No summary available.
ህዳር 03 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ኢትዮ ቴልኮም - ነገረጅ ፈቃዱ ኃይል ቀረቡ ተጠሪ፡- ፒቲኢ ኢንተርናሽናል ኢንኮፖሬትድ - ተወካይ ዶ/ር ብርሃነ ገብራይ ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ ከስራ ውል ጋር ተያይዞ የመልካም ስራ አፈፀፃጸም ዋስትና ገንዘብ ይለቀቅልኝ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በግልግል ጉባኤ ነው። የግልግል ጉባኤው ግራ ቀኙ ሚያዚያ 09 ቀን 2000 ዓ/ም በፈረሙት ውል መሰረት የተቋቋመ ሲሆን ግልግሉ በውሉ መሰረት ከተቋቋመ በኋላ ክሱን ያቀረበው የአሁኑ ተጠሪ ነው። የተጠሪ ክስ ይዘትም በአሁኑ ተጠሪና በአሁኑ አመልካች በታህሳስ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. ተደርጎ ሚያዚያ 09 ቀን 2000 በተፈረመና ከታህሳስ 25 ቀን 2000 ዓ/ም እስከ ነሐሴ 28 ቀን 2000 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ውል ተዋውለው እንደነበር፣ ውሉ የተደረገውም አመልካች አለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴልኮም ኩባንያ ለመፍጠር እገዛ ለማድረግ ተግባር መሆኑና በውሉ መሰረት ተጠሪ የአመልካችን የሰው ኃይል ችሎታ ከፍ በማድረግ የአሰራር ሂደቶችን፣ ፖላሲዎችንና የአሰራር ደንቦችን ለማጎልበት፣ አመልካች የአሰራር ሂደቱን ለመደገፍ በጥቅም ላይ ያዋለውን ቴክኖሎጂ እንዲረዳ ለማስቻል፣ የአሰራር ሂደቱ ከቴክኖሎጂው ጋር የተጣጣመ መሆኑን ማረጋገጥና ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም በጥቅም ላይ የዋሉ ሲስተሞችና ሥርዓቶችን በተግባር ላይ መዋላቸውን ማረጋገጥ፣ ለአመልካች ፐርሶኔል /የሰው ኃይል/ ተገቢ የሆነ መዋቅርን በማቅረብ እነዚህን ቴክሎኖሎጂዎችና የአሰራር ሂደቶችን በተሳካ ሁኔታ በጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማስቻል፣ በትራንስፎርሜሽን /ለውጥ/ ሂደት ተሳትፎ የሚያደርጉ ፐርሶኔሎችን መሰረታዊ የስራ መስፈርቶችን ለማቅረብ፣ የስልጠና ፕሮግራሙ በተሳካ ሁኔታ መስጠት እንዲቻል ተገቢ የሆኑ ይዘቶችን እና አስፈላጊ የሆኑ ፋሲላቲዎችን መለየትና የመፍትሕ ሃሳብን ለማቅረብ ግድታ መግባቱን፣ አመልካች ለዚህ የተጠሪ ስራ $ 4,289,189.60 (አራት ሚላዮን ሁለት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ሺህ አንድ መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ከስልሳ ሳንቲም የአሜሪካን ዶላር) ለመክፈል መስማማቱንና ተጠሪ ደግሞ አስራ አራት አማካሪዎችን ለማሰማራትና ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ ለስምንት ወራት በቋሚነት እንዲሰሩ እና ስድስቱ ደግሞ ለሰባት ወራት እየተቀያየሩ የሚሰሩ አማካሪዎች እንዲሁም ቀሪዎቹ ደግሞ ለአራት ወራት እየተቀያየሩ የሚሰሩ አማካሪዎችን መድቦ የነበረ መሆኑን፣ በውሉ መሰረትም የአከፋፈሉ ሁኔታ ለመጀመሪያ ሶስት ወራት (ጥር፣ የካቲትና መጋቢት) ለተሰሩት ስራዎች የውሉን ዋጋ 40%፣ ለሁለተኛው ሶስት ወራት (ሚያዚያ፣ ግንቦትና ሰኔ) ለሚሰሩት ስራዎች እንዲሁ የውሉን 40%፣ ቀሪውን የውሉን 20% ደግሞ በሁለት ወራት (ሐምልና ነሐሴ) ለሚሰሩት ስራዎች እንደሚከፈል መገለጹን፣ 12% የሚሆነው የውሉ ዋጋ ደግሞ ከእያንዳንዱ ክፍያ ከመጀመሪያው ክፍያ ጀምሮ እየተቆረጠ ተይዞ እንደሚቆይ ስምምነት መደረጉና ተጠሪ ስራዎችን በትክክል አከናውኖ የስራ አፈጻጸምና በውሉ አስፈላጊ የሆኑት ተመጣጣኝ ደረሰኞችን ቢያቀርብም በውሉ አንቀፅ 11.4 መሰረት ላከፈለው የሚገባው የተያዘ ገንዘብ መኖሩን ገልፆና የውሉ ዘመን ማብቃቱን ጠቅሶ አመልካች $293,050.12 (ሁለት መቶ ዘጠና ሶስት ሺህ ሃምሳ ከአስራ ሁለት ሳንቲም የአሜሪካን ዶላር) የተያዘ ገንዘብ ለተጠሪ እንዲከፍል፣ በዚህ ገንዘብ ላይ ከነሐሴ 28 ቀን 2000 ዓ/ም ጀምሮ ተከፍሎ እስከሚያበቃ ድረስ ወለድ እንዲታሰብለትና ለክሱ የወጡት ወጪና ኪሳራዎች እንዲተኩለት ይወሰንለት ዘንድ ዳኝነት ጠይቋል።
የአሁኑ አመልካች ለተጠሪ ክስ በሰጠው መልስም በግራ ቀኙ ውሉ መኖሩን ሳይክድ ተጠሪ የሚጠበቁበትን ግድታዎችን፣ መስራት ያለበትን ስራዎችን በሙሉ በመስራት ያላሟላ መሆኑን፣ የታቀደው በስራ ላይ ይውላል ተብሎ የነበረው አዲሱ ኩባንያ በተጨባጭ ሁኔታ ላታይ እንዳልቻለና በውሉ መሰረት ስራው መጠናቀቅ በነበረባቸው የስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ያለመሰራቱን፣ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሩብ አመታት በውሉ መሰረት መጠናቀቅ የነበረበት ስራ 80% የነበረ ሁኖ በተጨባጭ የተጠናቀቀው ግን 41.5% ብቻ መሆኑን፣ በሁለተኛው ግምገማም የውሉ ዘመን ካለቀ በኋላ የተከናወነው ስራ 71.3% ብቻ መሆኑ መረጋገጡንና በአጠቃላይ የተጠሪ የስራ አፈጻጸም እንደውሉ ያልተናከናወነና አጥጋቢና ስኬታማ ያልነበረ መሆኑን ዘርዝሮ ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል። ከዚህም በተጨማሪ የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ያቀረበ ሲሆን እንደ ውሉ ባለመፈጸሙ የደረሰውን ኪሳራ ዘርዝሮ $428,918.96 (አራት መቶ ሀያ ስምንት ሺህ ዘጠኝ መቶ አሥራ ስምንት ከዘጠና ስድስት ሣንቲም የአሜሪካን ዶላር) በተጠሪ እንዲከፈለው ይወሰንለት ዘንድ ዳኝነት ጠይቋል። የአሁኑ ተጠሪም ለአመልካች የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ተገቢ ነው ያለውን መልስ ሰጥቷል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የግልግል ጉባኤውም ተጠሪ በውሉ መሰረት የገባውን ግድታ ያለመወጣቱ መረጋገጡን ገልጾ አመልካች ለተጠሪ ላከፈል ይገባ ከነበረው $4,289,189.60 ውስጥ በተሰራው ስራ መጠን $2,442,084.39 ወይም የውሉን 56.93% መክፈሉ ስራው በድጋሚ እንዲገመገም ከተደረገ በኋላ እና አመልካች ቴክኒካዊ ፐርሶኔል ክፍል የድጋፍ ደብዳቤ ከተፃፈ በኋላ $726,498.55 አመልካች ለተጠሪ እንዲከፈል መደረጉንና በግራ ቀኙ መካከል ያለውን ውል ለማቋረጥ መስማማቱ መረጋገጡን በምክንያትነት ይዞ ከዚሁ ገንዘብ ውስጥ ለመልካም ስራ አፈጻጸም የተያዘው 12% ገንዘብ ከተሰራው ስራ ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ ላለቀቅ የሚገባው እንጂ በአመልካች የሚያዝበት አግባብ የለም ሲል አመልካች ለተጠሪ $87,169.02 ከነሐሴ 09 ቀን 2000 ዓ/ም ጀምሮ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ (9%) ጋር እንዲከፍል፣ በዚሁ ገንዘብ መጠን የጠበቃ አበል 10% እንዲከፈል የወሰነ ሲሆን የአመልካችን የተከሳሽ ከሳሽነትን ክስ ግን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎታል። በግራ ቀኙ ውል የግልግል ጉባኤ በሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ መሆኑ በመገለፁ ምክንያት አቤቱታው ለዚህ ሰበር ችሎት በቀጥታ ቀርቧል።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም በግራ ቀኙ መካከል ከታሀሳስ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚነት እንዲኖረው የተደረገው ውል በሕጉ አግባብ ሳይሻሻልና ይህንኑ ተጠሪ ባላረጋገጠበት ሁኔታ የዳግም ግምገማ ውጤቱን መሰረት በማድረግ የመልካም ስራ አፈጻጸም መያዣ ገንዘብ በተሰራው ስራ መጠን ላለቀቅ ይገባል ተብሎ መወሰኑም ሆነ ተጠሪ እንደ ውሉ ግድታውን ያልፈጸመ መሆኑ ተረጋግጦ እያለ የአመልካች የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ውድቅ የተደረገው ያላግባብ ነው በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም በአመልካች መስሪያ ቤት ሰራተኞች እ.ኤ.አ መስከረም 15 ቀን 2008 በተደረገው የመልሶ ግምገማ (Re-evaluation) በግራ ቀኙ መካከል ውሉን ለመቋጨት የታለመ ስምምነት መደረጉን ያመላክታል በማለት እና በዚሁ መልሶ ግምገማ አመልካች ተፈጻሚነቱ ባበቃው ውል የነበረውን የክፍያ ይገባኛል ጥያቄ የማቅረብ መብቱን ትቷል በማለት የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለትም ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ከመደረጉም በላይ መጋቢት 11 ቀን 2004 ዓ/ም በዋለው ችሎትም የቃል ክርክር እንዲያደርጉ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ግራ ቀኙ ከታህሳስ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ከነሐሴ 28 ቀን 2000 ዓ/ም ድረስ የሚቆይ የአለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴልኮም ኩባንያ ለመፍጠር ሲባል የተለያዩ ተግባራት የሚከናወኑበትን ስምምነት ማድረጋቸውን ግራ ቀኙ የማይካካዱበት ጉዳይ መሆኑን፣ ግልግል ጉባኤውም በአመልካችና በተጠሪ መካከል በተደረገው ውል የጊዜ ገደብና በውሉ በተገለፀው መሰረት ስራው ውጤታማና ስኬታማ በሆነ መንገድ በተጠሪ ምክንያት ያልተፈጸመ መሆኑን በፍሬ ነገር ደረጃ ያረጋገጠው ጉዳይ መሆኑን፣ ተጠሪ በአመልካች ላይ ክስ ላመሰርት የቻለው ዳግም ግምገማ ተካሄዶ ስራው 71.3% መሰራቱ በአመልካች ተወካዮች ተረጋግጦ የውሉ ገንዘብ በዚሁ በተሰራው ስራ መጠን ብር $726,489.55 እንዲሆን ተደርጎ ለተጠሪ እንዲከፈል ሲደረግ የመልካም ስራ አፈፃፀም ዋስትና ገንዘብ በተሰራው ስራ ልክ መለቀቅ ሲገባው ያላግባብ የተያዘበት መሆኑን ገልጾ ይኸው ገንዘብ እንዲለቀቅለት መሆኑን፣ አመልካች የሚከራከረው ደግሞ በዳግም ግምገማ ጊዜ የቀድሞው ውል ያልተሻሻለ መሆኑንና ክፍያ እንዲፈፀም የተደረገውም በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ለማቋረጥ በማሰብ የአከፋፈሉ ሁኔታ የቀድሞውን ውል መሰረት በማድረግ ላሆን እንደሚገባ መስከረም 05 ቀን 2001 ዓ.ም.
የተፃፈው ደብዳቤ ይዘት የሚገልፅ መሆኑና በጠቅላላው የቀድሞው ውል በሕጉ አግባብ ባልተሻሻለበትና ተጠሪ ግድታውን እንደ ውሉ አልፈጸመም ተብሎ በተረጋገጠበት አግባብ አመልካች ለተጠሪ የመልካም ስራ አፈጻጸም ዋስትና ገንዘብ ላለቅ ይገባል ተብሎ መወሰኑ ስለ ውል መሻሻል የሚደነግጉትን የፍትሐብሕር ሕግ ድንጋጌዎችንና የግራ ቀኙን ውል ይዘትና በጉዳዩ ላይ የተጠየቀውን ዳኝነት እንዲሁም የማስረጃ አቀራረብና የዳኝነት አሰጣጥ ስርአትን ያልተከተለ ነው በማለት መሆኑን ነው። ተጠሪ በግልግል ዳኝነት ክሱን ሲያቀርብ የቀድሞው ውል በህጉ አግባብ ተሻሽሐል በሚል ዳኝነት ያለመጠየቁንና ውል ስለመሻሻሉ የሚያሳይ ማስረጃ አለ ብሎ የማይከራከር መሆኑን በዚህ ችሎት በተደረገው የቃል ክርክር ያረጋገጠው ጉዳይ ከመሆኑም በላይ በግልግል ጉባኤው የተደረገው የክርክር ሂደትም አመልካች ውሉ ተሻሽሐል በማለት ያቀረበው ክርክር የልለ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ተገንዘበናል። እንዲሁም ተጠሪ በውሉ መሰረት ስራውን ሙሉ በሙሉ ሰርቼአለሁ ብሎ የማይከራከርና 71.3% ብቻ መስራቱን መረጋገጡን የማይክደው ፍሬ ነገር ሲሆን በውሉ ላይ የመልካም ስራ አፈጻጸም ዋስትና ገንዘብ በተሰራው ስራ ልክ መለቀቅ ያለበት ስለመሆኑ ስምምነት ተደርጓል በማለት የማይከራከር መሆኑን ተገንዝበናል። ተጠሪ የመልካም ስራ አፈፃፀም ዋስትና ገንዘብ በተሰራው ስራ መጠን ላለቀቅ ይገባል በማለት የሚከራከረው በግራ ቀኙ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመቋጨት ዳግም ግምገማ እንዲደረግ ተደርጎ የተሰራው ስራ መጠን ተጣርቶ በዚህ አግባብ ክፍያ እንዲከፈል አመልካች በተወካዮቹ አማካኝነት ስምምነት ላይ ደርሷል በሚል ምክንያት መሆኑንም ተረድተናል። አመልካች የዳግም ግምገማው ሪፖርት ተቀባይነት ላይ ክርክር የልለውና የዚህ ሪፖርት አላማ በግራ ቀኙ መካከል የነበረውን ግንኙነት ወደፊት ቀሪ እንዲሆን ታስቦ የተከናወነ መሆኑንም የሚቀበለው ጉዳይ መሆኑን ተረድተናል። ስለሆነም ምላሽ የሚያሻው የጉዳዩ ጭብጥም አመልካችና ተጠሪ ሚያዚያ 09 ቀን 2000 (እ.ኤ.አ አፕሪል 17 ቀን 2008) ያፀደቁት የሥራ ውል ተሻሽሐል ወይንስ አልተሻሻለም? የሚለው ነው። ይህንኑ ጭብጥ ከማየታችን በፊት ግን የተጠሪ ወኪል በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ባነሷቸው ነጥቦች ላይ ምላሽ መስጠቱ ተገቢ ሁኖ ተገኝቷል።
የተጠሪ ወኪል አመልካች የሰበር አቤቱታውን በጊዜ ገደቡ ያለማቅረቡንና በግልግል ጉባኤው የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ መሆኑን ግራ ቀኙ የተስማሙት መሆኑን ገልጸው ጉዳዩ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ላታይ አይገባም በማለት ተቃውሞ አቅርበዋል። ይሁን እንጂ አመልካች የሰበር አቤቱታውን እንዲያቀርብ በሰበር ሰሚ ችሎቱ በመ/ በሕጉ አግባብ የፈቀደለት በመሆኑ የሰበር አቤቱታ ማቅረቢያ ጊዜ ማለፉን መሰረት በማድረግ የተጠሪ ወኪል ያቀረቡትን ተቃውሞ አልተቀበልነውም። እንዲሁም በአመልካችና በተጠሪ መካከል የተደረገው ስምምነት ጉባኤው የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው የሚል ቢሆንም እንኳ የሰበር ሰሚ ችሎቱን ስልጣን በስምምነት ለማስቀረት የሚቻልበት አግባብ የልለ መሆኑን ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ በቀረበው ጉዳይ ላይ በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ቤትን የሚያስገድድ የሕግ ትርጉም የሰጠበት ጉዳይ በመሆኑ ተጠሪ በዚህ ረገድ ያቀረበው ተቃውሞም ተቀባይነት ላሰጠው የሚገባ ሁኖ አልተገኘም።
ወደዋናው ጉዳይ ስንመለስም በመሰረቱ በውል አመሰራረት ሂደት ውል ተቀባይ ተብሎ የሚታወቅ ወገን ውሉን መቀበሉ በጽሁፍ፣ በልማዳዊ ምልክት ወይንም በተግባር ካላመለከተ በስተቀር መልስ ሣይሰጥ ቢቀር በግራ ቀኙ መካከል የውል ግድታ ተቋቁሟል ለማለት እንደማይቻል ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1682 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ መረዳት ይቻላል። ይህ ድንጋጌ የሚሳየው በመርህ ደረጃ ዝምታ ውልን እንደመቀበል ላቆጠር እንደማይችል ነው። ይሁን እንጂ በአንዳንድ ሁኔታዎች ዝምታ ውልን እንደመቀበል እንደሚያስቆጥር በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1683 እና 1684 ድንጋጌዎች ስር ከተመለከቱት ሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። በዚህም አግባብ አስቀድሞ በግራ ቀኙ መካከል የውል ስምምነት ባለ ጊዜ አንድ ወገን ይህንን ውል ለማደስ፣ የውሉን ዘመን ለማስረዘም፣ ለማሻሻል ወይም ከቀድሞው ውል ጋር በተዛመደ አኳኋን ተጨማሪ ውል ለማድረግ የሚያቀርበው ጥያቄ በበቂ ጊዜ ውስጥ በልላው ተዋዋይ ወገን አሉታዊ ምላሽ ካልተሰጠበት ዝምታው መቀበልን እንደሚያስከትል በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1684 ስር ተደንግጓል።
የፍ/ሕ/ቁጥር 1722 ድንጋጌ ሲታይ ደግሞ ቀድሞ የነበረ ውል በሚሻሻልበት ጊዜ አስቀድሞ በተደረገው የአፃፃፍ ሥርዓት መከናወን እንዳለበት በግልፅና አስገዳጅነት ባለው መልኩ ሰፍሯል።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም ግራ ቀኙ ሚያዚያ 09 ቀን 2000 ዓ.ም ባደረጉት የሥራ ውል ከታህሳስ 25 ቀን 2000 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ከነሐሴ 28 ቀን 2000 ዓ/ም ድረስ የሚቆይ አለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴልኮም ኩባንያ ለመፍጠር ሲባል የተለያዩ ተግባራት የሚከናወኑበትን ስምምነት ማድረጋቸው በግራ ቀኙ የታመነ ቢሆንም በውሉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብና የአፈጻጸም ጥራት ስራው ያልተከናወነ መሆኑን ተጠሪ የማይክደው፣ እንዲሁም የግልግል ጉባኤውም በፍሬ ነገር ደረጃ ያረጋገጠው ነጥብ ነው። ተጠሪ የክፍያ ጥያቄውን ያቀረበውም የቀድሞው ውል በሕጉ አግባብ ተሻሽሐል በሚል ምክንያት ስላለመሆኑ የክርክሩ ሂደት የሚያረጋግጠው ነጥብ ሲሆን ተጠሪው ለጥያቄው መሰረት ያደረገው መስከረም 5 ቀን 2001 ዓ.ም. በተደረገው የመልሶ ግምገማ አመልካች ለተጠሪ ለተሰሩ ስራዎች ክፍያ እንዲፈፀም ስምምነት አድርጓል በሚል ምክንያት ነው። ይሁን እንጂ መስከረም 5 ቀን 2001 ዓ/ም በአመልካች መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ተቀባይነት አግኝቷል የተባለው የመልሶ ግምገማ ሪፖርት ውጤት ተጠሪ ቀድሞ በተደረገው የውልና እና የጥራት ደረጃ 71.3% (ሰባ አንድ ነጥብ ሶስት ከመቶ) ብቻ የሰራ መሆኑ መረጋገጡን አመልካች በማመን አሁን አጥብቆ የሚከራከረው ይህ የመልሶ ግምገማ ሪፖርት በቀድሞው ውል ስለ ክፍያ አፈፃጸም የተመለከተውን ልሎች የተዋዋይ ወገኖችን መብትና ግድታ ቀሪ ያደረገ ባለመሆኑ ለመልካም ስራ አፈጻጸም ዋስትና የተያዘው ገንዘብ ስለመሰራቱ ከተረጋገጠው የስራ መጠን ጋር ተዛምዶ ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ አመልካች ለተጠሪ ላለቅ የሚገባበት ከሕግ ወይም ከውል የመነጨ ግድታ የለም በማለት ነው። ይህ ችሎትም ጉዳዩን እንደተመለከተው ተጠሪ የቀድሞ ውል የተሻሻለ ስለመሆኑ መሰረት አድርጎ ክስና ክርክር ያላቀረበ እና በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1722 መሰረትም የተሻሸለ ውል ስለመኖሩ የሚያረጋግጥ ማስረጃ በማቅረብ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2001 መሰረት መብቱን ያስረዳበት የክርክር ሂደት የለም። ተጠሪ የሚጠይቀውን ክፍያ ከውል ወይም ከሕግ የመነጨ ስለመሆኑ የማስረዳት ግድታ ያለበት መሆኑ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2001 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በዚህ አኳኋን በተጠሪ በኩል የቀረበ የውል ማሻሻል ጉዳይ በልለበት ሁኔታ አመልካች የመስከረም 5 ቀን 2001 ዓ/ም የመልሶ ግምገማ ውጤት በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1684 መሰረት በዝምታ ተቀብሐል ለማለት የሚቻልበት የሕግ አግባብም ላኖር አይችልም። ይልቁንም የአመልካች መስሪያ ቤት ኃላፊ የመልሶ ግምገማ ሪፖርቱን ከተመለከቱ በኋላ ተጠሪ አለኝ የሚለውን ክፍያ በቀድሞው ውል መሰረት እንዲከናወን በሚያስገነዘብ መልኩ ጠቅሰው በመልሶ ግምገማ ሪፖርቱ ላይ ማዘዛቸውን አመልካች በአቀረበው የሰነድ ማስረጃ ይዘት የተረጋገጠ ስለመሆኑ በጉባኤው ላይ የተደረገው የክርክሩ ሂደት በግልጽ ያሳያል። በመሆኑም የመስከረም 5 ቀን 2001 ዓ.ም.
የመልሶ ግምገማ ሪፖርት በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1722 መሰረት የቀድሞው ውል የተሻሸለበት መሆኑን ባልተረጋገጠበትና በሪፖርቱ ላይ የክፍያው አፈጻጸም በቀድሞው ውል ከተገለፀው ውጪ ስለመሆኑ የሚያሳይ ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ በቀድሞው ውል አንቀፅ 11.4 ድንጋጌ መሰረት ተጠሪ ከሚገባው ክፍያ በተሰራው ስራ መጠን መሰረት 12% እንደሚለቀቅለት በግልጽ ባልተቀመጠበት ሁኔታ ግልግል ጉባኤው የመልካም ስራ አፈጻጸም ቦንድ በመልሶ ግምገማ መሰረት በተረጋገጠው 71.3% ስልት መሰረት እንዲለቀቅ መወሰኑ የውል ወይም የሕግ መሰረት በልለበት ሁኔታ ሁኖ ተገኝቷል። አንድ የግልግል ጉባኤ ጉዳዩን በማየት የዳኝነት መፍትሕ ላሰጥ የሚችለው ደግሞ ተከራካሪ ወገኖች በተስማሙበትና በሚጸና ወይም ዋጋ ያለውን ግድታ በመከተል ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 356(ሀ) ድንጋጌ አቀራረፅ፣ ይዘትና መንፈስ ያስገነዝባል። ይህ ድንጋጌ የግልግል ወይም የቤተዘመድ ሽምግልና ዳኞች ተከራካሪዎቹ ወገኖች የተስማሙበት ነው በማለት በማይጸና ወይም ዋጋ የልለውን ግድታ በመከተል ወይም ባለጉዳዮቹ ያላቀረቡትንና ያልተከራከሩበትን ጉዳይ መሰረት በማድረግ ብይን የሰጡ መሆኑ ከተረጋገጠ ጉዳዩ ይግባኝ የልለው መሆኑን ቢስማሙም እንኳን ይግባኝ ለማቅረብ መሰረት ከሚሆኑ ነገሮች መካከል እንደሆኑ ጠቅሷል።በመሆኑም የግልግል ጉባኤው የመልካም ስራ አፈጻጸምን በተመለከተ ተጠሪ ስለመስራቱ በመልሶ ግምገማ በተረጋገጠው መጠን ስልት መሰረት ታስቦ ላመስለት ይገባል በማለት የሰጠው የውሳኔ ክፍል ከመልሶ ግምገማ በኋላ የቀድሞ ውል በሕጉ አግባብ የተሻሸለና ዋጋ ያለው ስምምነት ስለመኖሩ ባልተረጋጠበት ሁኔታ በመሆኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሁኖ አግኝተናል።
ልላው አመልካች አጥብቆ የሚከራከርበት ነጥብ የተከሳሽ ከሳሽነትን ክስ መሰረት ያደረገ የጉዳት ካሳ ክፍያ ጥያቄ ነው። በክርክሩ ሂደት አመልካች ከተጠሪ ጋር ያደረገው ውል በውሉ በተመለከተው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያለመከናወኑና የተሰራው ስራም በውሉ የተገለፀውን ያህል መጠን ያለመሆኑ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። አመልካች የጉዳት ካሳ ጥያቄን መሰረት ያደረገውም ስራው በውሉ በተመለከተው የጊዜ ገደብ ያለመሰራቱና በውሉ አንቀፅ 17 የተመለከተውን ድንጋጌ መሰረት በማድረግ ነው። በእርግጥ በውሉ አንቀፅ 17 ስር ከተዋዋይ ወገኖች አንዱ በውሉ በተመለከተው የጊዜ ገደብ ውስጥ በሙሉ ወይም በከፊል ግድታውን ካልተወጣ ልላው ወገን የጉዳት ካሳ የመጠየቅ መብት ያለው መሆኑንና ላጠየቅ የሚገባውን የጉዳት መጠን ምን ያህል እንደሆነ ተደንግጓል። ይሁን እንጂ የመልካም ሥራ አፈጻጸም (ቦንድ) ሰነድ የውል አፈፃፀምን ለማረጋገጥ የሚሰጥ የዋስትና ሰነድ መሆኑን፣ ይህም በባለገንዘብ እና በባለ እዳ መካከል የተደረገን ውል አፈፃፀም ለመጠበቅ የሚገባ ግድታ መሆኑ ከሰነዱ አይነተኛ ዓላማ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። የመልካም ስራ አፈፃፀም ቦንድ መሰረታዊ አላማ ስራው በውሉ መሰረት ስለመሰራቱ ለማረጋገጥ የሚገባ ግድታ መሆኑ እሙን ነው። በአመልካችና በተጠሪ መካከል ከታህሳስ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. ጀምሮ የጸናው ውል በአንቀጽ 11.4 ስር ከመጀመሪያ ክፍያ ጀምሮ እየተቀነሰ 12% የሚሆነው የውሉ ዋጋ እንዲያዝ የሚደረግ መሆኑንና የውሉ ዘመን ካለቀ ከ15 ቀናት በኋላ ስራዎቹ በስኬታማ ሁኔታ መጠናቀቃቸውን በሃርድ ኮፒ እና በሶፍት ኮፒ ከተረጋገጠ በኋላ የሚለቀቅ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። በዚሁ በውሉ ድጋንጌ ውስጥ "…..ስራዎቹ በስኬታማ ሁኔታ መጠናቀቃቸው----" የሚለው ሐረግ ሲታይ የመልካም ስራ አፈጻጸም ቦንድ ስራዎቹ በስኬታማ ሁኔታ ባይጠናቀቁ የሚደርሰውን ጉዳት ለማካካስ ጭምር ታስቦ የተገባ ግድታ መሆኑን ያሳያል። አመልካች ተጠሪ በተከሳሽ ከሳሽነት በውሉ አንቀጽ 17 መሰረት የጠየቀው የጉዳት ካሳ መጠን በውሉ አግባብ ሳይሰራ በዘገየበት ጊዜና ስራውን ሰርቶ ለማጠናቀቅ በተጨማሪነት አስፈላጊ የሆነውን ጊዜ መሰረት በማድረግ ተሰልቶና በአመልካች እጅ ይገኛል ከተባለው የመልካም ስራ አፈጻጸም ገንዘብ መጠን የበለጠ ስለመሆኑ በፍሬ ነገር የተረጋገጠ ጉዳይ አይደለም። ይልቁንም አመልካች ከተጠሪ ጋር የነበረውን ግንኙነት መሰረት በማድረግ የተሰራውን ስራ መልሶ በመገምገም በተሰራው ስራና ከታህሳስ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. ጀምሮ በጸናው ውል መሰረት ክፍያ እንዲፈጸም የተደረገ መሆኑን የክርክሩ ሂደት በግልጽ ያሳያል።
እንዲህ ከሆነ ስራውን በጊዜ ለማጠናቀቅ ባለመቻሉና ስራውን ወደፊት ሰርቶ ለመጨረስ የሚያስፈልገው ጊዜ ላይ ካሳ ለማስከፈል አመልካች ሃሳብ የነበረው ስለመሆኑ የሚያሳይ ማስረጃ የለም። አመልካች ከተጠሪ ጋር የነበረውን ግንኙነት መሰረት አድርጎ በተሰራው የስራ መጠን ለተጠሪ ክፍያ በመፈጸም የውሉ ማጠናቀቂያ ጊዜ ከሆነው ከነሐሴ 2000 በኋላ ስራው ለዘገየበትና ስራውን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ለሚያስፈልገው ተጨማሪ ጊዜ ያልተሰራውን ስራ 0.1% ያህል የክፍያ መጠን ለእያንዳንዱ ቀን ወይም የውሉን ጠቅላላ ዋጋ 10% በጠቅላላው የጉዳት ካሳ ከተጠሪ የሚጠይቅበት አግባብ ስለመኖሩ በማስረጃ ያላስደገፈው የክርክር ነጥብ ነው። ይልቁንም አመልካች ስራው በውሉ በተቀመጠው ጊዜና ጥራት ያለመጠናቀቁን እያወቀ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ቀሪ እንዲሆን መስከረም 05 ቀን 2001 ዓ.ም. በተደረገው የመልሶ ግምገማ ሪፖርት መነሻነት ስምምነት አድርጓል። ይህ ስምምነት የሚያሳየው ውሉ በጊዜው ባይጠናቀቅም በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት አቋርጧል። የተቋረጠ ውል ደግሞ በተዋዋይ ወገኖች መካከል እስከተቋረጠ ድረስ እንጂ ውሉ ከተቋረጠ በኋላ ባለው ጊዜ ወይም ወደፊት ውጤት የሚያስከትልበት አግባብ የልለ መሆኑን ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1819(2) ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በመሆኑም የአመልካች የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ውድቅ የሆነው የመስከረም 05 ቀን 2001 ዓ.ም. የመልሶ ግምገማን ሪፖርት አመልካች በመቀበል ስራውን ለወደፊት ለመስራት የሚያስፈልጉ ጊዜያትን ቀሪ በማድረጉ ሁኖ ስለአገኘነው በዚህ ረገድ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት አልተቻለም።
ው ሣ ኔ
የግልግል ጉባኤው በጉዳዩ ላይ ነሐሴ 06 ቀን 2002 ዓ.ም. የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 353 መሰረት ተሻሽሐል።
በአመልካችና በተጠሪ መካከል መስከረም 05 ቀን 2001 ዓ.ም. ተደረገ የተባለው የመልሶ ግምገማ ሪፖርት ስምምነት በመካከላቸው ታህሳስ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. የተደረውን ውል ያላሻሻለ በመሆኑ አመልካች ለተጠሪ በመልሶ ግምገማ መሰረት ስለመሰራቱ በተረጋገጠው 71.3% ስራ መጠን መሰረት የመልካም ስራ አፈጻጸም ቦንድ ለተጠሪ የሚለቅበት አግባብ የለም ብለናል። የአመልካች የተከሳሽ ከሳሽነት ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ታህሳስ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. ከተደረገው ውል አንቀፅ 11.4፣ 17 ይዘትና መንፈስ ከመስከረም 5 2001 ዓ.ም. የመልሶ ግምገማ ሪፖርትና ውጤቱ ጋር ባገናዘበ መልኩ ነው ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.