No summary available.
ጥር 02 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- ጥቁር ዓባይ ኮንስትራክሽን አ/ማህበር ሂሣብ አጣሪ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ባለአደራ ቦርድ ነገረ ፈጆች አዲስ ቦጋለ እና ላዕከማሪያም ላቁ ቀረቡ ተጠሪ፡- ወጋገን ባንክ አ/ማህበር ነገረ ፈጅ ገቢሳ ተሬሳ ቀረቡ መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ አበዳሪ ወጋገን ባንክ ለጥቁር ዓብይ ኮንስትራክሽን ማህበር የሰጠው ብድር ባለመመለሱ ምክንያት ለብድር አመላለሱ ሲባል በመያዥ የያዘውን ንብረት በአዋጅ ቁጥር 97/9ዐ መሰረት በሐራጅ ሲሸጥ ይህንም የሀራጅ ሽያጭ ላፈርስ ይገባል በማለት የአሁን አመልካች ያቀረበው ክርክር በፍርድ ቤት ላወሰን የሚችል መሆን ያለመሆኑን የሚመለከት ነው።
ክርክሩ የጀመረው በፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሲሆን በዚህ ፍ/ቤት የአሁን አመልካች ከሳሽ ተጠሪ ደግሞ ተከሳሽ ነበሩ አመልካች በአሁን ተጠሪ ላይ የመሰረቱት ክስ ባጭሩ፡ የፈረሰውን ጥቁር ዓባይ አ/ማህበር አመልካች በሂሣብ አጣሪነቱ ተረክቦ በማጣራት ላይ እያለ አበዳሪ ወጋገን ባንክ አ/ማህበር በህግ በተሰጠኝ ስልጣን በሐራጅ የመሸጥ መብት አለኝ በማለት የባለዕዳውን ንብረት በሐራጅ እሸጣለሁ በማለቱና ይህም በማጣራቱ ስራ ላይ ችግር ስላስከተለ የተጀመረው በሐራጅ የመሸጥ እንቅስቃሴ እንዲቆም ይደረግልኝ በማለት ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።
የአሁን ተጠሪ በሰጠው የመከላከያ መልስ በጥቁር ዓባይ ኮንስትራክሽን አ/ማህበር እና በተጠሪ ወጋገን ባንክ መካከል በተፈረመው የብድር ውል መሰረት ተበዳሪ የወሰደውን የብድር ገንዘብ በውሉ መሰረት ስላልከፈለ ለብድሩ አከፋፈል በመያዥ የያዘውን ንብረት በአዋጅ ቁጥር 97/90 እና 216/92 በተሰጠን ስልጣን መሰረት በሐራጅ የመሸጥ ስልጣን ስላለው በህግ አግባብ በተቋቋመ የብድር ሰነድ ውል መነሻ ለብድር አመላለስ የተያዘን ንብረት የሐራጅ አሻሻጥን ምክንያት በማድረግ ፍ/ቤቱ ጣልቃ ገብቶ የማየት ስልጣን የለውም። ይህንንም በሚመለከት የፍደራል ሰበር ሰሚው ችሎት በተመሳሳይ ጉዳይ በሰበር መ/ በሆነው ጉዳዩን ፍ/ቤት ተቀብሎ የመወሰን ስልጣን የለውም በሚል ትርጉምም የተሰጠበት ስለሆነ መዝገቡ ላዘጋ ይገባል። በማለት ተከራክሯል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤትም በቅድሚያ ከሳሽ ክስ ያቀረበበትን ጉዳይ ይህ ፍ/ቤት ተቀብሎ ለማየትና ለመወሰን የሚያስችል የዳኝነት ስልጣን አለው ወይስ የለውም የሚለውን ጭብጥ ይዞ ይህንኑ ነጥብ ከህጉ ጋር በማገናዘብ ተመልክቶ የተጠየቀው ዳኝነት በወጋገን ባንክ አ/ማህበር የተጀመረ የሐራጅ የመሸጥ እንቅስቃሴ እንዲቆም ትዕዛዝ እንዲሰጥ ነው። ሆኖም በአዋጅ ቁጥር 90/97 አንቀጽ 3 እና 4 እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 216/92 እንደተሻሻለው ባንኮች ለሰጡት ብድር አከፋፈል በመያዥነት በዋስትና የያዙትን ንብረት የብድር ዕዳው እንዲከፈለው በተወሰነው ጊዜ ሳይከፈል ከቀረ ከ3ዐ ቀናት ያላነሰ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ይህንኑ በመያዣ የተያዘውን ንብረት ያለማንም ጣልቃ ገብነት በሐራጅ የመሸጥና የባለቤትነት መብት ለገዥው የማዛወር ስልጣን ተሰጥቷቸዋል። ባንኩ በእነዚህ ህጐች መሰረት ንብረቱን በሐራጅ በሚሸጥበት ጊዜ በአሻሻጡ ሂደት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 394-449 የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ባለመከተል ያደረሰው ጉዳት ካለ ለደረሰው ጉዳት ኪሣራ ከመጠየቅ በቀር የሐራጅ ሸያጭ በፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዲቆም ክስ የሚቀርብበት መብት እንደልለና ፍ/ቤትም ተቀብሎ የማየት ስልጣን እንደልለው በፍደራል ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መ/ የካቲት 27 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም. በሰጠው ውሣኔ በዚህ አኳኋን ተተርጉሟል። ስለሆነም በባንኩ የተጀመረ የሐራጅ ሽያጭ እንቅስቃሴ እንዲቆም የቀረበውን የዳኝነት ጥያቄ ፍ/ቤቱ የማየትና የመወሰን የዳኝነት ስልጣን ስለልለው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁ 244/2//ሀ/ እና 244/2/ መሰረት መዝገቡ ተዘግቷል
No topics extracted.