ን ጠቅሰው ያቀረቡት መቃወሚያ ተቀባይነት የለውም ካለ በኋላ በፍሬ ጉዳዩ ላይ በሰጠው ፍርድ ከሳሽ የሽርክናው ማህበር ሰነዶች ናቸው በሚል ያቀረቡአቸው ውሎች ብቻ በመሆናቸውና የሽርክና ማህበር ነው የሚሉትም በንግድ ህጉ መሰረት የንግድ ስም የልለው፣ በንግድ መዝገብ ያልተመዘገበ እና የመመስረቻ ጽሁፍ የልለው በመሆኑ በከሳሽና በ1ኛ ተከሳሽ ባለቤትና ከተራ ቁጥር 2-7 ተከሳሾች አውራሽ መካከል የሽርክና ማህበር ውል የለም። የሽርክና ማህበር ባልተቋቋመበት ደግሞ እንዲፈርስ ጥያቄ ላቀርብ ስለማይችል ከሳሽ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 33(2) መሰረት ክስ የማቅረብ መብት የላቸውም ብሐል።
ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የፍ/ከ/ፍርድ ቤትም የይግባኝ ባዩን ይግባኝ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/337 መሰረት በመዝጋት ይግባኝ ባዩን በማሰናበቱ አመልካች በስር ፍርድ ቤቶች ብይን/ትዕዛዝ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል የሰበር አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን የቅሬታ ነጥቡም ሲጠቃለል፡- ከሟች አቶ ተስፋዬ ወ/ሥላሴ ጋር ለመኪና ጋራዥ ሥራ የሚሆን ቦታ የአፈር ኪራይ እየከፈልን በህብረት ለመስራት ህዳር 17 ቀን 1967 ዓ.ም.
የህብረት ስምምነት ውል ፈጽመን እየሰራን እያለ ቦታው ለውኃ ማጠራቀሚያ መንግስት ስለወሰደው በምትኩ በቀድሞ ከፍተኛ 23 በአሁን አጠራር ቂርቆስ ክ/ከ/ቀበል 08/09 ቦታ ተሰጥቶን ቁጥሩ 826 የሆነ ቤት ሰርተን የመጀመሪያውን ውል የካቲት 27 ቀን 1979 በተጻፈ አዲስ ውል በመተካት ስንዋዋል የንግድ ፈቃዱ በሟች ስም እንዲሆንና ተሻራኪዎቹ የጋራዡን ሥራ በአንድ መልክ እንድናስተዳድር፣ ፈቃዱ በስሙ የሆነው ተሻራኪ ቢሞት በህይወት ባለው ተሻራኪ ስም እንዲሆንና በውርስ እንደማይተላለፍ በማድረግ ከ38 ዓመት በላይ የጋራ ባለሀብት በመሆን የቆየን ሆኖ ሳለና ክሱን ለማስረዳት በቂ ሰነዶችን አቅርቤ እያለሁ የስር ፍርድ ቤቶች ያቀረብኩትን ክስ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ 33(2) መሰረት ውድቅ ያደረጉት ተገቢነት የለውም የሚል ነው።
ተጠሪዎች በሰጡት መልስ፡- አመልካች እና ሟች ተስፋዬ ወ/ሥላሴ የጋራ የሆነ ቤትም ሆነ ቦታ ኖሮአቸው አያውቁም፣ አመልካች የሽርክና ማህበር አለ የሚሉት በንግድ ህጉ መሰረት ያልተመዘገበ፣ የመመስረቻ ጽሁፍና የመተዳደሪያ ደንብ የልለው በመሆኑ የስር ፍርድ ቤቶች የአመልካችን ክስ ውድቅ ያደረጉት ተገቢ ነው ብለዋል።
No topics extracted.
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተጠቀሰው ሲሆን እኛም፡- አመልካች ክስ ባቀረቡት ሀብት ላይ ጥቅም ወይም መብት የላቸውም ተብሎ ክሱ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 33(2) መሰረት ውድቅ የተደረገው በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
አመልካች ክስ ሲያቀርቡ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ 223 መሰረት በማስረጃነት የተለያዩ ውሎችንና ልሎች ሰነዶችን ማቅረባቸውን የመ/ደ/ፍርድ ቤት ብይን ያመለክታል። የመጀመሪያው የውል ሰነድ ህዳር 17 ቀን በ1964 ዓ/ም የአሁኑ አመልካች፣ የ1ኛ ተጠሪ ባለቤትና ከተራ ቁጥር 2-7 ያሉ ተጠሪዎች አውራሽ እና መንግሥቱ ጋሼ የተባሉ ሰው ሆነው አቶ ነጋሽ ወሰኔ ከተባሉ ሰው ለመኪና ጋራዥ የሚሆን ቦታ ወስደው በ1960 ዓ/ም ለመኪና ማቆሚያ የሚሆን ቤት መሥራታቸውን በመግለጽ እነ ካሳሁን ቦሰና የተባሉ ልሎች 4 ሰዎች በደባልነት ገብተው የጋቢናና የባላስትራ ሥራ እንዲሰሩ ስምምነት ያደረጉበት ነው። እንዲሁም በውሉ የተካተቱት ሁሉም ሰዎች በ1ኛ ተጠሪ ባለቤትና ከተራ ቁጥር 2-7 ያሉ ተጠሪዎች አውራሽ ስም የንግድ ፈቃድ ወጥቶ የመንግስት ግብርም ሆነ ለባለይዞታው የሚከፈለውን የቦታ ኪራይ እያዋጡ ለመክፈል መስማማታቸውን ሰነዱ ይገልጻል። ከዚህ በኋላም የካቲት 27 ቀን 1979 ዓ/ም የአሁኑ አመልካች፣ የ1ኛ ተጠሪ ባለቤትና ከተራ ቁጥር 2-7 ያሉ ተጠሪዎች አውራሽና ወ/ሮ አሥራት መንግስቴ ሆነው ቀደም ሲል ያደረጉትን ውል በማሻሻል ‹‹ የንግድ የጋራ ሽርክና ውል ›› በሚል ባደረጉት ስምምነት ቀድሞ ጋራዡ የተቋቋመበትን ቦታ ለውኃ ማጠራቀሚያ እንዲሆን በመፈለጉ በምትኩ በከፍተኛ 23 ቀበል 09 ክልል ውስጥ ቦታ ተሰጥቶ የጋራዡን ስራ መቀጠላቸውን በመጥቀስ ማንኛውም ስራ ተሻራኪዎቹ በአንድ መልክ ሆነው ለማስተዳደር፣ የንግድ ፈቃዱ በስሙ የወጣ ሰው በሞት ቢለይ በህይወት ባሉ ተሻራኪዎች እንዲዛወር፣ ከጋራዡ ሥራ የሚገኘውንም ገቢ እያንዳንዱ ተዋዋይ በሥራው ድርሻው ተጠቃሚ እንዲሆን ከመስማማታቸውም በላይ ልሎች መብቶችና ግድታዎችንም አካትተዋል።
ከተጠቀሱት ውሎች በተጨማሪ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የመንግስት አካላት የጻፉአቸው ደብዳቤዎችን አመልካች በማስረጃነት ለስር ፍርድ ቤት ስለማቅረባቸው በክርክራቸው ገልጸዋል። በዚህ መልኩ የቀረበውን ክስ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ለማድረግ የጠቀሰውም በንግድ ህጉ መሰረት የተቋቋመ ማህበር የለም በሚል ነው። በንግድ ህጋችን ቁጥር 212(1) መሰረት የሚታወቁ የንግድ ማህበሮች 6 ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል አንዱ በዚሁ ቁጥር በንዑስ ቁጥር 1 በፊደል (ለ) ስር የተጠቀሰው የእሽሙር ማህበር ተብሎ የሚጠራው ነው። የእሽሙር ማህበር ህጋዊ ሰውነት የልለው እንዲሁም በጽሁፍ መረጋገጥና በልሎች ንግድ ማህበሮች የተደነገጉት የማስታወቅና የማስመዝገብ ሥርዓቶች እንደማይፈጸሙበት በንግድ ህጉ አንቀጽ 272 ተጠቅሷል። ሸሪኮቹም እንደ ተራ ተዋዋይ ወገኖች የሚታዩ ናቸው። ማህበሩ ህጋዊ ሰውነት የልለው በመሆኑ ምክንያትም የንግድ ሥራ እንቅስቃሴ የሚያደርገውም በሸሪኮቹ ስም ነው። አመልካችና የ1ኛ ተጠሪ ባለቤትና ከተራ ቁጥር 2-7 ያሉ ተጠሪዎች አውራሽ ያደረጉት የሽርክና ውል ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው የእሽሙር ማህበር ባህርያት ጋር የሚመሳሰል ሆኖ እያለ የስር ፍርድ ቤቶች ከእሽሙር ማህበር ውጪ ያሉ ልሎች በንግድ ህጉ የሚታወቁ ማህበራት ላያሟሉ የሚገባቸውን ነጥቦች በመጥቀስ በንግድ ህጉ መሰረት የተቋቋመ ማህበር ባለመኖሩ እንዲፈርስ የሚቀርብ ጥያቄ የለም ሲሉ የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/33(2)ን ጠቅሰው የአመልካችን ክስ በብይን ውድቅ ማድረጋቸው መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በማግኘታችን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍ/የመ/ደ/ፍርድ ቤት በመ/ቁ/53795 በቀን 08/03/2004 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የሰጠውን ብይን እንዲሁም የፍ/ከ/ፍርድ ቤት በመ/ቁ/116705 በቀን 9/05/2004 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት ሽረናል።
በአመልካችና የ1ኛተጠሪ ባለቤትና ከተራ ቁጥር 2-7 ያሉ ተጠሪዎች አውራሽ መካከል የተቋቋመው የእሽሙር ማህበር በመሆኑ አመልካች ባላቸው የሽርክና ስምምነት መሰረት ክስ የማቅረብ መብት አላቸው ብለናል። ስለሆነም ፍ/የመ/ደ/ፍርድ ቤት ወደ ፍሬ ነገሩ በመግባት የግራ ቀኙን ማስረጃዎች በመስማትና በመመዘን አግባብ ባለው ህግ መሰረት የበኩሉን ፍርድ በጉዳዩ ላይ እንዲሰጥበት ክርክሩን በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ 341(1) መሰረት መልሰናል።
የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።