No summary available.
ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- 1ኛ አቶ ሽፈራው ደጀኔ ቀረቡ 2ኛ ወ/ሮ ፀሐይ ተስፋዬ በወኪልና 1ኛ አመልካች ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ሲሳይ አበቡ ቀረቡ መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ይህ የሰበር ጉዳይ ቤትን በሚመለከት ግራ ቀኙ ያደረጉት የቤት ሽያጭ የሰነድ ውል ቤቱ በምን ያህል ዋጋ ተሸጧል? የሚለውን አከራካሪ ነጥብ በማስረዳት ረገድ ይኸው የጽሑፍ ውል ያለውን የማስረጃ ተቀባይነት ከግራ ቀኙ ክርክር ጋር አገናዝቦ ተገቢውን ትርጉም ለመስጠት ሲባል የቀረበ ነው።
የጉዳዩም መነሻ የሆነው የአሁን ተጠሪ በአመልካቾች ላይ ያቀረበው ክስ ሲሆን የክሱም ይዘት ተከሳሾች እና እኔ ሐምል 17 ቀን 2003 ዓ.ም ባደረግነው የቤት ሽያጭ ውል በኡኬ ከተማ በአሁን 1ኛ አመልካች ስም ተመዝግቦ የሚገኘውን ቤት በብር 20,000.00 /ሃያ ሺህ ብር/ ሸጠውልኛል። ነገር ግን በውሉ መሰረት የሽያጭ ዋጋውን ተቀብለው ከወሰዱ በኋላ የተሸጠውን ቤት እና የቤቱን ሰነድ ለማስረከብ እምቢተኛ ሆነዋል። ስለሆነም እንደ ግድታቸው እንዲፈፅሙ ይወሰንልኝ የሚል ነው።
የአሁን አመልካችም በተከሳሸነታቸው የሰጡት መልስ ሐምል 17 ቀን 2003 ዓ.ም ባደረግነው የቤት ሽያጭ ውል አድራሻው የተገለፀውን ቤት በብር 40,000.00 /አርባ ሺህ ብር/ ሸጠናል።
በዚህ የሽያጭ ሰነድ ላይም ገዥው የቤቱን ዋጋ በ10 ቀን ውስጥ ለመከፈል ግድታ ገብቷል።
ይሁን እንጂ የግዥውን ዋጋ በቀብድም ሆነ በሙሉ የከፈለው ክፍያ የለም። ስለሆነም ገዥው እንደ ግድታቸው የቤቱን ዋጋ በጊዜው ባለመከፈሉ የተነሳ ቤቱን ለመረከብና ስመሀብቱ እንዲዛወር ለማድረግ ያልተቻለ መሆኑ ታውቆ ከወጪና ኪሣራ ጋር እንድንሰናበት ይደረግልኝ በማለት ተከራክረዋል።
ክሱ የቀረበለት በምስራቅ ወለጋ መስ/ዞን የጉቶ ጊዳ ወረዳ ፍ/ቤትም አከራካሪው ቤት የተሸጠው በስንት ዋጋ ነው የሚለውን ነጥብ ለመለየት የግራ ቀኙን የሰው ማስረጃዎች ከሰማ በኃላ በመ/ ጥር 17 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት በቀን 17/11/2003 ዓ.ም ግራ ቀኙ የቤት ሽያጭ ውል ማድረጋቸውን አምነው የቤቱን ዋጋ በመክፈልና አለመክፈል እንዲሁም በተሸጠው የቤት ዋጋ ላይ ተካክደዋል። ሆኖም በቤቱ የሽያጭ ውል የቤቱ ዋጋ ብር 20,000.00 /ሃያ ሺህ ብር/ መሆኑንና ይህም ዋጋ መከፈሉን በውሉ ላይ በግልፅ ተመልክቷል። በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2005 (1) እንደተደነገገው በፅሑፍ ማሰረጃ ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ ቃልና ቀን በፈረሙት ሰዎች መካከል እምነት የሚሰጠው ማስረጃ ነው። በዚሁ የፅሑፍ ማስረጃ ላይ የሚገኘውን ቃል መቃወም የሚቻለው በመሃላ ቃል ብቻ እንጂ በሰው የምስክርነት ቃል ማስተባበል አይቻልም። ስለሆነም ሻጮች ግድታቸውን ስላልተወጡ ቤቱን ለከሳሽ እንዲለቁ እና አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን በማቅረብ ድጋፍ ያድርጉ፤ እንደ ግድታቸው ባለመፈፀማቸውም ገደብ ብር 10,00.00 /አስር ሺህ ብር/ ይክፈሉ በማለት ወስኗል።
ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የመቀጫ ገንዘቡን ከማንሳቱ በቀር በተመሳሳይ ምክንያት የሥር ፍ/ቤቱን ውሳኔ አፅንቶታል።
የምስራቅ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በይግባኝ በሰጠው ውሳኔ የአሁን አመልካች ቅር ተሰኝተው ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 337 መሰረት ተቀባይነት አላገኘም።
በዚህ ከላይ በተገለፀው መሰረት በየደረጃው የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት አይደለም በማለት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዳኝነት በመሰጠቱ ይህ የሰበር ጉዳይ ለዚህ ለፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ላቀርብ ችሐል።
ግራ ቀኙ በሰበር ደረጃ ያቀረቡት የፅሑፍ ክርክር በሥር ፍ/ቤት አንስተው የተከራከሩበትን የሚያብራራ እና የሚያከራክር እንጂ በይዘቱ የተለየ አየደለም።
እኛም ጉዳዩን እንደሚከተለው መርምረናል። እንደመረመርነውም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 2005 እንደተደነገገው በፅሑፍ ሰነዱ ላይ ስለሚገኘው የስምምነት ቃል እንዲሁም ስለ ተፃፈው ቀን በተፈራራሚዎቹ መካከል ሙሉ እምነት የሚጣልበት በቂ ማስረጃ ነው። ብሎ ላደመደም የሚችለው እንደውለታው ዓይነት የጽሑፍ ውል አደራረግን ሥርዓት አስመልክቶ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1678 (ሐ)፣ 1719(2) የተመለከተውን በህግ ፊት ላፀና የሚችል ውል ለመያዝ አስፈላጊ የሆነውን የውል አደራረግ ሥርዓት አሟልቶ የያዘ ስለመሆኑ ላታይ የሚገባው ጉዳይ ነው።
No topics extracted.
በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1678(ሐ) እና 1719 (2) መሰረት የውሉ አደራረግ ሥርዓት በተለየ አኳኋን እንዲደረግ በህግ ተለይቶ ከተመለከተው ድንጋጌ አንዱ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1723 (1) የተመለከተው ይገኝበታል። በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ያለን የባለቤትነት መብት በሽያጭ ለማስተላለፍ ሲባል የሚደረገው የውል ስምምነት በፅሑፍ ሆኖ ውል ለማዋዋል ሥልጣን ባለው አካል ፊት መደረግ ያለበት ስለመሆኑ ተደንግጓል። በዚህ አኳኋን ውል ለማዋዋል ሥልጣን ባለው አካል ፊት መደረግ አለበት የሚለውም የህግ ማሟያ ክፍል አስፈላጊነት የሽያጭ ውል ተደርጓል ወይስ አልተደረገም? ተደርጎ ከሆነስ መቼ በምን ያህል ዋጋ፣ የትኛው ንብረት ወዘተ የሚለውን አስመልክቶ አላስፈላጊ የሆኑ ሙግቶችን ለማስቀረት ታስቦ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚፈፀሙ የባለቤትነትን መብት የሚያስተላልፉ ውሎች ውሉ ስለመኖሩ እስካልታመነ ድረስ በአዋዋይ ፊት መደረግ ይኖርባቸዋል።
በዚህ በተያዘዉም ጉዳይ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2005 (1) እንደተመለከተው በፅሑፍ ሰነድ ላይ ስለሚገኘው የስምምነት ቃል እንዲሁም በላዩ ላይ ስለተፃፈው ቀን በተፈራራሚዎቹ መካከል ሙሉ እምነት የሚጣልበት በቂ ማስረጃ ነው የሚለው ድንጋጌ ከላይ በተገለፀው አኳኋን ከፍ/ብ/ሕ/ቁ 1678(ሐ)፣ 1719(2) እና 1723 (1) ድንጋጌዎች ጋር ተገናዝቦ ሲታይ ለማናቸውም የፅሑፍ ውል ስምምነት ተፈፃሚ ላሆን የሚችል አይደለም።
ይህ አከራካሪ የሆነው ሽያጭ ውል የተደረገው የማይንቀሳቀስ በሆነው ንብረት በቤቱ ላይ ነው።
ውሉ የተደረገውም በፍ/ሕ/ቁ 1723 የተመለከተውን ድንጋጌ አሟልቶ አይደለም። ውል ለማዋዋል ሥልጣን ባለው አካል ፊት ተደርጎ ቢሆን ኖሮ የቤቱን ዋጋ እና ይህንኑ ዋጋ ተቀብለዋል አልተቀበሉም የሚለውን አስመልክቶ በፅሑፍ ከሰፈረው ቃል ውጭ የመቅረብ ማናቸውም ክርክር በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2005(1) እንደተደነገገው ተቀባይነት ያለው ክርክር አይደለም፣ ከፅሑፍ ሰነዱ በቀር የሚቀርብ ማናቸውም ማስረጃ የሰውም ምስክሮች ቃል ተቀባይነት የለውም በማለት መደምደም ባልተቻለ ነበር።
ስለሆነም በህግ ፊት ላፀና በሚችል ውል ለመመደብ ቋሚ ማሟያ ሆኖ የተያዘውን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1678 (ሐ)፣ 1719(2) እና 1723 የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ተከትሎ የተደረገ ስምምነት ባለመሆኑ ይህ ዓይነት ስምምነት በህግ ፊት ዋጋ ያለው ሆኖ፤ ላፀና የሚችል ስምምነት ነው ብሎ ውጤት ለመስጠት የሚቻል ባለመሆኑ የአሁን ተጠሪ ይህን በህግ ፊት ላፀና የማይችለውን ውል መነሻ በማድረግ እንደ ውሉ ይፈፀምልኝ በማለት በአመልካቾች ላይ ክስ ለማቅረብ የሚቻል ሆኖ አላገኘነውም ።
ሆኖም የአሁን አመልካቾች ይህንኑ ቤት በብር 40,000.00 /አርባ ሺህ ብር/ ሸጠናል በማለት በፍሬ ነገር ረገድ ገልፀው የተከራከሩ ከመሆኑ እና የሽያጭ ዋጋም አልተቀበልንም በማለት የተከራከሩ በመሆኑ የአሁን ተጠሪ በዚሁ አመልካቾች በጠቀሱት የሽያጭ ዋጋውን ከፍለው ቤቱን ለመረከብ እና አስፈላጊ ሰነዶችን ለመጠየቅ ከፈለጉ ግን ይህ ውሳኔ ይህንኑ መብቱን ቀሪ ላያደርግ የሚችል አይደለም። ስለሆነም በዚህ ሁሉ ምክንያት በግራ ቀኙ መካከል የተደረገው ሽያጭ ውል የማይንቀሳቀስ የሆነውን ቤትን አስመልክቶ የተደረገ እንደመሆኑ መጠን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2005 (1) የተመለከተው ድንጋጌ አፈፃፀም ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር አገናዝቦ ሳይመለከት በዚህ በውል አዋዋይ ፊት ባልተደረገ የቤት ሽያጭ ውል ላይ የሰፈሩት ማናቸውም የውል ቃሎች ሁሉ ያለቅድመ ሁኔታ እንዳሉ የሚታመኑ ናቸው፤
በማናቸውም ዓይነት የሰው ምስክርነት ቃል ማስተካከል አይቻልም በሚል የሰጠው ትርጉም መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ተገኝቷል።
በምስራቅ ወለጋ ዞን መስተዳደር የጎቶ ጊዳ ወረዳ ፍ/ቤት በመ/ በቀን 17/5/04 የሰጠው ውሳኔ የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ በቀን 28/06/2004 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት በፋ. በቀን 11/07/2004 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝና የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በፋ. በቀን 18/7/2004 የሰጠው ትዕዛዝ ሁሉ ተሻሽሐል።
ተጠሪ ክርክር ያስነሳው ቤት ውል ለማዋዋል ሥልጣን ባለው አካል ፊት ያልተደረገን የቤት ሽያጭ ውል መሰረት አድርጎ ያቀረበው የቤት ክርክር ጥያቄ ተቀባይነት ያለው አይደለም፤
ሆኖም ሻጮች ባመኑት ዋጋ መሰረት የሽያጭ ዋጋውን የመክፈል ግድታ በእራሱ በኩል ከተወጣ ክርክር ያስነሳውን ቤት እና በዚህ ቤት ላይ ያለን የባለቤትነት መብት ለማስተላለፍ አስፈላጊ ከሆኑት ሰነዶች ጋር ያለውን የመረከብ መብት ይህ ውሳኔ አያግደውም ብለናል።
በሥር ፍ/ቤቶችም ሆነ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ግራ ቀኙ ያደረጉት ክርክር ላስከትለው ማናቸውም ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
የመስማሚያ ሀሳብ እኔ በሶስተኛው ተራ ቁጥር የተሰየምኩት ዳኛ አብላጫው ድምፅ በደረሰበት መደምደሚያ የምስማማ ሲሆን አብላጫው ድምፅ የፍታብሕር ህግ ቁጥር 1723 (1) እና የፍታብሕር ህግ ቁጥር 2005ን በማጣመር በሰጠው ትርጉም አልተስማማሁም። በእኔ እምነት የአመልካቾችን የትምህርት ሁኔታ በማጣራት የፍታብሕር ህግ ቁጥር 1728 ንዑስ አንቀፅ 3ን መሰረት በማድረግ ጉዳዩን መወሰን የተሻለ ነው የሚል ሀሳብ አለኝ።