No summary available.
ጥር 27 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- ዩኒስ ቡራል ሲጋል የራይስ ጫት ላኪዎች ማህበር - ጠበቃ ነፃነት ጌታሁን ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ አብዲ አልሚ መሐመድ - ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የሱማል ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ ተጠሪ ከማህበሩ ላቀመንበርነት በማህበሩ ደንብ መሰረት ተነስቷል ወይስ አልተነሳም የሚለውን ጭብጥ የሚመለከት ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በሽንል ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ነው።
በዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት አመልካች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል። አመልካች ማህበሩ አንድ መቶ ሃምሳ አምስት አባላት ያሉትና በ1999 ዓ.ም. የተቋቋመ ነው። ተከሳሽ የማህበሩ ላቀመንበር እንዲሆን በማህበሩ አባላት ተመርጦ ለሶስት ዓመት ማህበሩን በላቀመንበርነት መርቷል። ተከሳሽ የማህበሩን ንብረትና ሰነድ ለግል ጥቅም ያዋለ በመሆኑ ከማህበሩ ላቀመንበርነት እንዲነሳ የማህበሩ አባላት ግንቦት 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ባደረጉት ስብሰባ ወስነዋል። ስለዚህ የማህበሩን ዶክመንትና ንብረት እንዲያስረክብ ውሳኔ ይሰጥልኝ በማለት ክስ አቅርቧል።
ተጠሪ በተከሳሽነት ቀርቦ አንድ የማህበሩ አባል ከአባልነት የሚወገድበት ሥርዓት በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ተደንግጓል። የማህበሩ አባላት በሙሉ ድምፅ የማህበሩ ላቀመንበር ሆኜ እንድሰራ መርጠውኛል። ስለዚህ ከላቀመንበርነት የምወገድበት ምክንያት የለም በማለት ተከራክሯል። የስር ፍ/ቤት የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 11(2) የማህበሩ ላቀመንበር ሥራውን በአግባቡ ለመፈፀም ካልቻለ በማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ላሰናበት እንደሚችል ይደነግጋል። ከሣሽ ከማህበሩ አባላት መካከል አንድመቶ ሃያ የሚሆኑ አባላት ተከሣሽ ከላቀመንበርነቱ እንዲወገድ ውሣኔ የሰጡበት (የወሰኑ) መሆኑን የሚያረጋግጥ የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል። አንዳንዶቹ አባላትም ፍርድ ቤት በመቅረብ ተከሣሽ ከማህበሩ ላቀመንበርነት የተነሣ መሆኑን አረጋግጠዋል። ስለዚህ ተከሣሽ በማህበሩ አባላት ውሣኔና በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ከማህበሩ ላቀመንበርነት የተነሣ በመሆኑ ሰነዶችንና ሥልጣኑን አዲስ ለተመረጠው ላቀመንበር ያስረክብ በማለት ውሣኔ ሰጥቷል።
ተጠሪ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቧል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የማህበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ መካሄዱንና ተጠሪ ከላቀመንበርነት መነሣቱን የሚያሣይ የሰነድ ማስረጃ ቀርቧል። ከማህበሩ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መካከል ሰባት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ፍርድ ቤት በመቅረብ ይህንን አረጋግጠዋል በማለት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል።
ተጠሪ የሰበር አቤቱታ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርቧል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የሽንል ዞን ዐቃቤ ሕግ ለሰበር ችሎቱ ደብዳቤ የፃፈ መሆኑን በመጥቀስ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የሰጡትን ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ሽሮታል።
አመልካች ተጠሪ በማህበሩ አባላት የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣቱ በማህበሩ አባላት ተረጋግጦ ከላቀመንበርነቱ እንዲወገድ የማህበሩ አባላት የማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በማድረግ ወስነዋል። ይህም ፍሬ ጉዳይ የማጣራት ሥልጣን ባለው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና በይግባኝ ሰሚው ችሎት ተረጋግጧል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ጉዳዩን አመልካች በልለበት እንዲታይ ሲያደርግ ህጉን ተከትሎ መወሰን ሲገባው፣ አመልካች ቀርቦ መልስ አለመስጠቱን እንደምክንያት በመግለጽ የስር ፍ/ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡትን ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት በማለት መሻሩ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልክቷል።
ተጠሪ በበኩሉ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡትን ውሣኔ የሻረው፣ አመልካች መጥሪያ ከደረሰው በኋላ ቀርቦ ባለመከራከሩና ገዳዩ በልለበት ታይቶ የተወሰነ በመሆኑ፣ የሸንል ዞን ዐቃቤ ሕግ የፃፈውን ደብዳቤ በማገናዘብና ተጠሪ ከላቀመንበርነት ተወግዷል የተባለው በአንድ የማህበሩ አነሳሽነትና በጥቂት የማህበሩ አባላት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ሰብስበን አዲስ ላቀመንበር ሹመናል በማለት ማህበሩ ሣይጠራ እንደተጠራ አድርገው ባቀረቡት ማስረጃ መሰረት መሆኑን በማረጋገጥ ስለሆነ ተገቢነት የለውም።
አመልካች ታህሣሥ 16 ቀን 2005 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቀርቧል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ተጠሪ የማህበሩ ላቀመንበር ከመሆን የተነሳ በመሆኑ ሰነዶችንና የማህበሩን ንብረቶች እንዲያስረክብ በማለት በሽንል ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡትን ውሣኔ የሻረው በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡትን ውሣኔ የሻረው አመልካች በሰበር ችሎቱ ክርክሩን እንዲያቀርብ መጥሪያ ከደረሰው በኋላ ባለመቅረቡና ጉዳዩ በልለበት የታየ በመሆኑ ነው። አንድ ተከሳሽ /ተጠሪ/ በልለበት ጉዳዩ እንዲታይ ብይን መሰጠቱ ፍርዱ ለከሳሽ ወይም /በሰበር ደረጃ/ ለአመልካች በሚጠቅም መንገድ የመወሰኑን ሁኔታ በአስገዳጅነት የሚያስከትል እንዳልሆነ ከፍትሐብሄር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 70/ሀ/ ድንጋጌዎች ይዘት መንፈስና ዓላማ ለመገንዘብ ይቻላል።
የሽንል ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ አመልካች ያቀረበውን የሰነድ ማስረጃዎችና የማህበሩ ሥራ አስፈፃሚ ኮሜቴ አባላት የምስክርነት ቃል በመስማትና ፍሬ ጉዳይ በማጣራትና ማስረጃ በመመዘን የሰጠውንና የደረሰበትን የፍሬ ጉዳይ መደምደሚያ ፍሬ ጉዳይ በማጣራትና ማስረጃ በመመዘን ሂደት የተፈፀሙ ስህተቶችን የማረም ስልጣን ባለው የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በኩል ተመርምሮ የፀና መሆኑን ከውሣኔው ተረድተናል።
የማህበሩ አባላት ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ በማድረግ በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 11/2/ በሚደነግገው መሰረት ተጠሪ ከማህበሩ ላቀመንበርነት እንዲነሳ የወሰኑ መሆናቸውንና ለማህበሩም ልላ ላቀመንበር የሾሙ መሆኑን ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ባላቸው የሽነል ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተረጋግጧል። የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ መዝኖ ውሣኔ የመስጠት ስልጣን በተሰጣቸው የስር ፍ/ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት ውሣኔ የተረጋገጠው ፍሬ ጉዳይ ሀሰተኛ መሆኑን የሽንል ዞን ዐቃቤ ህግ ደብዳቤ ጽፎልኛል በማለት የስር ፍ/ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡትን ውሣኔ ሽሮታል።
በመሰረቱ ዐቃቤ ሕግ የጻፈው ደብዳቤ የግራቀኙን ክርክርና ማስረጃ በመስማትና በመመርመር በፍርድ ቤት ከተረጋገጠው ፍሬ ጉዳይ በላይ ተአማኒነት እና ክብደት የሚሰጠው አይደለም።
ዐቃቤ ህግ የጻፈው ደብዳቤ አከራካሪው ጭብጥ ላይ ተጨማሪ ማጣራት የሚያስፈልገው መሆኑን የሚጠቁም ነው ከተባለ ጉዳዩ ፍሬ ነገር የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ባላቸው የሸንል ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በኩል እንደገና ተጣርቶ እንዲወስን የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት ጉዳዩን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 343/1/ መሰረት መመለስ ነበረበት። የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት በሽንል ዞን ዐቃቤ ሕግ በኩል የተጻፈውን ደብዳቤ ራሱ በመመዘን ስልጣን ባላቸው ፍ/ቤቶች የተረጋገጠውን ዕውነታ ውድቅ በማድረግ መወሰኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የሱማል ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት ውሣኔ ተሽሯል።
የሽንል ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤትና የሱማል ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት ውሳኔ ፀንቷል።
በዚህ ፍ/ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
No topics extracted.