No summary available.
ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ.ም .
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ መኰንን ገ/ሕይወት አመልካች፡- ሮያል ከረሜላ ኃ/የተ/የግ/ማህበር - ጠበቃ አቶ መድህን መሐሪ ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሪት ፀሐይ ብርሀኑ - ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ እንዲሻርልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የተጠሪ የሥራ ስንብት በአሰሪው (በአመልካች) አነሣሽነት የተፈፀመ ነው ወይስ በተጠሪ (በሰራተኛዋ) ጠያቂነት የተፈፀመ ነው የሚለውን ጭብጥ የሚመለከት ነው።
የክርክሩ መነሻ ተጠሪ ለፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አመልካች ከህግ ውጭ ከሥራ ያሰናበተኝ በመሆኑ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ መሰረት የተለየዩ ክፍያዎች እንዲከፍል ይወሰንልኝ በማለት ያቀረበችው ክስ ነው። አመልካች ተጠሪ ሥራቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁት ከቅርብ አለቃቸው ጋር ባለመግባባታቸው ነው። የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ተጠሪ (ከሣሽ) ወደ ሥራቸው እንድትመለስ በቃልና በጽሑፍ የጠየቋት ቢሆንም ከሣሽ (ተጠሪ) ወደሥራዋ ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆነችም፣፣ ከሣሽ (ተጠሪ)ን ከሥራ ለማሰናበት ሥልጣን በተሰጠው ኃላፊ የሥራ ውላቸው አልተቋረጠም። የሥራ ውሉ የተቋረጠው በተጠሪ ፈቃድ ነው የሚል ክርክር አቅርቧል። የሥር ፍርድ ቤት የሥራ ውሉ የተቋረጠው በአሰሪው ነው ወይስ በሰራተኛው ተነሣሽነትና ፈቃድ የሚለውን ጭብጥ በመያዝ የግራ ቀኙን ማስረጃ ሰምቷል።
ተጠሪ ሥራውን የለቀቅሁት የቅርብ አለቃዬ ሥራውን እንድለቅና እንድሄድ ስላዘዙኝ ነው በማለት ጭብጥ አስይዘው ምስክሮች አስምተዋል። በልላ በኩል አመልካች የተጠሪ የቅርብ አለቃ ተጠሪን ከሥራ ውጪ ካላት በኃላ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ተጠሪ የቀረበችበት ደመወዝ ተከፍሐት ከቅርብ አለቃዋ ጋር የተፈጠረው ችግር ተስተካክሎ ሥራውን ለመቀጠል የምትችል መሆኑን ተጠይቃ ተጠሪ እንቢተኛ መሆኗን አመልካች አስረድቷል።
ስለዚህ ተጠሪን ከሥራ የማስናበት ሥልጣን የልለው ሰው ከሥራ ውጪ በማለት ተናግሮኛል በማለት ወደ ሥራ እንድትመለስ ብትጠየቅ እንቢተኛ በመሆኗ የሥራ ውሉ የተቋረጠ በመሆኑ የሥራ ውሉ የተቋረጠው በተጠሪ ፈቃድ (አነሣሽነት) ነው በማለት ወስኗል። የሥር ፍርድ ቤት አመልካች ለተጠሪ የሥራ ስንብት ክፍያ ብር 520 (አምስት መቶ ሃያ ብር) የዓመት እረፍት ፈቃድ በገንዘብ ተቀይሮ ብር 190.67 (አንድ መቶ ዘጠና ብር ከስልሣ ሰባት ሣንቲም) እና የዘጠኝ ቀን ደመወዝ ብር 48 (አርባ ስምነት ብር) እንዲከፍል በማለት ወስኗል።
ተጠሪ በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይገባኝ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርባለች። የከፍተኛው ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ይግባኝ ባይ በቅርብ አለቃቸው ከሥራ እንዲወጡ መደረጉ ተረጋግጧል። የይግባኝ ባይ የቅርብ አለቃ ሰራተኛ የማሰናበት ሥልጣን የልላቸው መሆኑና ይግባኝ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተጠይቀው ወደ ሥራ ለመመለስ አለመስማማታቸው ስንብቱን ህጋዊ አያደርገውም። ስለዚህ አመልካች የሥራ ውሉን ያቋረጠው በህገ ወጥ መንገድ በመሆኑ፣ የመጀመሪያ ደረጃው ፍርድ ቤት ከወሰናቸው ክፍያዎች በተጨማሪ የካሣ ክፍያና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ መልስ ሰጭ ለይግባኝ ባይ ይክፈል በማለት ወስኗል።
አመልካች ሚያዚያ 25 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ የቅርብ አለቃዋ ሥራዋን እንድታቋርጥ ከተናገራት በኋላ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ተጠሪ ስራዋን እንድትቀጥል የነገራትና እንቢተኛ ሆና ከሥራ ገበታዋ የቀረች መሆኑ እንደተረጋገጠ የከፍተኛው ፍርድ ቤት በውሣኔው አስፍሯል። ይህ ፍሬ ጉዳይ ህግ ወጥ ስንብትን ያሣያል በማለት የሰጠው ውሣኔ የአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረታዊ ዓላማ ያልተከተለና የህግ መሰረት የልለው ነው በማለት አመልክቷል። ተጠሪ የሥራ ውሉ የተቋረጠው በቅርብ አለቃዬ ተዘልፍና ሞራል ተነክቶ ነው። ሥራ አስኪያጁም ይህንን የቅርብ አለቃዬን ተግባር ደግፈዋል። ስለዚህ ስንብቱ ህገ ወጥ ነው መባሉ ተገቢ ነው በማለት ሐምል 30 ቀን 2004 ዓ.ም መልስ ሰጥታለች።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው የጽሑፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች ተጠሪን ከሥራ ያሰናበታት በህገ ወጥ መንገድ ስለሆነ የማስጠንቀቂያና የካሣ ክፍያ የመክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት የሰጠው ውሣኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርመረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው የተጠሪ የቅርብ አለቃ ተጠሪን ከስራ እንድትወጣ የተናገራት መሆኑ በሥር ፍርድ ቤትና በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ተረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪ የተጠሪ የቅርብ አለቃ ተጠሪን ሥራ ለቅቃ እንድትወጣ ከተናገራት በኋላ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ተጠሪን ቢሮ ድረስ በማስጠራት በቅርብ አለቃዋ የተሰጠው ትእዛዝ ተገቢ እንዳልሆነ፣ የቀረችበት ቀን ደመወዝ እንደሚከፈላትና ወደ ሥራዋ እንድትመለስ ጠይቋት ተጠሪ ወደ ሥራ ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆነች መሆኑን የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ያረጋገጡት ፍሬ ጉዳይ ነው።
ተጠሪን ሥራ ለቅቃ እንድትሄድ የተናገራት የተጠሪ የቅርብ አለቃ በድርጅቱ ያለው ኃላፊነት በሥራ መሪነት የሚያስመድበውና፤ በሥራ መሪነቱ የተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነትም ሰራተኛ ለማሰናበት የሚያስችለው ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 2(ሐ) በአዋጅ ቁጥር 494/98 እንደተሻሻለው ተጠሪ አላስረዳችም። በልላ በኩል የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ተጠሪ የቅርብ አለቃ ስራዋን እንድትለቅ መወሰኑ ተገቢነት የልለው በመሆኑ ተጠሪ ወደ ሥራዋ እንድትመለስ ተጠሪን ጠይቀዋት ተጠሪ እንቢተኛ በመሆኗ የሥራ ውሉ የተቋረጠ መሆኑ ተረጋግጧል።
አንድ ሰራተኛ ከሥራ ለማሰናበት ስልጣንና ኃላፊነት የልለው የቅርብ አለቃው ከሥራ ለቅቆ እንዲሄድ ስለተናገረው ብቻ፣ አሰሪው የሥራ ውሉን አቋርጦታል ብሎ ለመደምደም አይቻልም። ሰራተኛው የሥራ ውል ተቋርጧል ከማለቱ በፊት የቅርብ አለቃው በሥራ ያለውን ሰራተኛ፣ ከመምራትና ከመቆጣጠር ባለፈ በሰራተኛው ላይ የዲሲፒላን እርምጃ ለመውሰድና ያለውን ሥልጣን በተለይም ከሥራ የማስናበት ሥልጣን ያለው መሆኑን ወይም አለመሆኑን የማወቅና የማረጋገጥ ግድታ አለበት። ተጠሪ የቅርብ ኃላፊዋ ሥራ ለቅቃ እንድትወጣ ቢናገራትም የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የቅርብ አለቃዋ እሷን ከሥራ የማሰናበት ስልጣን እንደልለው ገልፀው ወደ ሥራ እንድትመለስ ጠይቀዋል።
ይህ ከሆነ አመልካች የሥራ ውል ለማቋረጥና ተጠሪን ከሥራ ለማስናበት ሥልጣንና ኃላፊነት ባለው የሥራ መሪ በኩል የሥራ ውልን አቋርጧል ብሎ ለመደምደም የሚያስችል የህግ መሰረት የለም። ስለዚህ የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ በቅርብ አለቃዋ ሥራ እንድትለቅ የተናገራት መሆኑ ብቻ የሥራ ስንብቱን ህገ ወጥ ያደርገዋል። የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ተጠሪ ወደ ሥራ እንድትመለስ መጠየቁ ህገ ወጥ ስንብቱን ህጋዊ አያደርገውም በማለት የሰጠውን የህግ ትርጉም የአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረታዊ ዓላማ ያላገናዘበና መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ተሽሯል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ፀንቷል።
በዚህ ፍርድ ቤት የወጣውን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሣቸው ይቻሉ።
መዝገቡ ተዘግቷል። መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.