No summary available.
የሰ/መ/ ጥር 2 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ልዩ የገንዘብ እገዛ ተቋም ጠበቃ ሺፈታ በለጠ ቀረቡ ተጠሪዎች፡-
በዚህ መዝገብ የቀረበው ክርክር ከዋስትና ውል አፈፃፀም ጋር የተያያዘ ነው። ጉዳዩ በተጀመረበት በፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት የአሁኖቹ ተጠሪዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች የነበረ ሲሆን 1ኛ ተከሣሽ የነበረው ደግሞ የሰበር ክርክሩ አካል ያልሆነውና በአሁኑ አመልካች /በስር ከሳሽ/ መስሪያ ቤት በሰራተኛነት በተቀጠረበት ጊዜ የአሁኖቹ ተጠሪዎች እያንዳንዳቸው ለብር 50,000.00 /ሀምሣ ሺህ ብር/ የዋስትና ግድታ ገብተውለት ነበር የተባለ ግለሰብ ነው። አመልካች ክስ ያቀረበው 1ኛ ተከሳሽ ይዞት የተሰወረውን ገብዘብ ብር 109,487.95 2ኛ እና 3ኛ ተከሣሾች በዋስትናቸው መጠን ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍሉ ለማስወሰን ሲሆን የተጠሪዎቹን የዋስትና ውሎች አያይዞ አቅርቧል።
የዋስትና ውሉን አስመልክቶ 1ኛ ተጠሪ በወቅቱ በዋሰትና ውሉ ላይ ለመፈረም ወደ ከሳሽ ተቋም ሄጄ የከሳሽ ተወካይና ምስክሮች ስላልነበሩና ስላልፈረሙ ውሉ ረቂቅ ሆኖ ቀርቶአል።
ከሳሽ የራሱን ተወካይ እና ምስክሮቹን ያስፈረመው በልላ ጊዜ ነው በእጄ በሚገኘውና በማስረጃነት ባቀረብኩት የዋስትና ውሉ ቅጂ ላይ የከሳሽ ተወካይና የምስክሮች ፊርማ የለበትም በማለት የተከራከረች ሲሆን 2ኛ ተጠሪ በበኩሉ የዋስትና ውሉ በሁለት ምስክሮች ፊት ያልተደረገ በመሆኑ ፈራሽ ነው በማለት ተከራክሯል።
ፍ/ቤቱም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ 1ኛ ተጠሪን አስመልክቶ ከሳሽ የቀረበው የዋስትና ውል የተሟላ ቢሆንም በ1ኛ ተጠሪ/በስር 2ኛ ተከሳሽ/ በኩል የቀረበው የዋስትና ውል ግን የከሳሽና የምስክሮች ፊርማ የማይታይበት መሆኑን ከሳሽ ያቀረበው የዋስትና ውል በኮምፒተር ጽሑፍ የተዘጋጀ ሆኖ የምስክሮች ስም ግን በእጅ ጽሑፍ የተፃፈ መሆኑን ይህም የዋስትና ውሉ የተደረገው በሁለት ምስክሮች ፊት እንዳልሆነ እና ከሳሽ ምስክሮቹን ያስፈረመው ውሉ ከተደረገ በኋላ እንደሆነ መንዘብ የሚያስችል መሆኑን 2ኛ ተጠሪን /የስር 3ኛ ተከሳሽን/ አስመልክቶ በዋስትና ውሉ ግርጌ በእጅ ጽሑፍ ተሞልቶ የሚታየው የአንድ ምስክር ስም እና ፊርማ ብቻ እንደሆነ እና የዋስትና ውል በጽሑፍ ሆኖ በሁለት ምስክሮች ካልተረጋገጠ ውጤት እንደማይኖረው በፍ/ሕ/ቁ 1725/ሀ/ እና 1727/2/ ተደንግጐ የሚገኝ መሆኑን በዝርዝር በመግለጽ በክሱ የተጠየቀውን ገንዘብ 1ኛ ተከሳሽ እንዲከፍል 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ግን እንዲሰናበቱ ውሣኔ የሰጠ ሲሆን የፍ/ከ/ፍ/ቤትም ውሣኔው ግድፈት የለበትም በማለት የአሁኑ አመልካች ያቀረበለትን ይግባኝ ዘግቶ አሰናብቷል።
አመልካች የሰበር አቤቱታውን ያቀረበው የስር ፍ/ቤቶች ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው በማለት ሲሆን የዋስትና ውሉ በጽሑፍ ሆኖ በሁለት ምስክሮች ስላልተረጋገጠ የፍ/ሕ/ቁ 1727/2/ መስፈርትን አያሟላም ተብሎ ውድቅ የመደረጉን አግባብነት ለማጣራት ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ያስቀርባል በመባሉ ግራ ቀኙ በሰበር ደረጃ የጽሑፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ባጭሩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን አኛም የዋስትና ውል በፍ/ሕ/ቁ 1727/2/ መሰረት በሁለት ምስክሮች ፊት ካልተረጋገጠ ውጤት አይኖረውም ሲሉ የአሁኖቹን ተጠሪዎች በማሰናበት የስር ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት መሆን አለመሆኑን መርመረናል።
በዚህም መሰረት 1ኛ ተጠሪን በተመለከተ አመልካች ለስር ፍ/ቤት በማስረጃነት ያቀረበው የዋስትና ውል የተጠሪዋ የአመልካች ተወካይ እና የሁለት ምስክሮች ፊርማ የሚታይበት መሆኑ ተረጋግጦአል። በውሉ ላይ መፈረሟንም 1ኛ ተጠሪ አልካደችም 1ኛ ተጠሪ በወቅቱ ውሉን ለመፈረም ወደ ከሳሽ ተቋም ሄጄ የተቋሙ ተወካይና ምስክሮች ስላልነበሩና ስላልፈረሙ ውሉ ረቂቅ ሆኖ ቀርቶአል ከማለት በስተቀር የሰበር ከሳሽ በማስረጃነት ያቀረበውና በተጠሪዋ ያልተካደው ፊርማ የሚገኘበት የዋስትና ውል የተሟላ ቅጅ በከሳሽ እጅ እንድት ላገባ ወይም ላገኘ እንደቻለ ተጠሪዋ በግልጽ ያቀረበችው ክርክር አለመኖሩን የመዝገቡ ግልባጭ ያስረዳል።
ነገሩን በመሸሽ የቀረበ የዚህ ዓይነት ክርክር ደግሞ ውሉ በሁለት ምስክሮች የተረጋገጠው እርሷ በፈረመችበት ጊዜ እንደሆነ ተጠሪዋ አምና እንደተቀበለች የሚያስቆጥር መሆኑን ከፍ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 83 እና 235 ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል። የስር ፍ/ቤቶችም የተጠሪዋን ክርክር በዚህ አግባብ ተገንዝበው ውሣኔ መስጠት ሲገባቸው ውሉ በሁለት ምስክሮች ፊት መረጋገጡን እንደካደች አድርገው መውሰዳቸው በክርክሩ ስነስርአታዊ አመራር ረገድ ስህተት መፈፀማቸውን የሚያመለክት ነው።
No topics extracted.
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሁለቱም ተጠሪዎች በተናጠል የገቡት የዋስትና ውል በሁለት ምስክሮች ፊት ያልተረጋገጠ ነው ቢባል እንኳን ተጠሪዎቹ በፍ/ሕ/ቁ 1727 የተመለከተውን የፎርማላቲ መስፈርት ጠቅሰው የሚከራከሩት ውሉ በሁለት ምስክሮች ፊት አልተረጋገጠም በማለት እንጂ አልፈረምንበትም በማለት አይደለም። በመሰረቱ ሕጉ የውሉን በሁለት ምስክሮች ፊት የመረጋገጥ አስፈላጊነት የደነገገው በውሉ መደረግ ወይም ይዘት ወይም መሰል ሁኔታዎች ላይ በተዋዋዮች መካከል ላነሳ የሚችለውን አለመግባባት ወይም ክርክር ውሉ ሲደረግ በነበሩ ግለሰቦች እገዛ ጭምር ለመፍታት እንዲያስችልም በማሰብ እንደሆነ ይታመናል። በተያዘው ጉዳይ ተጠሪዎቹ ውሉን ስላለመፈረማቸው ወይም ስለውሉ ቃል ያቀረቡት ማናቸውም ዓይነት ክርክር አለመኖሩን መዝገቡ ያስረዳል። ስለራሳቸው ፊርማ እና ስለ ውሉ ቃል በተጠሪዎቹ የተካደ ነገር ከልለ ደግሞ እነዚህ ነጥቦች ቢካዱ ኖሮ በአስረጅነት ላቀርቡ ይችሉ ነበር የሚባሉት ምስክሮች በውሉ ላይ ሳይፈርሙ መቅረታቸው የተጠሪዎቹን የውል ግድታ ተፈፃሚነት ላያስቀር የሚችል አይደለም።
ሲጠቃለል የስር ፍ/ቤቶች ክርክሩን በዚህ አግባብ መምራት ሲገባቸው የዋስትና ውሉ በሁለት ምስክሮች ፊት ስላልተረጋገጠ አይፀናም ሲሉ ተጠሪዎቹን በማሰናበት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሣኔ ተሰጥቶአል።
ው ሣ ኔ
ተጠሪዎቹን አስመልክቶ የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት በመ/ በ25/ዐ3/ዐ4 የሰጠው ውሣኔ እና የፍ/ከ/ፍ/ቤት በመ/ በዐ1/ዐ8/ዐ4 የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 348/1/ መሰረት ተሽረዋል።
በስር 1ኛ ተከሣሽ በአቶ ተስፋዬ በላይ ላይ የተወሰነውን ገንዘብ ተጠሪዎቹ በገቡት የዋስትና ግድታ መጠን ከተከሳሹ ጋር በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍሉ ወስነናል።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
የውሣኔው ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
ክርክር ውሣኔ ያገኘ በመሆኑ መዝገቡ ተዘግቶአል።