No summary available.
ህዳር 17 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ መኰንን ገ/ህይወት ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የዳንግላ ማዘጋጃ ቤት ፍትህ ቢሮ - ዐ/ህግ እዮብ ጌታቸው ተጠሪዎች፡- 1/ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ - አልቀረቡም 2/ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ - ነ/ፈጅ ተመስገን ዘውድ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
መዝገቡ የቀረበው አመልካች የአማራ ክልል የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው።
ጉዳዩ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ አመዘጋገብ ስህተት ላደረሰ ኪሳራ ካሳ የመክፈል ኃላፊነትን የሚመለከት ነው።
የክርክሩ መነሻ የአንደኛ ተጠሪ ያቀረበው ክስ ነው። የክሱ ይዘት በስር ፍ/ቤት ሁለተኛ ተከሳሽ የነበረችው ወ/ሮ ዘውድ ሽፈራው ጥር 14 ቀን 1988 በተፈረመ የብድር ውል ለሆቴል ህንፃ ግንባታ የሚውል ብር 110,800 (አንድ መቶ አስር ሺህ ስምንት መቶ ብር) ከከሳሽ (አንደኛ ተጠሪ) ተበድራ ወስዳለች። ተበዳሪዋ ይህንን ገንዘብ የወሰዱት የካርታ ቁጥሩ 614/935/61 በሆነው ይዞታ ላይ የሰፈረውን የድርጅት ቤት በመያዣነት እንዲያዝ በመስማማት ሲሆን ይሕ የመያዣ ውል እንዲመዘገብልን ጠይቀን የዳንግላ ማዘጋጃ ቤት (አመልካች) በቁጥር 642/4188 ጥር 24 ቀን 1988 ዓ.ም የማይንቀሳቀስ ንብረቱን ለከሳሽ ብድር የመጀመሪያ መያዣ አድርጎ የመዘገበው መሆኑን አረጋግጦልኛል። ሆኖም ሁለተኛ ተከሳሽ (ተበዳሪዋ) በብድር የወሰደችውን ገንዘብ ባለመክፈሐ፣ ከሳሽ (ሁለተኛ ተጠሪ) መያዣውን በሀራጅ በመሸጥ የብድር ገንዘቡን ለመሰብሰብ ሲንቀሳቀስ፣ ይኸው የተበዳሪዋ የማይንቀሳቀስ ንብረት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሀምል 11 ቀን 1987 የብድር ውል ሲይዝ ቤቱን በመያዣነት የያዘው መሆኑን በመግለፅ ደብዳቤ ፅፏል። አንደኛ ተከሳሽ (አመልካች) ቤቱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ላበደረው ብድር መያዣ መሆኑን ቢገልፅልኝ ኖሮ የብድር ገንዘቡን ለሁለተኛ ተከሳሽ አልሰጥም ነበር። ስለዚህ ከተበዳሪዋ የምንፈልገውን ብር 265,661.40 እንዲከፍል ይወሰንልኝ የሚል ይዘት ያለው ክስ አቅርቧል። አመልካች በተከሳሽነት ቀርቦ ለንብረቱ ሁለት የይዞታ ማረጋገጫ ያልሰጠሁ በመሆኑ በኃላፊነት አልጠየቅም። ከሳሽ መጀመሪያ የተበዳሪዋን ንብረት በመከታተል ዕዳውን ለመሰብሰብ ሳይሞክር ክስ ማቅረቡ ተገቢ አይደለም። ሁለተኛ ተጠሪ ጣልቃ ገብቶ ቤቱ መያዣው ስለነበር በአዋጅ ቁጥር 97/90 በተሰጠው ሥልጣን መሰረት የሰጠው መሆኑን አረጋግጧል። ሁለተኛ ተጠሪ ለሁለተኛ ተከሳሽ ብድር ስናበድር ቤቱ የማይሸጥ የማይለወጥ ፣ የዕዳ መክፈያ መያዣ መሆኑን በቁጥር 30/2834 ሀምል 13 ቀን 1987 በፃፈው ደብዳቤ መያዣውን መዝግቦ አረጋግጦልናል የሚል ክርክር አቅርቧል።
የስር ፍርድ ቤት አመልካች የማይንቀሳቀሰው ንብረት በሁለተኛው ተጠሪ በመያዣነት የተያዘ መሆኑን ለአንደኛ ተጠሪ ባለመግለፁ በአንደኛ ተጠሪዎች ላይ ለደረሰው ኪሳራ ኃላፊነት እንዳለበት ወስኗል። አመልካች ኃላፊ የሚሆነው አንደኛ ተጠሪ በመጀመሪያ የሁለተኛ ተከሳሽን ንብረት በማፈላለግ ዕዳውን ለማስከፈል ተገቢውን ትጋት አድርጎ ላልተከፈለው ገንዘብ እንደሆነና አመልካች የሚከፍለው ካሳ መጠን በመያዣነት ተሰጥቶ የነበረው የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሚያወጣው ዋጋ በላይ መሆን እንደልለበት በመግለፅ ውሳኔ ሰጥቷል። አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቧል።
ይግባኝ ሰሚው ችሎት ይግባኙን በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 ሰርዞታል። አመልካች የሰበር አቤቱታ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት አቅርቦ የሰበር ችሎቱ ጉዳዩን በሰበር የማየት ሥልጣን የለኝም በማለት አሰናብቶታል።
አመልካች መጋቢት 7 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ንብረቱ የሁለቱን ባንኮች ዕዳ የሚሸፍን ከሆነ መያዣው ላመዘገብ የሚችልበት ሁኔታ ያለ በመሆኑ አመልካች ጥፋት እንደፈፀመ መታየቱ ተገቢነት የለውም። መያዣው አስር ዓመት ያለፈው ስለሆነ ህጋዊ ውጤት ስለማይኖረው አመልካች መጠየቁ ተገቢ አይደለም። የመያዣው የገንዘብ መጠን ያለተገለፀ በመሆኑ ውሉ ውጤት የለውም። ስለዚህ የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ማፅናቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት በማለት አመልክቷል።
አንደኛ ተጠሪ አመልካች ያቀረበው የሰበር አቤቱታ የህግ መሰረት የልለው ነው። አመልካች ማድረግ የሚገባውን ጥንቃቄ በማድረግ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ በአንደኛ ተጠሪ ላይ የደረሰውን ኪሳራ የመካስ ኃላፊነት አለበት። የበታች ፍ/ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት ነሐሴ 30 ቀን 2004 ዓ.ም በፅሁፍ መልስ ሰጥቷል። ሁለተኛ ተጠሪ አመልካች እኔን በተጠሪነት መዝግቦ የሰበር አቤቱታ የሚያቀርብበት ምክንያት የለም በማለት ነሐሴ 30 ቀን 2004 ዓ.ም መልስ ሰጥቷል። አመልካች መስከረም 10 ቀን 2005 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ ሰጥቷል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍ/ቤቶች አመልካች በአንደኛ ተጠሪ ላይ ለሚደርሰው ኪሣራ በመያዣያ የተያዘው የማይንቀሳቀስ ንብረት የሚያወጣውን ዋጋ ያህል በኃላፊነት ይጠይቃል በማለት የሰጡት ውሳኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ሆኖም የአመልካች የማይንቀሳቀስ ንብረት ለአንደኛ ተጠሪ ብድር የመጀመሪያ ደረጃ መያዣ መሆኑን በማረጋገጥ እንደመዘገበው ለአንደኛ ተጠሪ ጥር 14 ቀን 1988 ዓ.ም ከመግለፁ በፊት ይህንኑ ተመሣሣይ ንብረት ሁለተኛ ተጠሪ ለወ/ሮ ዘውድ ሽፈራው ሀምል 11 ቀን 1987 በተደረገ የብድር ውል ለሰጠው የብድር ገንዘብ የመጀመሪያ ደረጃ መያዣ አድርጎ የመዘገበ መሆኑን ሀምል 11 ቀን 1987 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ ለሁለተኛው ተጠሪ እንዳረጋገጠና፣ ይህንን ዕውነታ ለአንደኛው ተጠሪ ያልገለፀ መሆኑን በዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት ተረጋግጧል። በዚህ ምክንያት ባለዕዳዋ ወ/ሮ ዘውድ ሽፈራው የማይንቀሳቀሰውን ንብረት በመጀመሪያ ሁለተኛ ተጠሪ ለወሰደችው ብድር መያዣ እንደሆነ ተስማምታና መያዣውም በፍታብሕር ህግ ቁጥር 3052 በአመልካች ተመዝግቦ በሁለተኛ ተጠሪ ገንዘብ ተበድራ ከወሰደች በኋላ ሰባት ወራት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ይህንኑ በዕዳ ያስያዘቸውንና ያስመዘገበችውን ቤት በመጀመሪያ ደረጃ መያዣ አድርጋ ለአንደኛ ተጠሪ በማቅረብ የብድር ገንዘብ የወሰደች መሆኑ ተረጋግጧል።
ሁለተኛ ተጠሪ በመያዣው ላይ ያለውን የቀዳሚነት መብት በመጠቀም ለዕዳው መክፈያ እንዲሆነው ንብረቱን የሸጠው በመሆኑ አንደኛ ተጠሪ በንብረቱ ላይ የነበረውን የመያዣ መብት ሙሉ በሙሉ ያጣና በዚህም ምክንያት ዕዳውን ለማስከፈል ችግር ላይ የወደቀና ኪሳራ የደረሰበት መሆኑን ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው ፍ/ቤቶች ተረጋግጧል። ከዚህ አንፃር ሲታይ አመልካች የማይንቀሳቀሰው ንብረት የተጠሪዎችን ዕዳ እንደሚሸፍንና ጥፋት እንዳልፈፀመ በመግለጽ የሚያቀርበው ክርክር በስር ፍ/ቤት የተረጋገጠውን ነባራዊ እውነታ መሰረት ያላደረገና ተገቢነት የልለው ሆኖ አግኝተነዋል።
ይህም ሁለተኛው ተጠሪ በማይንቀሳቀሰው ንብረት ላይ የቀዳሚነት መብት /የመጀመሪያ ደረጃ የመያዣ መብት/ የሚኖረው ሁለተኛው ተጠሪ መሆኑን የፍትሐብሕር ህግ ቁጥር 3081 ድንጋጌዎችን በማየት ለመገንዘብ ይቻላል። ንብረቱ የሁለተኛ ተጠሪ መያዣ መሆኑን አረጋግጦ አመልካች ሀምል 11 ቀን 1987 ዓ.ም ከመዘገበ፣ ይኸው ንብረት አንደኛ ተጠሪ በጥር ወር 1988 ዓ.ም ለሰጠው ብድር የመጀመሪያ መያዣ የሚሆንበት የህግ አግባብ የለም። ስለዚህ አስቀድሞ በመያዣነት የተያዘውንና የተመዘገበውን የባለዕዳዋን ቤት በመጀመሪያ መያዣነት መዝግቤአለሁ በማለት አመልካች ጥር 14 ቀን 1988 ዓ.ም ለአንደኛ ተጠሪ የሰጠው ማረጋገጫ የፍ/ብሕር ህግ ቁጥር 3081 አስገዳጅ ህግ ድንጋጌዎች የሚቃረንና ህጋዊ ውጤት የልለው አንደኛ ተጠሪንም ያለመያዣ ያስቀረ ተግባር ነው።
የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ የሚመዘገበው ንብረቱ በሚገኝበት አገር ርዕተ መዝገብ መሆኑንና ንብረቱ እንዲመዘግብ ጥያቄ የቀረበለት የመንግስት አካል (ሰራተኛ) የመያዣ ውሉን የሚመዘግበው በህግ ስለማንቀሳቀሱ ንብረቶች አመዘጋገብ ሥርዓት የተደነገጉትን ደንቦች መሰረት በማድረግ መሆን እንዳለበት የፍ/ብሕር ህግ ቁጥር 3052 እና የፍ/ብሕር ህግ ቁጥር 3053 ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌዎችን በጣምራ በማንበብ ለመረዳት ይቻላል። አንደኛ ተጠሪ የማይንቀሳቀሰውን ንብረት በመጀመሪያ ደረጃ መያዣነት ይዣለሁ በሚል እምነት ያለምንም መያዣ ለባለዕዳዋ ገንዘብ ያበደረው አመልካች (የአመልካች) የሚመለከታቸው ሰራተኞች ንብረቱ ቀደም ብሎ በሁለተኛው ተጠሪ የተያዘና መያዣውም በማይንቀሳቀስው ርዕተ መዝገብ የተመዘገበ መሆኑን በጥንቃቄ በመመርመር ስላልገለፁለት መሆኑን ፍሬ ጉዳይ የማጣራት ሥልጣን ባለው ፍ/ቤት ተረጋግጧል። ይህም በፍ/ብሕር ህግ ቁጥር 1640 ንዑስ አንቀጽ 2 በተደነገገው መሰረት፣ አመልካችን በአንደኛ ተጠሪ ላይ በደረሰው ጉዳት በኋላፊነት የሚያስጠይቅ እንደሆነ ከህጉ ድንጋጌ ይዘትና ዓላማ ለመገንዘብ ይቻላል።
ከላይ በገለፅናቸው ምክንያቶች የበታች ፍ/ቤቶች አመልካች ንብረቱ ቀደም ብሎ በመያዣነት ሁለተኛው ተጠሪ የያዘውና መያዣውንም ያስመዘገበው መሆኑን ባለመግለፁ አንደኛው ተጠሪ በንብረቱ ላይ የአንደኛ ደረጃ መያዣ መብት አለኝ በሚል ዕምነት ለባለዕዳዋ በብድር ገንዘብ በመስጠት ለደረሰበት ኪሣራ በኃላፊነት የሚጠየቅ መሆኑንና አመልካች በመያዣነት ተመዝግቦ የነበረው የማይንቀሳቀስ ንብረት የሚያወጣውን ዋጋ ያህል ብቻ በኃላፊነት እንደሚጠይቅ ይህም ባለዕዳዋ ለመክፈል ሣትችል ስትቀር መሆኑን በመግለፅ የሰጠው ውሳኔ ከላይ የተዘረዘሩትን የህግ ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገና የህግ ስህተት የልለበት ነው በማለት ወስነናል።
የአማራ ክልል የምዕራብ ጉጃም ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት ውሳኔ ፀንቷል።
በዚህ ፍ/ቤት ያወጡትን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
No topics extracted.