No summary available.
ጥቅምት 22 ቀን 2005 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ መኰንን ገ/ሕይወት አመልካች፡- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ - ነ/ፈጅ አቶ አክላሉ ተስፋዬ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ጥጋቡ ተፈራ ጠበቃ አቶ ታዬ ገብረመድህን ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የምዕራብ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የማይንቀሣቀስ ንብረት ለማስያዝ የተደረገውን ውል በድጋሚ ማስመዝገብን የሚመለከት ነው።
የክርክሩ መነሻ ተጠሪ ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበው ክስ ነው። ተጠሪ ከአመልካች ለወሰደው የብድር ገንዘብ መያዣ እንዲሆን የማይንቀሣቀሥ ንብረት የመያዥያ ውል ከአመልካች ጋር በ18-07-1989 ዓ.ም የተዋዋለ መሆኑንና የመያዣ ውሉ በሚመለከተው የአስተዳደር ክፍል መጋቢት 23 ቀን 1989 ዓ.ም እንደተመዘገበ ገልጿል። ተጠሪ የመያዣ ውሉ ምዝገባ እንዲታደሰ ተጠሪ መስከረም 17 ቀን 2003 ዓ.ም የሚመለከተውን የአስተዳደር አካል ጠይቋል። የአስተዳደር አካሉም ያለእኔ ፈቃድ መጋቢት 13 ቀን 2003 ዓ.ም መያዣውን በድጋሚ በመመዝገብ /ለተከሳሽ/ አመልካች አሳውቋል። አመልካች የመያዣ ውል ምዝገባ እንዲታደስለት የጠየቀውና በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/2/ የተደነገገው አስር ዓመት የጊዜ ገደብ ካለፈ በኋላ ነው። ስለዚህ የታደሰው የመያዣ ውል ፈራሽ ነው ተብሎ እንዲወሰንልኝ በማለት ያቀረበው ክስ ነው።
አመልካች በዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሽነት ቀርቦ፣ በአዋጅ ቁጥር 97/90 በተሰጠኝ ሥልጣን መሰረት በመያዣው ላይ ያለኝን መብት ለመጠቀም ለተጠሪ ግንቦት 18 ቀን 1992 ዓ/ም እና መስከረም 24 ቀን 1994 ዓ/ም ማስጠንቀቂያ የሰጠሁ በመሆኑ ተጠሪ /ከሳሽ/ የፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/2/ን በመጥቀስ ያቀረበው ክስ የሕግ መሰረት የለውም በማለት ተከራክሯል። ተጠሪ ማስጠንቀቂያ እንዳልደረሰው በመግለጽ በመከራከሩ፣ የሥር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ማስረጃ ከመረመረ በኋላ አመልካች ግንቦት 18 ቀን 1992 ዓ/ም የተፃፈ ማስጠንቀቂያ በአዋጅ ቁጥር 97/1996 አንቀጽ 3 በሚደነግገው መሰረት ለተጠሪ አድርሷል።
አመልካች መስከረም 24 ቀን 1984 ዓ.ም የተፃፈውን ማስጠንቀቂያ በአዋጅ ቁጥር 97/90 አንቀጽ 3 መሰረት ለተጠሪ ሣይሆን ለልላ ሰው እንዳደረሰ ማስረጃው ያሣያል። ስለዚህ አመልካች በሕግ በተደነገገው መሰረት መስከረም 24 ቀን 1994 ዓ.ም ለተጠሪ ማስጠንቀቂያ አልሰጠም። አመልካች ማስጠንቀቂያ በአግባቡ ካደረሰበት ግንቦት 18 ቀን 1992 ዓ.ም ጀምሮ የመያዣ ውሉ በጊንቢ አስተዳደር ታድሶ እስከተመዘገበት መጋቢት 13 ቀን 2003 ዓ.ም ያለው ጊዜ ሲሰላ ከአስራ ሁለት ዓመት በኋላ የመያዣ ውሉ የታደሰ መሆኑን ያሣያል። ስለሆነም የመያዥያ ውሉ የታደሰው በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/2/ የተደነገገው የአሥር ዓመት የጊዜ ገደብ ካለፈ በኋላ በመሆኑ የመያዣ ውሉ በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 1632/1/ መሰረት ላሰረዝ የሚገባው ነው በማለት ወስኗል።
አመልካች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቧል። ይግባኝ ሰሚው ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ አፅንቶታል። አመልካች መጋቢት 27 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ፣ በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/2/ የተደነገገው የአስር ዓመት የጊዜ ገደብ ከማለፉ በፊት ለተጠሪ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ። ይህም አመልካች በሕጉ የተደነገገው የጊዜ ገደብ ከማለፉ በፊት በአዋጅ ቁጥር 97/90 መሰረት በመብቴ መገልገል መጀመሬን የሚያሣይ ነው። አመልካች በመብቴ መገልገል ከጀመርኩ በኋላ ከመያዣው ላይ ያለኝ መብት ቀሪ የማይሆን ስለመሆኑ ይህ ሰበር ችሎት በተመሣሣይ ጉዳይ በሰበር መዝገብ ጥቅምት 5 ቀን 2002 ዓ.ም አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል። የበታች ፍርድ ቤቶች ይኸ የሰበር ችሎት የሰጠውን የሕግ ትርጉም ሳያገናዝብ በመያዣው ላይ ያለኝ መብት እንዲሰረዝና ቀሪ እንዲሆን የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልክቷል።
ተጠሪ በበኩላቸው ግንቦት 16 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ መልስ አመልካች ግንቦት 18 ቀን 1992 ዓ.ም ማስጠንቀቂያ የሰጠ መሆኑን በመግለፅ የሚያቀርበው ክርክር እውነትነት የለውም። አመልካች ግንቦት 18 ቀን 1992 ዓ.ም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል ቢባል እንኳን፣ መያዣው የታደሰው መጋቢት 13 ቀን 2003 ዓ.ም በመሆኑ ምዝገባው የታደሰው ከአስራ ሁለት ዓመት በኋላ ነው። በሰበር መዝገብ ይህ ሰበር ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠው፣ መያዣውን የሰጠው ሰው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው መሆኑን በማመን የተከራከረ በመሆኑ ነው። ስለዚህ ከዚህ መዝገብ ጋር የሚመሳሰል ባለመሆኑ የአመልካች አቤቱታ ተገቢነት የልለው ነው። ስለዚህ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክሯል። አመልካች ሰኔ 6 ቀን 2004 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ በማቅረብ በስር አቤቱታው ያነሳቸውን ነጥቦች በማጠናከር ተከራክሯል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ግራ ቀኙ ያቀረቡት የፅሑፍ ክርክር ይዘት ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የምዕራብ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመያዣ ውሉ እድሳት ላሰረዝና ቀሪ ላሆን ይገባል በማለት የሰጡት ውሣኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ከዚህ በኋላ አመልካች ለተጠሪ ግንቦት 18 ቀን 1992 ዓ.ም መያዣውን በሰላሣ ቀን ውስጥ ሐራጅ አውጥቶ የሚሸጥ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 97/1990 አንቀጽ 3 መሰረት ማስጠንቀቂያ ለተጠሪ የሰጠ መሆኑን ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል። በልላ በኩል አመልካች ለተጠሪ መስከረም 24 ቀን 1994 ዓ.ም ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ በማለት ያቀረበውን ክርክር ለማስረዳት በሕግ ተቀባይነትና ክብደት ያለው ማስረጃ ያላቀረበ መሆኑን የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አረጋግጠዋል።
አመልካች መጋቢት 23 ቀን 1989 ዓ.ም የተመዘገበው የመያዣ ውል እንዲታደስለት መስከረም 13 ቀን 2003 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የጊንቢ ከተማ አስተዳደር የጠያቀ መሆኑንና የጊንቢ ከተማ አስተዳደር የመያዣ ውሉን ምዝገባ መጋቢት 13 ቀን 2003 ዓ.ም በማደስ የመዘገበ መሆኑን ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው ፍርድ ቤት ተረጋግጧል።
የማይንቀሣቀሥ ንብረት የመያዣ መብት ውጤት የሚኖረው ከተፃፈበት ቀን አንስቶ እስከ አስር ዓመት ድረስ እንደሆነ የፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/1/ ይደነግጋል። እንደዚሁም የመያዣ ውሉ በሕጉ የተመለከተው የአስር ዓመት የጊዜ ገደብ ከማለፉ በፊት የታደሰና በማይንቀሣቀሥ መዝገብ ውስጥ እንደተመዘገበ የተደረገ እንደሆነ ፀንቶ የሚቆይበት ዘመን እንደሚራዘም የፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/2/ የሚደነግግ ሲሆን፣ የመያዣ ውሉ አዲሱ ምዝገባ ከተከናወነበት ቀን ጀምሮ ወደፊት እስከ አስር ዓመት ውጤት የሚኖረው መሆኑን የፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/3/ ደንግጓል።
ከላይ ይዘታቸው በዝርዝር የተገለጹት የፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058 ድንጋጌዎች በጠቅላላውና የፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/1/ በተለየ ሁኔታ፣ በባህሪው የይርጋ የጊዜ ገደብ የሚደነግግ የሕግ ድንጋጌ አለመሆኑን፣ ድንጋጌው የመያዣ ውል ቀሪ የሚሆንበት ወይም በሕግ ውድቅ ስለሚሆንበት /Lapse of mortgage right/ የሚደነግግ እንደሆነ ይህ ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል።
ይህም በመሆኑ ንብረቱን በመያዣነት የያዘው ባለገንዘብ በመያዣው ላይ ያለው መብት ቀሪ የሚሆነው፣ መያዣው ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/1/ የተደነገገው የአስር ዓመት የጊዜ ገደብ ከማለፉ በፊት በመያዣው ላይ ያለውን መብት መገልገል ካልጀመረ እንደሆነ በተጠቀሰው መዝገብ ትርጉም ተሰጥቶበታል።
ይህም በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/1/ በተደነገገው መሰረት ባንኮች በመያዣው ላይ ያለው መብታቸው ቀሪ የሚሆንባቸው በምን ሁኔታ ነው የሚለውን ነጥብ መመልከት የሚጠይቅ ነው። ባለገንዘቡ በማይንቀሣቀስ ንብረት ላይ ያለው የመያዣ መብት በሕጉ የተደነገገው አስር ዓመት በማለፉ ምክንያት ውድቅ ሆኖበታል /ቀሪ ሁኗል/ ወይም /Lapse/ አድርጓል ተብሎ ሲወሰን የመያዣ ውሉ ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ አስር ዓመት ከማለፉ በፊት በመያዣ መብቱ መገልገል ያልጀመረ እንደሆነ ነው። በአዋጅ ቁጥር 97/90 ባንክ ለሰጠው ብድር በመያዣ የያዘውን ንብረት፣ ብድሩ ያልተከፈለው መሆኑን የሰላሣ ቀን ማስጠንቀቂያ በመስጠት ለመሸጥና የንብረቱን ባለሀብትነት ለገዥ ለማስተላለፍ የሚችል መሆኑ በአንቀጽ 3 ተደንግጓል። ስለዚህ ባንክ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በመብቱ መገልገል ጀምሯል ተብሎ ላወሰድ እንደሚገባ ይህ ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ በሰጠው ውሣኔ ግልፅ አድርጎታል።
ይህ የሰበር ችሎት ቁጥሩ ከላይ በተገለፀው መዝገብ ባንክ ማስጠንቀቂያ የሰጠው በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/1/ የተደነገገው አስር ዓመት ሣያልፍ ከሆነ፣ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ ቤቱን ሳይሸጥ አስር ዓመት ያለፈ ቢሆንም እንኳን፣ የቤቱ ሽያጭ ሣይጠናቀቅ አስር ዓመቱ ማለፉ ብቻውን በመያዣው ላይ ያለውን መብት ቀሪ /Lapse/ እንደማያደርገው ትርጉም ሰጥቷል። ከዚህ አንፃር ስንመለከተው አመልካች በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/1/ አስር ዓመት ከማለፉ በፊት ግንቦት 18 ቀን 1992 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 90/97 አንቀጽ 3 መሰረት ማስጠንቀቂያ በመስጠት በመብቱ መገልገል መጀመሩ ተረጋግጧል። ይህ ከሆነ አመልካች በመብቱ በመገልገል ግንቦት 18 ቀን 1992 ዓ.ም ጀምሮ መያዣውን ሳይሸጥ አስራ ሁለት ዓመት ያለፈው ቢሆንም በመያዣው ላይ ያለው መብት ቀሪ እንደማይሆን /Lapse/ እንደማያደርግ ይህ ሰበር ችሎት በመዝገብ ጥቅምት 5 ቀን 2002 ዓ.ም አስገዳጅ ትርጉም የሰጠበት በመሆኑ፣ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/1/ የተደነገገውን የአስር ዓመት ጊዜ እንደ ይርጋ ድንጋጌ በመቁጠር አመልካች ማስጠንቀቂያ ከሰጠበት ግንቦት 18 ቀን 1992 ዓ.ም ጀምሮ አስር ዓመት ያለፈው ስለሆነ አመልካች በመያዣው ላይ ያለው መብት ይሰረዛል በማለት የሰጡት ውሣኔ ከላይ በተገለፀው መዝገብ የተሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ያልተከተለና በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2 የተደነገገውን የሚጥስ ሆኖ አግኝተነዋል።
ስለሆነም አመልካች በመያዣ መብቱ መገልገል በመጀመሩ፣ በመያዣው ያለው መብት ቀሪ /Lapse/ የማይሆን በመሆኑና አመልካች መያዣያውን ለማሳደስ ካስመዘገበበት መጋቢት 13 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አስር ዓመት የሚኖረው መሆኑ በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 3058/3/ የተደነገገ በመሆኑ፣ የአመልካች በመያዣው ላይ ያለው መብት እንዲሰረዝ የምዕራብ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የምዕራብ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ ተሽሯል።
አመልካች በመያዣ መብቱ መገልገል በመጀመሩ፣ በመያዣው ላይ ያለው መብት ቀሪ አይሆንም /Lapse/ አያደርግም በማለት ወስነናል።
አመልካች የመያዥያ ውሉ በጊንቢ ከተማ አስተዳደር
No topics extracted.