No summary available.
ሰ/መ/ ጥር ዐ1 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት ነገረ ፈጅ መላኩ መኮንን ቀረቡ ተጠሪ፡- ዲ አም ሲ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግል ማህበር በልለበት የሚታይ መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን፤ መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ይህ የሰበር ጉዳይ ውልን አስመልክቶ የሚነሳን ክርክር በግልግል ዳኝነት እንዲያይ በውሉ ላይ የተሰየመው አካል በከሰመ ጊዜ ክርክሩ በማን ላታይ ይገባል? የሚለውን የሚመለከት ነው።
የጉዳዩም መነሻ የአሁን ተጠሪ በፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ያቀረበው የሽምግልና ዳኝነት አካል ይቋቋምልኝ ሲሆን የክሱም ፍሬ ቃል ከአመልካች ጋር መሰከረም 04 ቀን 1999 ዓ.ም ባደረግነው ውል ህንፃ ለመስራት ተስማምተናል። በውሉ መሰረት አለመግባባት ቢፈጠር ጉዳያችን በግልግል ዳኝነት ዕልባት እንዲያገኝ ተሰማምተናል። በዚህ መሰረት በመካከላችን የተፈጠረው አለመግባባት በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት የግልግል ዳኝነት ተቋም እንዲታይ አቅርቤ እርሱም ቀርቦ ጉዳዩን በግልግል ዳኝነት ማየት የሚችለው የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ባቋቋመው የዳኝነት ተቋም ላሆነ ይገባል በማለት ለግልግሉ ፈቀደኛ ሳይሆን ስለቀረ ጉዳያችንን አይቶ ለሚወስንልን የግልግል ተቋም እንዲመራልን በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ይሰጥልን የሚል ነው።
የአሁን አመልካችም ለዚሁ የክስ አቤቱታ በሰጠው መልስ ግራ ቀኛችን ባደረግነው ውል አንቀጽ 67 ላይ በመካከላችን የሚፈጠርን አለመግባባት በግልግል የሚዳኘው የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወይም እርሱ የሚወከለው አካል እንደሆነ በግልፅና በማያሻማ ሁኔታ ተመልክቷል። በአሁን ጊዜ ይህ የግልግል ተቋም የግልግል ተግባሩን መሥራት በማቆሙ፤
ሚኒስቴሩ የወከለው ልላ አካል ባለመኖሩ ጉዳዩ ወደ ግልግል ተቋም ላሄድ አልቻለም። ስለዚህ ይህ የግልግል የዳኝነት አካል በልለበት ወይም ሁለታችንም ያለልዩነት የመረጥነው ልላ የዳኝነት አካል በልለበት ሁኔታ በልላ የግልግል ዳኝነት ተቋም እንዲታይ አስገዳጅ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ በማለት ከሳሽ ያቀረበው ጥያቄ የህግ መሰረት የለውም በማለት ተከራክሯል።
ጉዳዩን የተመለከተውም የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኮ/መ/ ሚያዚያ 22 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት፡- በውሉ አንቀጽ 67 እንደተጠቀሰው አለመግባባት በሚከሰትበት ጊዜ በሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወይም በተፈቀደለት ወኪሉ እንዲፈቱ ተስማምተዋል። ጉዳዩን እንዲያይላቸው የመረጡት አካል በአሁኑ ጊዜ እንደልለ ተከሳሽ ገልጿል። ከሳሽም ይህንኑ አልተቃወመም። በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3336(1) ላይ አንድ የዘመድ ዳኛ ሆኖ የተመረጠ ወገን የሞተ ወይም ችሎታ ያጣ እንደሆነ በእርሱ ምትክ ልላ ዳኛ የሚመረጥ መሆኑ ተደንግጓል። በዚህ ጉዳይ በግራ ቀኙ የተሰየመው የግልግል ዳኛ ችሎታ ያጣ ወይም በአሁኑ ጊዜ የግልግል ሥራውን የማይሰራ በመሆኑ ጉዳዩ በልላ የግልግል ዳኛ ላታይ የሚገባ መሆኑን ፍ/ቤቱ አረጋግጧል።
ከሳሽ ይህንኑ ተገንዝቦ ጉዳዩ በልላ የዳኝነት አካል ቀርቦ እንዲታይ የሞከረ ቢሆንም ተከሳሽ በዚህ ከሳሽ በመረጠው አካል ለመዳኘት አልተስማማም። ስለሆነም በሁለቱም ወገኖች የተነሳውን አለመግባባት ሁለቱም በመረጡት ልላ ተቋም እንዲታይ መስማማት ካልቻሉ ፍ/ቤቱ በሚመድበው አካል ላታይ ስለሚገባ ክርክራቸው በጋራ በስምምነት በመረጡት የግልግል ዳኛ/ ተቋም/ ይታይ። በስምምነት የመረጡት አካል ከልለ በፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ዋና ፍጅስትራር በኩል ወደ ግልግል ዳኛ/ ተቋም/ ይመራ በማለት ወስኗል።
በዚህ ዉሳኔ ቅር ተሰኝቶ የአሁን አመልካች ያቀረበውን የይግባኝ አቤቱታ የፍደራል ከፍተኛው ፍ/ቤት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 337 እንደተደነገገው ተቀባይነትን ባለማግኘቱ በዚህ አኳኋን በሥር ባሉት ፍ/ቤቶች በየደረጃው የተሰጠው ዳኝነት መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነው በማለት እና በሰበር አቤቱታው በዝርዝር በማመልከት ጉዳዩ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ታርሞ ይወሰንለት ዘንድ የአሁን አመልካች ባቀረበው የሰበር አቤቱታ መነሻ ይህ የሰበር ጉዳይ ቀርቧል። የአሁን ተጠሪ በዚህ የሰበር ጉዳይ የበኩሉን ክርክር እንዲያቀርብ ጥሪ ቢደረግለትም ላቀርብ ባለመቻሉ ክርክሩን በፅሁፍ የማቅረብ መብቱ ታልፏል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ ባጭሩ የተመለከተው ሲሆን፤ እኛም ጉዳዩን እንደሚከተለው ተመልክተናል።
በዚህ ጉዳይ የህግ ትርጉም የሚያስፈልገው አከራካሪ ነጥብ ሆኖ የተገኘው የግራ ቀኙን አለመግባባት ተቀብሎ በግልግል ዳኝነት ለማየት የሚችል የግልግል ተቋም ፍ/ቤት በሚሰጠው ትዕዛዝ አማካኝነት ለመሰየም ይቻላል ወይስ አይቻልም? የሚለው ነው።
No topics extracted.
በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3328 ንዑስ ቁጥር (2) እንደተመለከተው አመልካችና ተጠሪ መስከረም 04 ቀን 1999 ዓ.ም ያደረጉትን የግንባታ ውል አስመልክቶ ወደ ፊት ክርክር በደረሰ ጊዜ ከዚሁ ውል ላነሳ የሚችለውን ክርክር በግልግል ዳኛ ወይም ለግልግል ተቋም ለማቅረብና ዳኝነት ለማግኘት የሚችሉ ስለመሆኑ በውሉ አንቀጽ 67 ጠቅሰው የተስማሙ ለመሆኑ የተካደ ጉዳይ አይደለም።
ከዚህም በቀር ይህንኑ ከውሉ ላመነጭ የሚችለውንም የግልግል ዳኛ/ተቋም/ ማንነት ሁሉ በስም ጠቅሰው የተስማሙ ለመሆኑም አላከራከረም።
ከዚሁ መሰከረም 04 ቀን 1999 ዓ.ም ከተደረገው ውል የመነጨውን ክርክሩን የአሁን ተጠሪ በዳኝነት አካል አቅርቦ ለማስወሰን በፈለገበት ጊዜ ጉዳያቸውን በግልግል ዳኝነት ተመልክቶ ዳኝነት እንዲሰጥበት በስም የተሰየመው የግልግል ተቋም የግልግል ዳኝነት ተግባሩን ማከናወን እንዳቆመም የተረጋገጠ የፍሬ ነገር ጉዳይ ነው።
ከላይ በፍሬ ነገር ረገድ ከተረጋገጡት ሶስት ጉዳዩች በመነሳት ግራ ቀኙን ያከራከረውን ጉዳይ ተመልክቶ ተገቢውን ዳኝነት ለመስጠት የሚቻለው የትኛው የዳኝነት አካል እንደሆነ ለይቶ ለመወሰን ለጉዳዩ ቀጥተኛ አግባብነት ያለው ድንጋጌ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3337 የተመለከተው እንጂ የሥር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የጠቀሰው የፍ/ብ/ሕ/ቁ 3336 እንዳልሆነ የሁለቱ ድንጋጌዎች ጥምር ንባብ አሰረጂ ነው። ይኸውም የአሁን አመልካችና ተጠሪ ከላይ ከተመለከተው ውል የመነጨ ክርክር ቢያጋጥማቸው ይህንኑ ክርክራቸውን በግልግል ዳኝነት ለመጨረስና በግልግል ዳኝነት ጉዳዩን የሚያየውን አካል ሳይቀር በስም ሰይመው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3328(2) እና በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3331 መሰረት በስምምነት ለይተው ያመለከቱ ወይም የመረጡ በመሆኑ በዚህ አኳኋን የተመረጠው የግልግል ዳኛ/ተቋም የግልግል ተግባሩን ማከናወን ማቆሙ ከተረጋገጠ ይህንኑ የግልግል ዳኛ/ተቋም/ ተክቶ የግልግል ዳኝነት ተግባሩን ላያከናውን የሚችል ልላ አካል ለመሰየም የሁለቱ የጋራ ስምምነት የግድ አስፈላጊ መሆኑን፣ ይህ ስምምነት ካልተገኘ ግን ጉዳዩን በግልግል ዳኝነት ለመጨረስ ያደረጉት ስምምነት ቀሪ ላሆን እንደሚገባ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3337 በግልፅ በመደንገጉ ለጉዳዩ ቀጥተኛ ተፈፃሚነት ያለው ይኸው ድንጋጌ በመሆኑ ነው።
በዚህ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3336(1) “….እንደሆነ የዘመድ ዳኛው ስምምነቱ ቀሪ ይሆናል።” ማለት ጉዳዩን እንደታሰበው በግልግል ለመጨረስ አድርገውት በነበረው ስምምነት ላገደዱ እንደማይችሉ እንጂ በውሉ ላይ በተሰየመው የግልግል ዳኛ ባይሆንም በፍ/ቤት አማካኝነት በማሰየም ልላ የግልግል ዳኝነት ጉዳዩን በግልግል ለመጨረስ ያደረጉት ስምምነት የፀና ነው የሚል ትርጉም ላያሰጥ እንደማይችል በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3325 እና 3344 ከተመለከቱት ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ግራ ቀኝ ወገኖች ካደረጉት የዋናው ጉዳይ ስምምነት ይዘት አንፃር ሲታይ ጉዳይቸውን በግልግል ዳኝነት አይቶ የሚወሰነው በሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወይም እርሱ በሚወክለው አካል በማለት አሰቀድመው በያዙት ውል ላይ በግልፅ ያመለከቱት ጉዳዩን በግልግል አይቶ ለመወሰን በጉዳዩ ላይ በቂ ዐቅምና ዕውቀት ያለውን ነው የሚል ሀሳብ ይዘው እንደሆነ ከተዋዋሉበት የውለታ ጉዳይ መገንዘብ ስለሚቻልና እንደዚያ ያለ አከራካሪ ጉዳይ ባጋጠመ ጊዜም የዘመድ ዳኛ ሥልጣንን አስመልክቶ በውል ላይ የተመለከቱት የስምምነት ቃሎች በጠባቡ መተርጐም እንዳለባቸውም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3329 ተደንግጓል።
ስለሆነም ግራ ቀኙ መስከረም 04 ቀን 1999 ዓ.ም ካደረጉት የግንባታ ውል የመነጨውን ክርክር አይቶ ላወስንላቸው የሚችለውን የግልግል ዳኛ/ተቋም/ በግልፅ በስም ጠርተው የሰየሙ በመሆኑ ክርክሩ በተነሳበት ጊዜም ይህ የግልግል ዳኛ የግልግል ዳኝነት ተግባሩን ማከናወኑን በማቆሙ ምክንያት ሁለቱም ወገኖች እንደነበራቸው ሀሳብ አሁንም ጉዳያቸውን በግልግል ተመልክቶ ላያይላቸው የሚችለውን ወገን ሁለቱም ወገኖች በጋራ ስምምነት ከሚሰየሙ በቀር፤ ጉዳዩን ተመልክቶ ላወስን የሚችልን የግልግል ተቋም ወይም አካል ፍ/ቤት የመወሰን ሥልጣን የለውም።
የአሁን ተጠሪ ከውሉ የመነጨውን ክርክሩን በዳኝነት አካል አቅርቦ የማስወሰንና ፍትህ የማግኘት መብቱ ላጣበብ ስለማይገባም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3337 የተመለከተው ድንጋጌ ከህገ መንግስቱ አነቀጽ 37 ጋር ተገናዝቦ ሲታይ ይህንን ጉዳይ በጋራ ስምምነት በሚሰይሙት አካል አቅርበው የማስወሰን መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በጉዳዩ ከተካተተው የገንዘብ መጠን እና ከተከራካሪ ወገኖች ማንነት አንፃር በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 5፣ 11(1) እንደተደነገገው ጉዳዩን አይቶ ለመወሰን ሥልጣን ያለው የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ላሆን ይገባል በማለት መተርጐም ሲገባ ያለ የጋራ ስምምነት የሽምግልና ዳኛ ላያቋቁም የሚያስችል ትዕዛዝ በሥር ፍ/ቤቶች መሰጠቱ ከላይ በፍርድ ሐተታው እንደተገለፀው ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ከማድረግ አንፃር መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ስላገኘነው የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኮ/መ/ በቀን 22/8/2004 ዓ.ም የሰጠው ፍርድም ሆነ የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በኮ/ ሰኔ 04 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ ተሽሯል።
ግራ ቀኙ ከዚህ ቀደም መስከረም 04 ቀን 1999 ዓ.ም ባደረጉት ስምምነት መሰረት በመካከላቸው ከዚህ ውል የተነሳውን አለመግባባት በጋራ ስምምነት ላያይላቸው የሚችለውን የግልግል አካል በእራሳቸው ከሚያቋቁሙ በቀር በፍ/ቤት የግልግል አካል ላቋቋም አይቻልም ብለናል።
ይህ የጋራ ስምምነት ካልተገኘ የአሁን ተጠሪ ሥልጣን ባለው ፍ/ቤት ጉዳዩን አቅርቦ የማስወሰን እና ፍትህ የማግኘት መብቱ የተጠበቀ ነው ብለናል።
በዚህ የሰበር ችሎት ክርክር ምክንያት ግራ ቀኙ ያወጡትን ወጪና ኪሣራ በየራሳቸው ይቻሉ።