No summary available.
የሰ/መ/ ታህሣስ 02 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት - ጠበቃ አቶ ማረን ወንደ ቀረበ ተጠሪ፡- ባርጉባ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን፤ መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ይህ የሰበር ጉዳይ በግራ ቀኙ መካከል ለተነሳው የይርጋ ክርክር ጉዳይ ተፈፃሚነት ካለው ህግ አንፃር በማየት የአሁን አመልካች በተጠሪ ላይ ያቀረበው ክስ በይርጋ ቀሪ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለይቶ ለመወሰን ሲባል የቀረበ ነው።
የአሁን አመልካችና ተጠሪ ባደረጉት የመጓጓዣ ውል መሰረት አመልካች ከጃካርታ ጅቡቲ ወደብ የጫነውን የተጠሪን ንብረት አጓጉዞ እ..አ.ኤ በ02/06/09 ለተጠሪ ማስረከቡንና ተጠሪም እቃውን ከተረከበ ከ5 ወር ከ24 ቀናት በኃላ እ.ኤ.አ በ26/11/09 በተፈረመ የመተማመኛ ሰነድ መክፈል የሚገባውን የመጓጓዣ ዋጋ እ.ኤ.አ. በ10/01/2010 ለመክፈል ግድታ የገባ ስለመሆኑ ግራ ቀኙን ያላከራከረ በክርክር ሂደት የተረጋገጡ የፍሬ ነገር ጉዳዮች ናቸው።
የአሁን አመልካች እቃዎችን ያጓጉዘበት ዋጋ በተጠሪ እንዲከፍለው መጋቢት 12 ቀን 2003 ዓ.ም በተፃፈ የክስ ማመልከቻ ዳኝነት ጠይቋል።
ተጠሪ በበኩሉ የግራ ቀኛችንን ውል በሚገዛው የባህር ህግ አንቀጽ 146 እና 203 ድንጋጌዎች መሰረተ አጓዡ እቃውን ከተረከበበት ቀን አንስቶ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መጠየቅ እንደለበት ተደንግጓል። ከሣሽ የሆነው የአሁን አመልካች ክሱን የመሰረተው ይህ በህጉ የተመለከተው የአንድ ዓመት የይርጋ ጊዜ ካለፈ በኃላ ስለሆነ ክሱ በይርጋ ቀሪ ነው በማለት ተከራክሯል።
የአሁን አመልካችም በዚህ በተጠሪ አመካኝነት ለቀረበበት የይረጋ ክርክር በቃል ክርክር ጊዜ ባቀረበው ክርክር ተከሣሹ በመካከሉ የዱቤ ክፍያ ሰነድ የፈረመ በመሆኑ የክፍያው ግድታ በዓይነቱ ተቀይሯል። ስለሆነም ለጉዳዩ አግባብነት ያለው የፍ/ብሕር ህጉ እንጂ የባህር ህግ አይደለም። ስለሆነም የፍ/ብሕር የይርጋ ዘመኑ 10 ዓመት ስለሆነ በይርጋ ላቋረጥ አይችልም የሚለውን አስመዝግቧል።
ጉዳዩን የተመለከተው የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤትም ጉዳዩን ተመልክቶ በከሣሽ እና በተከሣሽ መካከል የተደረገው የዱቤ አገለግሎት ክፍያና የተደረገው ግራ ቀኙ በመጀመሪያ የባህር ህጉን መሰረት አድርገው የተዋዋሉትን እና በባህር ህግ መሰረት የሚታየውን የመጓጓዣ ውል መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ በመሆኑ ተከሣሽ የአሁን ተጠሪ በዱቤ ውሉ እንደተገለፀው የመጓጓዣ ገንዘቡን እከፍላለሁ ካሉበት ጊዜ ጀምሮ ክሱ እስከቀረበበት ጊዜ ድረስ የአንድ ዓመት ጊዜ ያለፈ በመሆኑ በባህር ህጉ አንቀጽ 203 መሰረት ክሱ በይርጋ ቀሪ ነው በማለት ብይን ሰጥቷል።
ይግባኙን የተመለከተው ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ግራ ቀኙ የመጓጓዣ ዋጋውን የክፍያ ሁኔታ በሚመለከት ያደረጉት የዱቤ አገልግሎት ውል ቀደም ሲል ሁለቱም ወገኖች ያደረጉትና በባህር ህጉ መሰረት የሚገዛውን ውል ያሻሻለ እንጂ የተካ ሆኖ ስላልተገኘ ለጉዳዩ ተፈፃሚነት ያለው የባህር ህግ እንጂ የአሁን አመልካች እንደሚለው በፍ/ብ/ሕግ የሚሸፈን አይደለም። ስለሆነም ክሱ በይርጋ ቀሪ ነው። መባሉ አግባብ ነው በማለት በሥር ፍ/ቤት የተሰጠውን ብይን አጽንቶታል።
የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም ይህንኑ በየደረጃው ባሉት ፍ/ቤቶች የተሰጠውን ዳኝነት ግራ ቀኙ በዚህ ሰበር ደረጃ ካደረጉት የጽሑፍ ክርክር ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው መርምረናል።
እንደመረመርነውም የአሁን አመልካች በገባው ግድታ መሰረት እቃውን ጭኖና አጓጉዞ ለአሁን ተጠሪ ለሥር ከሣሽ እ.ኤ.አ. 20/06/09 ካስረከበ በኃላ እ.ኤ.አ. በ26/11/09 ከአሁን ተጠሪ ጋር ያደረገግነው የዱቤ አገልገሎት ውል በዓይነቱ እና በግቡ ሁለቱም ወገኖች ቀደም ሲል በባህር ህጉ መሰረት ያደረጉትን ውል የተካ ነው ወይስ ያሻሻለ? የሚለውን አከራካሪ ነጥበ በቅድሚያ ተመልክተናል።
የአሁን አመልካች አጥብቆ እንዲሚያነሣው ክርክር የባህር ህጉን መሰረት በማድረግ ሁለቱም ወገኖች የደረጉት ውል በኃላ በዱቤ አግልግሎት ውል ተተክቷል። ስለሆነም ለተነሣው የይርጋ ጊዜ አግባብነት ያለው ይህንኑ የተነሳውን ጉዳይ በሚገዛው በፍ/ብ/ሕግ የተመለከተው የይርጋ ዘመን ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለይቶ ለመወሰን ከአንድ ውል የመነጨ ግድታ በልላ ውል የተተካ ስለሆነ ቀሪ ነው ለማለት ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች አንፃር መመልከቱ አስፈላጊ ነው።
በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1807(ሐ) እንደተደነገገው አመልካች ተጠሪ በመጀመሪያ በባህር ህግ እንዲገዛ አድርገው የተዋዋሉትን ውል በዱቤ አገልግሎት ውል እንዲተካ የመነጨና ማናቸውም መበትና ግድታ እንዲተካ በማድረግ በባህር ህግ መሰረት ከሚታየው ውሉ የመነጨን ማናቸውም መብትና ግድታ እንዲተካ በማድረግ በባህር ህጉ የሚገዛውን ውለታ ሙሉ በሙሉ ቀሪ ስለማድረጋቸውም ሆነ ስላለማድረጋቸው ከፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1826 ጀምሮ በተቀመጡት መለኪያዎች አንፃር ላታይ ይገባል።
ከእነዚህም መከራከሪያዎች አንዱ ይተካል በተባለው እና ተተክቷል በሚባሉት ውሎች መካከል ያለው የውለታ ጉዳይም ሆነ የውለታው ምክንያት በይዘቱ አዲስ መሆኑ እንዳለበትና ይህንኑ በውለታውም አይነት ሆነ ከውለታው ምክንያት አንፃር ታይቶ አዲስ የሆነው ውል ከዚህ ቀደም ተደርጎ በነበረው ውል ላይ የተመለከቱትን ግድታዎች በማያጣራጥር አኳኋን ላያስቀር የሚችል ፈቃድ ከተዋዋይ ወገኖች እንዲኖር አስፈላጊ ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1826 እና 1828 የተደነገገ ከመሆኑም በላይ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1829(ሀ) እንደተመለከተው በመጀመሪያው ውል የተመለከተን እዳ ለማረጋገጥ ሲባል አዲስ ሰነድ የማደራጀት ተግባር የውል መተካት አድራጐት ላሆን እንደማይችል፤ ይህ ተግበር የውል መተካት አድራጎት እንዲሆን ከተፈለገ በውሉ ላይ በግልጽ መመልከት እንደሚገባ ተደንግጓል።
በመሆኑም ሁለቱም ወገኖች የሚጓጓዣ ዋጋ ክፍያን አስመልክቶ በተከታይ የደረጉት ውል በዓይነቱም ሆነ ለውለታው ምክንያት ከሆነው መመዘኛ አንፃር ሲታይ አዲስ ግድታ የተካተተበት ባለመሆኑ፤ ይህንኑ የኃላኛው ውል በዓይነቱም ሆነ በውለታው ምክንያት በመጀመሪያው ውል ከተመለከተው ግድታ የተለዩ አይደለም እንጂ የመተካት ሃሣብ አላቸው ቢባል ይህንኑ የውል መተካት ጉዳይ በዚህ በኋላኛው የ ውል በግልጽና በማየሻማ አኳኃን የተደረገ ሆኖ ባለመገኘቱ እንዲሁም በዱቤ አገልግሎት ውሉ የተደረገው ከተጠሪ በተነፃፃሪነት የሚፈለግበትን የመጓጓዣ ዋጋ በውሉ በተመለከተው ጊዜ የነበረበት የመክፈል ግድታ ለማራዘም ሲባል በእዳ ማረጋገጫ ሰነዱነቱ መደረጉን ይዘቱ አስረጂ ሆኖ በመገኘቱ ሁሉ ምክንያት በግራ ቀኙ መካከል የውሉ መተካት ተግባር የተፈፀመ ሆኖ አልተገኘም።
ይልቁንም የአሁን ተጠሪ በባህር ህጉ መሰረት በሚገዛው ውል ላይ ለመክፈል ግድታ ገብቶ የነበረበትን የክፍያ ጊዜ እ.አ.አ በ26/11/09 በተደረገ የዱቤ አገልግሎት ክፍያ ሰነድ እ.አ.አ.
በ10/01/2010 እከፍላለሁ በማለት የክፍያ ጊዜን የሚያሻሽል ግድታ የገባ በመሆኑ በባህር ህጉ የተመለከተው የአንድ ዓመት የይርጋ ጊዜ በዚህ ከተሻሻለው የክፍያ ጊዜ እ.አ.አ. ከ10/01/2010 ጀምሮ ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ስልት ይርጋው ላታሰብ ይገባል።
በዚህ ረገድም ሲታሰብ ክሱ እስከቀረበበት እስከ መጋቢት 12 ቀን 2003 ዓ.ም ድረስ ያለው ጊዜ ይህ የአንድ ዓመት የይርጋ ጊዜ አልፎታል። አመልካች ይህ የይርጋ ጊዜ ማለፉን ሣይክድ በመከራከሪያነት የሚቀርበው ከተሻሻለው የዱቤ ክፍያ ጊዜ ጀምሬ ሲታሰብ 10 ዓመት ያልሞላው ስለሆነ ክሱ በይርጋ ቀሪ ላሆን አይገባም በማለት በጉዳዩ ላይ ተፈፃሚነት ያለው የፍ/ብ/ብ/ሕገግ ነው ከሚለው የመነሻ ክርክር የመነጨ የክርክር መስመር ነው።
ይህም ከላይ እንደተገለፀው ተቀበይነት ያለው የህግ ክርክር ባለመሆኑ የይርጋ ዘመኑ 1 ዓመት እንጂ 10 ዓመት አይደለም።
በዚህ ሁሉ ምክንያት የሥር ፍ/ቤቶች አመልካች ያቀረበው ክስ በባህር ህጉ አንቀጽ 203 መሰረት የአንድ ዓመት የይርጋ ዘመን ያለፈው ስለሆነ በይርጋ ቀሪ ነው ሲሉ የሰጡት ዳኝነት መሰረታዊ የህግ ስህተት ያተፈፀመበት ሆኖ ስላላገኘነው የሚከተለውን ውሣኔ ሰጥተናል።
ው ሣ ኔ
የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በጉዳዩ ላይ በኮ/መ/ቁ. 117281 በሚያዝያ 10 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው የመጨረሻ ውሣኔ ፀንቷል።
በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ግራ ቀኙ ባደረጉት ክርክር ምክንያት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ።
No topics extracted.