No summary available.
የሰ/መ/ቁ/ 71972 ጥር 1 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ካሣሁን አያልው - ጠበቃ አቶ ፈንታ አያል ቀረቡ ተጠሪ፡- የምስራቅ ጎጃም ጎዛምን ወረዳ ጤና ጽ/ቤት - አልቀረቡም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ ለግንባታ ሥራ የሚከፈል ክፍያን የሚመለከት ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በጎዛምን ወረዳ ፍ/ቤት ነው። በወረዳው ፍ/ቤት አመልካች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
የክርክሩ መነሻ አመልካች ለወረዳ ፍ/ቤት ያቀረበው ክስ ነው። የክሱ ይዘት ተከሳሽ (ተጠሪ) የተመላላሽ ህክምና መስጫ አንድ ብሎክ ህንፃ ለማሰራት የጨረታ ማስታወቂያ አውጥቶ እኔ ተወዳድሬ አሸንፍአለሁ። ከተከሳሽ ጋር ሚያዝያ 2 ቀን 1999 ዓ.ም የግንባታ ስራ ውል ተዋውለን ግንባታው የሚከናወንበትን ቦታ አስረክቦኛል። ግንባታውን ሰርቼ የመጀመሪያ ክፍያ ጠይቄ፣ ከጠየቅሁት በመቀነስ ክፍያ እንዲፈጽም ለወረዳው ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት ደብዳቤ ፅፏል። እኔም ክፍያው የተሰራውን ሥራ የማይሸፍን መሆኑን በመግለጽ የግንባታውን ሥራ በመቀጠል ሁለተኛ ክፍያ በተቆጣጣሪ መሀንዲሱ ከፀደቀ በኋላ ተከሳሽ እንዲከፍለኝ ጥያቄ አቅርቤያለሁ። ተከሳሹ የክፍያ ሰርተፊኬቱ ለዞን ስራና ከተማ ልማት መምሪያ ያላከውና በውጤቱ ያልተስማማ መሆኑን በመግለፅ የግንባታ ሥራው ለጊዜው እንዲቋረጥ ሚያዝያ 3 ቀን 2000 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ አሳውቆኛል። ከዚህ በኋላ የጀመርከውን የግንባታ ሥራ በውሉ መሰረት አጠናቅቀህ እንድታስረክብ በማለት ሐምል 21 ቀን 2000 ዓ/ም ደብዳቤ የፃፈልኝ ሲሆን እኔ ያቀረብኩትን የክፍያ ጥያቄ መልስ አልሰጠኝም። ስለዚህ ተከሳሽ ለሰራሁት ሥራ መክፈል የሚገባውን ሁለተኛ ክፍያ ብር 88,913.39 (ሰማኒያ ስምንት ሺህ ዘጠኝ መቶ አስራ ሦስት ብር ከሰላሳ ዘጠኝ ሳንቲም) እዲከፍል ይወሰንልኝ የሚል ነው።
ተጠሪ በተከሳሽነት ቀርቦ ከሳሽ ያቀረበው የክፍያ ጥያቄ በግንባታ ስራ ውሉ ከተገለፀው አርባ ዘጠኝ ፐርሰንት ጭማሪ ያለው ነው። በግንባታ ሥራ ደንብና መመሪያ መሰረት ተጨማሪ ሥራና የሚከፈል ክፍያ ከሃያ አምስት ፐርሰንት በላይ ላሆን አይችልም። የዞኑ ሥራና ከተማ ልማት መምሪያ ስለ ክፍያው የሰጠው አስተያየት በጉዳዩ ተፈፃሚነት ያላቸውን የህግ ማዕቀፎችና የሙያ ሥነ ምግባር ደንብ የተከተለ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም። ስለዚህ የአመልካች ክስ ውድቅ ይደረግልኝ በማለት ተከራክሯል።
ተጠሪ በበኩሉም ከሳሽ (አመልካች) በግንባታ ሥራ ውሉ መሰረት ህንፃውን ሰርቶ አላስረከበም።
የግንባታ ሥራው የሚጠናቀቅበት የጊዜ ገደብ ያለፈ በመሆኑ ካሣ እንዲከፍል ይወሰንልኝ በማለት የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ለወረዳው ፍ/ቤት አቅርቧል። አመልካች፣ የተከሳሽ ከሳሽ የዳኝነት ያልከፈለ በመሆኑ የተከሳሽ ከሳሽነት ክሱን ሥርዓቱን አሟልቶ አላቀረበም። ግንባታው በወቅቱ ያልተጠናቀቀው የተከሳሽ ከሳሽ የግንባታ ሥራው ለጊዜው እንዲቋረጥ በፅሁፍ በማዘዙና በተከሳሽ ከሳሽ ጥፋት በመሆኑ ተጠያቂነት የለብኝም በማለት ተከራክሯል።
የወረዳው ፍ/ቤት፡- 1ኛ የከሳሽ የክፍያ ጥያቄ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም?
2ኛ/ ከሳሽ የጠየቀው ከግንባታ ሥራ ውሉ ውጭ ነው ወይስ አይደለም?
3ኛ/ የግንባታ ሥራው የተቋረጠው በተከሳሽ ጥያቄ ነው ወይስ አይደለም?
4ኛ/ ከሳሽ በግንባታ ሥራ ውሉ መሰረት ግድታውን ተወጥቷል ወይስ አልተወጣም?
የሚሉትን ጭብጦች በመያዝ ከሳሽ በተሰጠው ዲዛይን መሰረት መስራት የሚገባውን ሥራ የሰራ ስለመሆኑ በተከሳሽ ተቆጣጣሪ መሀንዲስ በማረጋገጥ የክፍያ የምስክር ወረቀት አጽድቋል። የዋጋው ልዩነት የተፈጠረው በመጀመሪያ በዲዛይኑ መሰረት ሥራውን ለመስራት የሚያስፈልገው የግንባታ ቁሳቁስና ሥራ መጠን (ቢል ኦፍ ኳንቲቲ) ተቆጣጣሪ መሀንዲስ ሲያወጣ ዝቅተኛ ግምት በማውጣቱ መሆኑ የዞኑ ስራና ከተማ ልማት መምሪያ ባደረገው ሙያዊ ምርመራ አረጋግጧል። ስለዚህ ከሳሽ የግንባታ ውሉን በተሰጠው ዲዛይን መሰረት ሥራውን የሰራ በመሆኑ ተከሳሽ ከሳሽ የጠየቀውን ብር 88,913.39 (ሰማንያ ስምንት ሺህ ዘጠኝ መቶ አስራ ሶስት ብር ከሰላሳ ዘጠኝ ሳንቲም) የመክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት አንደኛውንና ሁለተኛውን ጭብጥ ወስኗል። እንደዚሁም የግንባታ ሥራው የተቋረጠው በተከሳሽ ጥያቄ በመሆኑና ከሳሽ በግንባታ ሥራ ውሉ መሰረት ኃላፊነቱን የተወጣ በመሆኑ፣ ተከሳሽ ኃላፊነት የለበትም በማለት የተከሳሽን የተከሳሽነት ክስ ውድቅ አድርጎታል። የወረዳው ፍ/ቤት ተከሳሽ ክፍያውን ለከሳሽ እንዲከፍል፣ ከሳሽ በግንባታ ሥራ ውሉ መሰረት ግንባታውን አጠናቅቆ ለተከሳሽ እንዲያስረክብ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል። ተጠሪ ለዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርቧል። የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት የተጠሪን ይግባኝ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 መሰረት ሰርዞታል።
ተጠሪ በወረዳ ፍ/ቤት መከራከሪያ አድርጎ አቅርቧቸው የነበሩ ነጥቦችን በመዘርዘር የሰበር አቤቱታ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት አቅርቧል። የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ አመልካች ያቀረበው የክፍያ ጥያቄ በግንባታ ስራ ውሉ ከተገለፀው በላይ በመሆኑና የግንባታ ሥራ ውሉ በተዋዋዮች መካከል የህግ ያህል አስገዳጅነት ያለው የፍ/ብሕር ህግ ቁጥር 1731 የሚደነግግ በመሆኑ ይግባኝ ባይ (ተጠሪ) ለመልስ ሰጭው (አመልካች) የተጠየቀውን ክፍያ የመክፈል ኃላፊነት የለበትም በማለት የወረዳው ፍ/ቤትና የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጡትን ውሳኔ ሽሮታል።
አመልካች ሀምል 25 ቀን 2003 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ የግንባታ ሥራውን ለመስራት በጨረታ ተወዳዳሪ ሆኜ ያሸነፍኩት ህንፃውን በዲዛይኑ መሰረት ሰርቶ ለማስረከብ ነው።
የህንፃው ዲዛይን የግንባታ ሥራ ውሉ ክፍል እንደሆነ በግንባታ ሥራ ውሉ ተገልጿል።
ዲዛይኑ ተሰርቶ የተሰጠኝ በተጠሪ ነው። የዋጋ ልዩነቱ የተከሰተው የስራውንና ስራውን ለመስራት ያስፈልጋል ተብሎ በተጠሪ በኩል የተገመተውና በውሉ የተገለፀው መጠን (ቢል ኦፍ ኳንቲቲ) የግንባታ ሥራው በዲዛይኑ መሰረት በሚሰራበት ወቅት የማነስ ወይም የመብለጥ ሁኔታ በመከሰቱ ነው። ይህም የቁፋሮና ገረጋንቲ ሥራ በውሉ ሰላሳ ሁለት ሜትር ኪውብ እንደሚሆን የተገለፀ ቢሆንም ሥራው ሲከናወን መጨረሻ ላይ ሲለካ አርባ ስምንት ሜትር ኪውብ መሆኑ፣ የቢም የፎርምወርክና የጣውላ ስራ አስራ ሰባት ሜትር ኪውብ እንደሚሆን በውሉ የተገለፀ ቢሆንም በዲዛይኑ መሰረት ተሰርቶ ሲለካ ዘጠና አራት ሜትር ኪውብ መሆኑ በተቆጣጣሪ መሃንዲሱና በስራና ከተማ ልማት መመሪያ መረጋገጡና በአንፃሩ 366 ካ.ሜትር እንደሚሆን በውሉ የተገለፀው የላይኛው አፈር ማንሳት ሥራ በዲዛይኑ መሰረት ስራው ሲሰራ ሁለት መቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር እንደሆነ፣ በአጠቃላይ በዲዛይኑ መሰረት የግንባታ ሥራውን ለመስራት የሚያስፈልገውን የግንባታ ማቴርያልና የስራ መጠን ከሙያ አንፃር በአግባቡ ባለመሰራቱና ባለመገመቱ የተፈጠረ ልዩነት ነው። ስለዚህ እንደተጨማሪ ሥራ እንዲታይለት ተጠሪ ያቀረበው ክርክር የህግ መሰረት የለውም። ተጨማሪ ስራ ነው የሚባል ቢሆን እንኳን ሥራው የተሰራው በተጠሪ አማካሪና ተቆጣጣሪ መሃንዲስ የስራ ትዕዛዝ መሰረት በመሆኑ ተጠሪ ክፍያ ከመክፈል ነፃ የሚሆንበት የህግ መሰረት የለም።
ስለዚህ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል።
ተጠሪ በበኩሉ ህዳር 4 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ መልስ የዋጋ ልዩነት የተፈጠረው አመልካች ሆነ ብለው ከመሃንዲስ ዋጋ በታች ዋጋ በማቅረብ ጨረታ በማሸነፉ ነው። ስለዚህ ተጨማሪ ሥራ ሳይሰራ በጨረታ ካሸነፈበትና በግንባታ ሥራ ውሉ ከተገለፀው በላይ ዋጋ የምንከፍልበት ሁኔታ የለም። አመልካች በነጠላ ዋጋ በመግለፅ በዲዛይኑ መሰረት ለመስራት ውል እስከተዋዋለ ድረስ በውሉ መሰረት ግንባታውን ሰርቶ ለማስረከብ ግድታ አለበት። የአመልካች ጥያቄ ቅን ልቦናን መሰረት ያደረገ የውል አተረጓጐምና አፈፃፀም መርህን የተከተለ አይደለም።
አመልካች ተጨማሪ ሥራ ሳይሰራ ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፈለው ያቀረበው ጥያቄ የግንባታ አሰራር ደንብንና ልሎች የህግ ማዕቀፎችን መሰረት ያላደረገ በመሆኑ የክልሉ የሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ ሰጥቷል።
አመልካች በበኩሉ ታህሳስ 12 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ የመልስ መልስ በግንባታ ስራ ውሉ የተገለፀው የስራ መጠንና በተሰራው የስራ መጠን ላይ በመብለጥ ወይም በማነስ ተጠሪ በሞላው ዋጋ ምክንያት የመጣ አይደለም ልዩነቱ በስታንዳርድ ዲዛይኑ መሰረት ለጨረታ ቀርቦ የነበረው ቢል ኦፍ ኳንቲቲና የስራ መጠን ሥራው በዲዛይኑ መሰረት ከተሰራ በኋላ ከተገኘው ልኬት የመብለጥና (የማነስ) ልዩነት በማሳየቱ ነው። ስለዚህ አመልካች ለተጠሪ ሥራ ክፍያ ለመክፈል ያቀረበው ክርክር የህግ መሰረት የለውም በማለት ተከራክሯል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት አመልካች ለሰራው የግንባታ ሥራ የጠየቀውን ክፍያ ተጠሪ የመክፈል ኃላፊነት የለበትም በማለት የሰጠው ውሳኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ይህም የሚያሳየው የአመልካችና የተጠሪ የግንባታ የሥራ ውል አመልካችና ተጠሪ ሚያዝያ 9 ቀን 1999 ዓ.ም ያደረጉት የግንባታ ሥራ ውል ሰነድን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፣ ተጠሪ የግንባታ ሥራው እንዲሰራ ያወጣው ፕላንና የግንባታው ንድፍ (ዲዛይን)፣ በግንባታ ስራው ሂደት፣ ተጠሪ ለአመልካች በፍ/ብሕር ሕግ ቁጥር 3152 ንዑስ አንቀጽ 1 እና በፍ/ብሕር ህግ ቁጥር 3266(1) ድንጋጌዎች መሰረት የሰጣቸው ተጨማሪ የስራ ትዕዛዞች የግንባታ ሥራ ውሉ አካል ተደርገው የሚያዙ ናቸው።
ከዚህ አንፃር ስንመለከተው ተጠሪ በመደበው ተቆጣጣሪ መሀንዲስ መሰረት ግንቦት 1 ቀን 1999 ዓ.ም በተደረገው ውል ከተገለፀው የስራ መጠንና የግንባታ ጥቅል ዋጋ በላይ፣ የግንባታ ሥራውን በግንባታው ንድፍ (ዲዛይን) መሰረት ለማከናወን አስፈላጊ የሆኑ የስራ ትዕዛዞችን እየሰጠ አመልካቹ በመጀመሪያው ውል ከተገለፀው የስራ መጠንና ዋጋ በላይ አርባ ዘጠኝ ፐርሰንት የሚደርስ ተጨማሪ የስራ መጠን ያከናወነ በመሆኑ አመልካችና ተጠሪ በወረዳው ፍ/ቤት ያረጋገጡት እስከ ሰበር ባቀረቡት ክርክር የማይካካዱበት ጉዳይ ነው። አመልካች የግንባታ ሥራውን ሚያዝያ 9 ቀን 1999 ዓ/ም በተደረገው ልዩ የግንባታ ሥራ ውልና፣ የዚሁ ልዩ የግንባታ ሥራ ውል አካል በሆነው የግንባታው ንድፍ (ዲዛይን) እና አሰሪው(ተጠሪው) በግንባታ ሥራ ውሉ ሒደት በፅሁፍ በሰጠው የስራ ትዕዛዝ መሰረት በመሆኑ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት በአመልካችና በተጠሪ መካከል የተደረገውን የግንባታ ሥራ ውል ልዩ ባህሪና ይዘት ሣያገናዝብ፣ የአመልካችና የተጠሪ የግንባታ ሥራ ውል ግንቦት 1 ቀን 1999 ዓ.ም በተደረገው የስራ ውል ላይ የተገለፁት ሀያለ ቃሎች ብቻ እንደሆኑ በመግለፅና የፍትሐብሕር ህግ ቁጥር 1731 ድንጋጌን በመጥቀስ አመልካች የሰራው ተጨማሪ የግንባታ ሥራና የጠየቀው ክፍያ ከግንባታ ሥራ ውሉ ውጭ የቀረበ ነው በማለት የሰጠው ውሳኔና ትርጉም፣ ከላይ የገለፅናቸውን የፍ/ብሕር ህግ ቁጥር 3252 እና የፍ/ብሕር ሕግ ቁጥር 3266(1) ድንጋጌዎች ይዘት መንፈስና ዓላማ ያላገናዘበና መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል።
በያዝነው ጉዳይ ተጠሪ የሚያሰራውን ህንፃ በዲዛይኑ መሰረት ለመስራት የሚያስፈልገው የስራ መጠንን የገመቱት ባለሞያዎች የስራውን መጠን በማብዛት ወይም በመቀነስ፣ ትክክለኛ የሙያ ግምት አለማስቀመጣቸውና፣ አመልካች የግንባታ ሥራውን በዲዛይኑ መሰረት ሲያከናውን አንዳንድ የግንባታ ስራዎች በግንባታ ስራ ውሉ ከተገለፀው በላይ ከፍተኛ የስራ መጠን ጭማሪ ማሳየታቸው፣ አንዳንድ የግንባታ ስራዎች በግንባታ ስራ ውሉ ከተገለፀው በታች በዝቅተኛ የስራ መጠን የተከናወኑ መሆናቸው፣ በዚህ ምክንያት አመልካች የጠየቀው የግንባታ ስራ ክፍያ በግንባታ ሥራ ውሉ (ግንቦት 1 ቀን 1999 ዓ.ም በተደረገው ውል) ከተገለፀው በላይ እስከ አርባ ዘጠኝ ፐርሰንት የሚደርስ ጭማሪ ማሳየቱ በምስራቅ ጎጃም ዞን ስራና ከተማ ልማት መምሪያ ተጠሪ የሚያሰራውን ህንፃ ዲዛይን፣ ህንፃውን በዲዛይኑ መሰረት ለመስራት ያስፈልጋል ተብሎ ሥራው ከመጀመሩ በፊት በተቆጣጣሪ መሃንዲስ የወጣው የስራ መጠን ግምት፣ አመልካች የግንባታ ስራውን በዲዛይኑ መሰረት ሲሰራ የሰራው የስራ መጠንና ለዚህ ሥራ መጠን በግንባታ ሥራ ውሉ መሰረት ላከፈል የሚገባውን ክፍያ በመመርመርና በማጥናት ሙያዊ ማረጋገጫና ማስረጃ ሰጥቷል። ተጠሪ የመደበው ተቆጣጣሪ መሃንዲስ እስከ አስር ፐርሰንት ድረስ ለሚሰጠው ተጨማሪ የስራ ትዕዛዝ ከመጠባበቂያ በጀት እስከ ሃያ አምስት ፐርሰንት ለሚሰጠው የስራ ትዕዛዝ ውሉ ተሻሽሎ ክፍያ እንደሚከፈልና ከሃያ አምስት ፐርሰንት በላይ ለተሰጠው የጭማሪ ሥራ ትዕዛዝ ሥራው የተሰራ መሆኑ ተመርምሮና ተጠንቶ ክፍያ እንደሚፈፀም የዞኑ ሥራና ከተማ ልማት መምሪያ ለተጠሪ በሰጠው ሙያዊ ማብራሪያ እንደገለፀ፣ በስር ፍ/ቤት ተረጋግጧል።
የዞኑ ከተማ ልማት መምሪያ የሰጠው ሙያዊ ማብራሪያና ማረጋገጫ በፍ/ብሕር ህግ ቁጥር 3265 ንዑስ አንቀጽ 1 እና ንኡስ አንቀጽ 2 የተደነገጉ ድንጋጌዎችን መሰረት ያደረገ ነው። አመልካች ህንፃውን በዲዛይኑ መሰረት ሰርቶ ለማጠናቀቅ በተቆጣጣሪ መሃዲስ ተገምቶ ከነበረው ዋጋ ከሃያ አምስት ፐርሰንት በላይ ጭማሪ ካሳየ፣ አመልካች ሥራውን በተቆጣጣሪ መሃንዲሱ ትዕዛዝ መሰረት በአግባቡ ካከናወነ በተጨማሪነት የሰራው ሥራ አሰሪው (ተጠሪ) ክፍያ እንዲከፍለው ጥያቄውን ለዳኞች በማቅረብ ማስወሰን እንደሚቻል የፍ/ብሕር ህግ ቁጥር 3265 ንዑስ አንቀጽ 3 ይደነግጋል።
በመሆኑም አመልካች በተሰጠው የህንፃ ዲዛይን መሰረት ግንባታውን በሚያከናውንበት ወቅት ተጠሪ በመደበው ተቆጣጣሪ መሃንዲስ የስራ ትዕዛዝ ላከናወነው ግንባታ ክፍያ ጭማሪው ከሃያ አምስት ፐርሰንት በላይ ቢሆንም፣ የግንባታ ሥራው፣ ህንፃውን በዲዛይኑ መሰረት ለመስራት መከናወን ያለበት አስፈላጊ በመሆኑና፣ አመልካች ሥራውን የሰራ መሆኑ በተጠሪ ተቆጣጣሪ መሃንዲስ እና በዞኑ ስራ ከተማ ልማት መምሪያ በኩል የተረጋገጠ በመሆኑ፣ አመልካች ለሰራው ሥራ ክፍያ አልፈፅምም በማለት ከኃላፊነት ነፃ የሚሆንበት የህግ መሰረት የለም።
በመሆኑም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት ለጉዳዩ አግባብነት የልላቸውን የህግ ድንጋጌዎችን በመጥቀስና በመተርጐም አመልካች ላከናወነው የግንባታ ሥራ ክፍያ አይከፈለውም በማለት የሰጠው ውሳኔ፣ የፍ/ብሕር ህግ አንቀጽ 3244፣ አንቀጽ 3152(1) አንቀጽ 3265 እና አንቀጽ 3266(1) ድንጋጌዎችን ያላገናዘበና መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ ተሽሯል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የጎዛምን ወረዳ ፍ/ቤትና የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጡት ውሳኔ ፀንቷል።
በዚህ ፍ/ቤት የወጣውን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
No topics extracted.