No summary available.
ታህሣሥ 30 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል አላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አሕመድ አመልካች፡- ዲ.ኤች ገዳ ብርድ ልብስ ፋብሪካ ኃ.የተ.የግ. ማሕበር ነ/ፈጅ አቶ ስንታየሁ ጌታቸው ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሪት ቅድስት ጌታቸው ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳይ የስራ ክርክር ስሆን የአሁኗ ተጠሪ በስር ፍ/ቤት ከሣሽ የአሁኑ አመልካች ደግሞ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል። የክሱም ይዘት ከሳሽ በተከሳሽ ድርጅት ተቀጥራ በማገልገል ላይ እያለች ተከሣሸ ድርጅት ሕጋዊነት የልለውን መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በማድረግ ከሣሽ የስራ ውል ወዳልፈፀመችበት ዲ.ኤች ገዳ ንግድና ኢንዱስትሪ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ነቀምቴ ቅርንጫፍ እንዳዛወራት እርሷም ዝውውሩን በመቃወም ክስ አቅርባ እያለ በተዛወርሽበት ቦታ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በስራ ላይ አልተገኘሽም በሚል ምክንያት ተከሳሽ የስራ ውሐን አላግባብ እንዳቋረጠባት የሚገልጽ ሆኖ ስንብቱ ሕገወጥ ነው ተብሎ ከስንብት ጋር የተያያዙ ክፍያዎች እንዲፈፀሙ እንዲወሰንላት ዳኝነት የተጠየቀበት ነው።
ተከሣሽ በበኩሉ የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 1ዐ.2 በሚፈቅደው መሰረት ከሳሽ ወደ ነቀምቴ ቅርንጫፍ እንድትዛወር የተደረገ ቢሆንም ዝውውሩን ተቀብላ በስራ ገበታዋ ላይ ባለመገኘቷ እንድትሰናበት የተደረገው በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1)(ለ) መሰረት በአግባቡ መሆኑን እና የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ የስራ ውሉን ለማቋረጥ በቅ ምክንያት ተደርጐ የሚወሰድ ስለመሆኑ የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ቀደም ሲል በመ.ቁ.37778 በ04/03/01 በትርጉም አስገዳጅነት ያለው ውሳኔ የሰጠበት መሆኑን በመግለጽ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ተከራክሯል።
ክሱ የቀረበለት የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤትም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ አሰሪ አንድን ሰራተኛ ጥቅሙን ሳያጓድል ከአንድ የስራ መደብ ወደ ልላ የስራ መደብ አዛውሮ ማሰራት እንድሚችል በአዋጅ ቁጥር 377/96 በአንቀጽ 13(2) እና (7) የተመለከተ መሆኑን ሰራተኛውን ከአንድ እህት ኩባንያ ወደ ልላ እህት ኩባንያ አዛውሮ ማሰራት እንደሚቻል በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ በአንቀጽ 1ዐ.2 የተመለከተ መሆኑን በዝርዝር ገልጾ ክሱን ውድቅ በማድረግ ተከሣሽ የ14 ቀን የዓመት ፈቃድ በገንዘብ ለውጦ እንዲከፍልና የስራ ልምድ ማስረጃ እንዲሰጥ ውሳኔ ሰጥቷል።
በአሁኗ ተጠሪ የቀረበለትን ይግባኝ የተመለከተው የፍ/ከ/ፍ/ቤት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ተከሳሽ ድርጅት በሰበር ውሳኔውም መሰረት ቢሆን አንድን ሰራተኛ ማዛወር የሚችለው የራሱ ቅርንጫፍ ወደሆነ ልላ የስራ ቦታ እንጂ በእህት ኩባንያ ስም ራሱን የቻለ ሕጋዊ ሰውነት ወዳለው ልላ ማሕበር ባለመሆኑ ዝውውሩም ሆነ ዝውውሩን ተከተሎ የተወሰደው የስንብት እርምጃ አግባብነት የለውም በማለት የሥር ፍ/ቤትን ውስኔ ሽሮ ከስንብት ጋር የተያያዙ ክፍያዎች እንዲፈፀሙ ውስኔ ሰጥቷል።
አመልካች የሰበር አቤቱታ የቀረበው የይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው በማለት ሲሆን በከፍተኛ ፍ/ቤት የተሰጠውን ውሳኔ አግባብነት አመልካች ከሰራተኞች ጋር ካቋቋመው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 10.2 አንፃር ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሑፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።
የጉዳዩ አመጣጥና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም የአሁኑ አመልካች የወሰደው የዝውውርም ሆነ የስንብት እርምጃ እግባብነት የልለው በመሆኑ የስንብትና ተያያዥ ክፍያዎችን ለተጠሪ ላፈጽም ይገባል በማለት የፍ/ከ/ፍ/ቤት የስር ፍ/ቤት ውሳኔን በመሻር የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት መሆን አለመሆኑን መርምረናል።
በዚህም መሰረት አመልካች በሰበር ደረጃ አጥብቆ የሚከራከረው ተጠሪዋ ተዛውራበት የነበረው የነቀምቴ የሽያጭ ማዕከል ለስራው አመራር አመቺነት ሲባል ብቻ የአመልካች እህት ኩባንያ በሆነው ድ.ኤች ገዳ ንግድና ኢንዱስትሪ ኃ.የተ.የግ፤ ማህበር ስር እንዲተዳደር የተደረገ ቢሆንም በተለይ ከብርድልብስ ሽያጭ ጋር ተያይዞ የአመልካች ቅርንጫፍ ወይም የስራ ቦታ እንጂ የእህት ኩባንያው ቅርንጫፍ ወይም የስራ ቦታ ባለመሆኑ አመልካች ተጠሪዋን ያዛወረው ወደ እህት ኩባንያ እንደሆነ አድርጐ ፍ/ከ/ፍ/ቤት የደረሰበት ድምዳሜ ተገቢነት የለውም በማለት መሆኑን ተገንዝበናል። በመሰረቱ ፍሬ ነገርን በማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው የስር የመጀመሪያ ደረጃ እና ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቶች የክርክሩን ፍሬ ነገር በማጣራትና የቀረበላቸውን የጽሑፍ ማስረጃ በመመዘን አመልካች ተጠሪዋን ያዛወረበት የነቀምቴ የሽያጭ ማዕከል የራሱ ቅርንጫፍ ወይም የስራ ቦታ ሳይሆን የእህት ኩባንያው ቅርንጫፍ ወይም የስራ ቦታ እንደሆነ በተመሳሳይ ሁኔታ ማረጋገጣቸውን የመዝገቡ ግልባጭ ያስረዳል። ለዚህ ሰበር ችሎት በሕግ የተሰጠው ስልጣን በስር ፍ/ቤቶች የተጣራውን ፍሬ ነገር መሰረት በማድረግ አቤቱታ በቀረበበት ውሳኔ ላይ የተፈፀመ መሰረታዊ የሕግ ስህተት መኖር አለመኖሩን መርምሮ ውሳኔ ከመስጠት ውጪ ፍሬ ነገር በማጣራትና በማስረጃ ምዘና ረገድ የስር ፍ/ቤቶች የደረሱበትን ድምዳሜ ተገቢ መሆን አለመሆኑን ለመመርመር የሚያስችለው አለመሆኑን ከኢ.ፍ.ድ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3)(ሀ) እና ከአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል።
አመልካች ተጠሪዋን ያዛወረው ወደ እህት ኩባንያው መሆኑ ከተረጋገጠ ደግሞ ቀጥሎ የሚነሣው ጥያቄ አመልካች የዚህ ዓይነቱን ዝውውር ለማድረግ የሚያስችል መብት አለው ወይስ የለውም? የሚል ነው። በመሰረቱ ተጠሪ የቅጥር ውል ያቋቋመችው ከአመልካች ጋር ብቻ መሆኑ በአመልካች ያልተካደ ሲሆን የአመልካች እህት ኩባንያ ወደሆነ ልላ ማሕበር ጭምር ተዛውራ ለመስራት በስራ ውሉ ወይም በልላ ሰነድ በግሐ ወይም በጋራ የሰጠችው ስምምነት ወይም የገባችው ግድታ ስለመኖሩ አመልካች በስር ፍ/ቤቶችም ሆነ በሰበር ደረጃ የቀረበው ክርክር አለመኖሩን ተገንዝበናል። በዚህ ረገድ ይደግፈኛል በማለት ጠቅሶ የሚከራከርበት የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ቀደም ሲል በመ.ቁ. 37778 የሰጠው ውሳኔ ከፍተኛ ፍ/ቤት እንደገለፀው ወደ አሰሪው ድርጅት ቅርንጫፍ ወይም የስራ ቦታ የሚደረግ ዝውውርን እንጂ ወደ እህት ኩባንያ የሚደረግ የሰራተኛ ዝዉውርን የሚመለከት ባለመሆኑ በዚህ መዝገብ ለተያዘው ጉዳይ አግባብነት ያለው አይደለም።
ሲጠቃለል ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ለማለት የሚያስችል ሁኔታ ስላልተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
የፍ/ከ/ፍ/ቤት በመ/ቁ. 116426 በ14/12/2004 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ ፀንቷል
በዚህ መዝገብ ተሰጥቶ የነበረው የአፈፃፀም እግድ ተነስቷል።
የውሳኔው ቅጂ ይላክ። ክርክሩ ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል። ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.