No summary available.
ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- 1.ወ/ሮ ሙሉወርቅ ኃ/ገብርኤል - የቀረበ የለም 2. በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ዲዛይንና አስተዳደር ጽ/ቤት - ነ/ፈጅ ሽመልስ ኃ/ጊዮርጊስ ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሪት ጽጌ መብራቴ - ቀረቡ በሰ/መ/ የቀረበው ጉዳይ በስር ፍርድ ቤት አሁን ከተያዘው ጉዳይ ጋር በተመሳሳይ ተከራካሪ ወገኖች ሲካሄድ የነበረ መሆኑን ስለተገነዘብን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 11 መሰረት አጣምረን በመመርመር ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የመንግስት ቤቶችን ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመፈታት ታስቦ ጥቅምት 17 ቀን 2004 ዓ/ም የወጣውን መመሪያ አፈጻጸም ጋር ተይይዞ የተነሳውን የተከራይነት ጥያቄ የሚመለከት ነው። ክርክሩ የተጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን በዚህ ፍርድ ቤት ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ ሲሆኑ ተከሳሾች የአሁኑ አመልካቾች ነበሩ። የተጠሪ ክስ ይዘትም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ክልል ውስጥ የሚገኝ ቁጥሩ 143 የሆነን የንግድ ቤት ከአሁኗ 1ኛ አመልካች በወር በብር 2500.00 (ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር) ሕዳር 07 ቀን 2003 ዓ.ም. በተደረገው ውል ተከራይተው በመስራት ላይ ባሉበት ሁኔታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዲዛይንና ግንባታ ቢሮ በመንግስት ቤቶች ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ሲል መመሪያ ቁጥር 3/2004 ማውጣቱን፣ይህንን መመሪያ መነሻ በማድረግም ከአሁኗ 1ኛ አመልካች ጋር የነበረውን ውል በማቋረጥ ከአሁኗ ተጠሪ ጋር የኪራይ ውል አድርጎ በተጠሪ ስም የኪራይ ገንዘብ እየተከፈለ መቆየቱንና በኋላ ግን ውሉን አቋርጦ ለቀድሞ ተከራይ ለሆኑት 1ኛ አመልካች ቤቱ እንዲመለስ በማለት መወሰኑን ገልጸው ከ2ኛ አመልካች ጋር ያደረጉት የኪራይ ውል እንዳይቋረጥ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው። የአሁኑ 2ኛ አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም በመመሪያው መሰረት እርምጃ ሲወሰድ የ1ኛ አመልካች ጉዳይ ያላግባብ የተስተናገደ መሆኑን በማጣራትና 1ኛ አመልካችም አዛውንትና የራሳቸው የሆነ ገቢ የልላቸው መሆኑ ተረጋገጦ እና ይህ ደግሞ በመመሪያው መሰረት ውሉን ለማቋረጥ የማያስችል ምክንያት መሆኑ ታውቆ ከተጠሪ ጋር ያደረገውን ውል ማቋረጡን ገልፆ እርምጃው ሕጋዊ ነው ሲል ተከራክሯል። የአሁኗ 1ኛ አመልካችም ተመሳሳይ ይዘት ያለውን ክርክር በማቅረብ የተጠሪ ክስ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል። ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር በመመርመርና 1ኛ አመልካች ገቢ ያላቸው መሆን ያለመሆኑን በማጣራት ጉዳዩን መርምሮ 1ኛ አመልካች አዛውንትና ገቢ የልላቸው መሆኑ መረጋገጡንና ይህ ምክንያት ደግሞ አመልካች ከመንግስት የተከራዩትን ንግድ ቤት ለሶስተኛ ወገን አከራይተው ገቢ ቢያገኙበትም ከቀበልው ጋር ያላቸውን የተከራይነት ግንኙነት ቀሪ የማያደርገው መሆኑ በመመሪያው መመልከቱን በምክንያትነት ይዞ የተጠሪን ክስ ውድቅ አድርጎታል። በዚህ ውሳኔ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም። ጉዳዩን ለከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ግራ ቀኙ እንዲከራከሩ ተደርጎ 1ኛ አመልካች የግል ቤት ያላቸውና በግቢያቸው ካሉት ሱቆችም ለልጅ ልጃቸው ሰጥተው የልጅ ልጃቸው የንግድ ፈቃድ አውጥቶ የፎቶ ግራፍ ስራ የሚሰሩበት መሆኑ ተረጋገጧል በሚል ምክንያት የበታች ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ሽሮ ቀበልው ከተጠሪ ጋር ያደረገው የኪራይ ግንኙነት ላቀጥል ይገባል በማለት ወስኗል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
የ1ኛ አመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት አመልካች ገቢ ያላቸው መሆኑ ተረጋገጧል በማለት የደመደመው የፍሬ ነገር ጉዳይ ከስልጣኑ ውጪ መሆኑንና በስር ፍርድ ቤት ከተረጋገጠው የማስረጃ ይዘት ውጪ መሆኑን በመጥቀስ ውሳኔው እንዲሻርላቸው ዳኝነት የጠየቁ ሲሆን 2ኛ ተጠሪ ደግሞ ለአሁኗ አመልካች የኪራይ ግንኙነት እንዲቀጥል ያደረገው በአግባቡ በማጣራት በመመሪያው መሰረት መሆኑና የመዋዋል ነጻነቱን በመጠቀም መሆኑን ጠቅሶ የከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ሲል መከራከሩን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም 2ኛ አመልካች 1ኛ አመልካች አዛውንትና ገቢ የልላቸው መሆኑን በማረጋገጥ ኪራዩን ከ1ኛ አመልካች ጋር ለመቀጠል በመፈለግ ከተጠሪ ጋር ያደረገውን የኪራይ ውል ማቋረጡ ያላግባብ ነው ተብሎ መወሰኑ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው በሰጡት መልስ 1ኛ አመልካች ገቢ ያላቸው መሆኑ መረጋገጡንና በመመሪያው መሰረት የኪራይ ውሉ ላቀጥልላቸው የማይገባ መሆኑን እንዲሁም በመመሪያው መሰረት ተጠቃሚ መሆን ያለባቸው ተጠሪ መሆናቸውን ዘርዝረው በከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም ተብሎ ላፀና ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል። አመልካቾችም የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልሳቸውን ሰጥተዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም 1ኛ አመልካች ገቢ ያላቸው መሆኑ ተረጋግጧል ተብሎ በመመሪያው መሰረት ተጠቃሚ ላሆኑ አይገባም ተብሎ በከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት መወሰኑ ባግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ አግኝተናል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው 1ኛ አመልካች ከ2ኛ አመልካች ጋር መስረተውት የነበረው የኪራይ ውል ተቋርጦ የነበረው በመመሪያ ቁጥር 3/2004 መሰረት ሲሆን አመልካች በመመሪያው መሰረት ጉዳዩ ያለመታየቱን በመግለፅ ለ2ኛ ተጠሪ ባቀረቡት አቤቱታ መነሻም ጉዳዩ እንደገና ታይቶ 1ኛ አመልካች አዛውንትና የራሳቸው ገቢ የልላቸው መሆኑ ተረጋግጦ እርምጃው እርምት ተወስዶ በተሳሳተ ውሳኔ ለተጠሪ ተሰጥቶ የነበረው የተከራይነት መብት ቀሪ ሁኖ ከ1ኛ አመልካች ጋር የነበረው የኪራይ ውል እንዲቀጥል መደረጉን ነው።የከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት 1ኛ አመልካች ገቢ ያላቸው መሆኑ ተረጋግጧል ያለው በስር ፍርድ ቤት መጣራት ሲደረግ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የተፃፈውን ደብዳቤ ይዘት በመመልከት ነው። በዚህ ረገድ የወረዳው አስተዳደር በደብዳቤ ቁጥር የካ/ወ1/06-003/6862/04 ሰኔ 04 ቀን 2004 ዓ.ም. ጽፎ የላከው ደብዳቤ ይዘት የአሁኗ አመልካች በግል ቤት ነዋሪ ሁነው የሚኖሩትም ከአራት የልጅ ልጆቻቸው ጋር መሆኑን ፣ በይዞታቸው በፊት በኩል ሱቅ ያለ ሁኖ በዚህ ሱቅ የልጅ ልጃቸው የሆነውን ቢኒያም ተስፋዬ በስሙ በተመዘገበ የንግድ ፈቃድ የፎቶ ቤት አገልግሎት የሚሰራበት መሆኑን የሚገልጽ ነው። ይህ የደብዳቤው ይዘት 1ኛ አመልካች የራሳቸው የሆነ የግል ይዞታ እንዳላቸውና በዚህ የግል ይዞታቸው ላይም የልጅ ልጃቸው የንግድ ፈቃድ አውጥቶ የሚሰራበት ሁኖ የንግድ ስራው የሚሰራበት ንብረት የ1ኛ አመልካች ስለመሆኑ ያረጋግጣል በሚል ምክንያት የከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት 1ኛ አመልካች ገቢ አላቸው ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው። ይሁን እንጂ 1ኛ አመልካች የግል መኖሪያ ያላቸውና በዚህ ይዞታቸው ስር ሱቅ የሚገኝ መሆኑ ከመረጋገጡ ውጪ ከመመሪያውም በፊትም ሆነ በኋላ በሱቁ ገቢ በትክክል እያገኙበት የነበረ ወይም እያገኙ ያሉበት መሆኑ አልተረጋገጠም። 1ኛ አመልካች ሱቁን በማከራየት ገቢ ማግኘት ይችሉ የነበረ መሆኑን ግን የደብዳቤው ይዘት የሚያስገነዝብ ቢሆንም ሱቁ ተይዞ የንግድ ስራው የሚከናወነው በልጅ ልጃቸው ከመሆኑም በላይ ስራው መመሪያ ቁጥር 3/2004 ከመውጣቱ በፊት የተጀመረና ሲሰራ የቆየ ከመሆኑ አንፃር ለቤተሰብ የሰጡትን ሱቅ ለግላቸው የኪራይ ገንዘብ በመቀበል ለራሳቸው ገቢ ማድረግ ነበረባቸው ማለት በነባራዊው ሁኔታ ላያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ውጤት ያላገናዘበ ምክንያት መሆኑ እሙን ነው።
በመመሪያው አንቀጽ 6.1 ስር አዛውንት የሆነ ከሆነና በማከራየት ከሚያገኙት ገቢ ልላ ገቢ የልለው መሆኑ ከ2ኛ ተጠሪ ጋር ያለውን የኪራይ ውል እንዳይቋረጥ የሚያደርግ መሆኑ በግልጽ የተመለከተ ሲሆን ቀድሞ እነዚህ ሁኔታዎች ሳይጣሩ የተሰጠው ውሳኔ ጉዳዩ በአግባቡ ከተጣራ በኋላ ቀሪ እንዲሆን መደረጉም ከአመልካች ሃላፊነትና ተግባር አንጻር ሲታይ የሚነቀፍ ካለመሆኑም በላይ በመመሪያው ላይ ያሉትን ቅድመ ሁኔታዎችን መሰረት አድርጎ ኪራዩን ከአመልካች ጋር ለመቀጠል በፈለገበት ሁኔታ ደግሞ 2ኛ አመልካች ከተጠሪ ጋር የኪራይ ግንኙነት እንዲቀጥል በፍርድ ኃይል ማስገደድ የመዋዋል ነጻነትን ጽንሰ ሀሳብ የሚጻረርና 2ኛ አመልካች ለማህበረሰቡ የሚያበረክተውን አገልግሎትም በተገቢው መንገድ እንዳይወጣ የማድረግ ውጤት የሚያስከትል ነው። በመሆኑም 1ኛ አመልካች ከመመሪያው በፊት በይዞታቸው ስር ያለውን ሱቅ ለልጅ ልጃቸው ሰጥተው የልጅ ልጃቸው የንግድ ስራ የሚሰሩበት መሆኑ ገቢ ያገኙ ይችሉ የነበረ መሆኑን ከሚያስገነዝብ በቀር በትክክል አመልካች ገቢ ነበራቸው፣ ይህንኑ ገቢም ለእለት መተዳደሪያቸው በማድረግ የሚኖሩ መሆኑን በማናቸውም መመዘኛ የማያሳይ ሁኖ እያለ የከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት 1ኛ አመልካች ገቢ ላያገኙ በሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ አሉ በሚል ምክንያት የበታች ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ መሻሩ የመመሪያውን ዓላማና መንፈስ ከመዋዋል ነጻነትና ከ2ኛ አመልካች ኃላፊነትና ተግባር ጋር ያላገናዘበ በመሆኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስለተገኘ ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1)መሰረት ተሽሯል።
በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ሰኔ 26 ቀን 2004 ተሰጥቶ በከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በመ/ ሐምል 10 ቀን 2004 ዓ/ም በትዕዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል።
2ኛ አመልካች ከ1ኛ አመልካች ጋር ያደረገውን ውል ላያቋርጥ አይገባም፣ ከተጠሪ ጋር የኪራይ ውል እንዲያደርግ የሚገደድበት ምክንያት የለም በማለት በድምጽ ብልጫ ወስነናል።
በዚሀ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
በዚህ መዝገብ የተሰጠው ውሳኔ ግልባጭ ከሰ/መ/ ጋርም ይያያዝ ብለናል።
No topics extracted.