No summary available.
ህዳር ዐ4 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል አዳነ ንጉሴ መኰንን ገ/ሕይወት ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ነገረ ፈጅ አቶ ጌታቸው ለማ ቀረቡ ተጠሪዎች፡-
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
የሰበር አቤቱታው የቀረበው የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ሚያዝያ 1ዐ ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ መሰረታዊ የሕግ ሥህተት አለበት በማለት ፍርዱ እንዲሻር እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 191ዐ1 ጥር 14 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ ይፀና ዘንድ ነው። አመልካች በሥር ፍ/ቤት ተከሣሽ ሲሆን ተጠሪዎች ከሣሾች ነበሩ።
የጉዳዩን አመጣጥ ስንመለከት ተጠሪዎች በሥር ፍ/ቤት በአሁኑ አመልካች ላይ ያቀረቡት ክስ ተከሣሽ /በአሁኑ አመልካች/ በተለያዩ ጊዜያት በጉልበት፣ በፍራዮነትና ረዳት ፍራዮነት በተለያየ የደመወዝ መጠን ቀጥሮ ሲያሰራን ቆይቶ አለአግባብ ከሥራ ያሰናበተን ስለሆነ ውዝፍ ደመወዝ ከፍሎ ወደ ሥራችን ይመልሰን ዘንድ ይወሰንልን ካልሆነም ያለአግባብ የሥራ ውሉ መቋረጥ ጋር በተያያዘ ላከፍለን የሚገባውን ክፍያዎች ይከፍለን ዘንድ ይወስንልን የሚል ነው።
ተከሣሽ /የአሁኑ አመልካች/ በሰጠው መልስ ከሣሾች /የአሁኑ ተጠሪዎች/ የደመወዝ መጠን የተለያየ መሆኑ የሥራ ውሉም የተቋረጠው ተጀምሮ የነበረው የፕሮጀክት ሥራ በመጠናቀቁ ስለሆነ የጠየቁት ክፍያ የሚገባቸው አይደለም ብሐል።
ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር እና ማስረጃ መርምሮ ተከሣሽ /የአሁኑ አመልካች/ ከሣሾችን /የአሁኑ ተጠሪዎች/ ሥም ዝርዝር ያለበትና በተለያየ ሙያ ሲሰሩ መቆየታቸው እና የበጋ ወራት ከጥቅምት ዐ1 ቀን ጀምሮ ፕሮጀክቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የተቀጠሩ ለመሆናቸው የሚያሣይ ሰነድ ከሐምል ዐ2 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም ጀምሮ የሥራ ውሉ የተቋረጠ መሆኑን የሚገልጽ ሰነድ ያቀረበ ሲሆን ይህም ከሣሾች የተቀጠሩት ለተወሰነ ጊዜ መሆኑ ያመለክታል።
2ኛ እና 4ኛ ከሣሾችም ያቀረቡት የምስክር ወረቀት ላልተወሰነ ጊዜ ለመቀጠራቸው አያመለክትም በማለት ተከሣሽ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 77 መሰረት የዓመት ዕረፍት የ14 ቀን ክፍያ ለከሣሾች ይክፈል ሲል ወስኗል።
ከሣሾችው በውሣኔው ቅር በመሰኘት ይግባኝ ያቀረቡ ሲሆን የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ሥራ ክርክር ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ መልስ ሰጪ ቅጥሩ ለተወሰነ ጊዜ ነው ቢልም የሥራ ቅጥር አላቀረበም፣ ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎችም ውስጥ ለውስጥ ራሱ የተፃፃፈባቸው ናቸው፣ ይግባኝ ባዮች ከ6 እስከ 14 ዓመት ያገለገሉ ለመሆናቸው ተረጋግጧል፣ ቋሚ ሰራተኞች ናቸው ስንብቱ ሕገወጥ ነው በማለት የሥር ፍ/ቤትን ውሣኔ ሽሮ፤ መልስ ሰጪ ለይግባኝ ባዮች የስንብት ካሣ፣ የማስጠንቀቂያ እና የዓመት ዕረፍት ክፍያዎችን ይክፈል ሲል ወስኗል።
የሰበር አቤቱታው የቀረበው በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ሲሆን አመልካች በተወካዩ አማካኝነት ግንቦት 15 ቀን 2004 ዓ.ም ጽፎ ያቀረበው አቤቱታ አጠር ባለመልኩ፡- ተጠሪዎቹ ለ2ዐዐ2 ዓ.ም የበጀት ዓመት ለበጋ ወራት መቀጠራቸው እየታወቀ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ተጠሪዎቹ ላልተወሰነ ጊዜ የተቀጠሩ ናቸው ሲል መወሰኑ የሕግ ሥህተት ነው ማስረጃችንንም አልመረመረም፡- ተጠሪዎቹ የቅጥር ጊዜ በማለት በክስ ማመልከቻቸው ላይ ከመግለፃቸው ባለፈ በማስረጃ ሣያረጋግጡ ተጠሪዎች ከ6 እስከ 14 ዓመት ድረስ አገልግለዋል ሲል ፍ/ቤቱ መወሰኑ፤ ተጠሪዎቹ የተቀጠሩት ለተወሰነ ጊዜ መሆኑ የሥር ፍ/ቤት በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 24/1 መሰረት የሰጠውን ውሣኔ ቅጥሩ በአዋጁ አንቀጽ 39 እንደሆነ በማስመሰል የስንብት ካሣ ክፍያ ይከፈል ሲል መወሰኑ የሕግ ሥህተት ፈጽሟል። ተጠሪዎቹ የቀን ሰራተኞች እንደመሆናቸው መጠን በወር 22 ቀናት እንደሚከፈላቸው እየታወቀ ክፍያው በ30 ቀናት እንዲታሰብ ማድረጉ አግባብ ስላልሆነ፤ ችሎቱ የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤትን ውሣኔ ሽሮ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የሰጠውን ውሣኔ ያፅናልኝ የሚል ነው።
ችሎቱ የሰበር አቤቱታውን መርምሮ ሰኔ 22 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፡“ ተጠሪዎች የተቀጠሩት ለፕሮጀክት ሥራ መሆኑንና ሥራው መጠናቀቁን አመልካች ቢያስረዳም፣ የሥር ፍ/ቤት ተጠሪዎች በክሳቸው ላይ የገለፁትን የአገልግሎት ዘመን መሰረት በማድረግ ተጠሪዎች ለረዥም ጊዜ ሲሰሩ የቆዩ በመሆናቸው ላልተወሰነ ጊዜ እንደተቀጠሩ ይቆጠራል በማለት የተለያዩ ክፍያዎችን ይከፈላቸው በማለት የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ለሰበር ችሎት ይቅረብ ” ሲል አዟል።
የሰበር ችሎቱ ተጠሪዎቹ የሰበር አቤቱታው እንዲደርሣቸው በማድረግ፣ መልስ እንዲሰጡበት ያደረገ ሲሆን ተጠሪዎቹ ሐምል 26 ቀን 2004 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት 4 ገጽ መልስ፡ተጠሪዎች ከ2002 ዓመት በፊት ለመሥራታችን የ1999 ዓ.ም እና የ2000 ዓ.ም የመልካም ሥራ አፈፃፀም የምስክር ወረቀት አቅርበናል። መልስ ሰጪ ከ6 እስከ 14 ዓመት ላለመስራታችን አላስተባበለም “ እኛ ግን ምስክሮቻችን አስረድተውልናል” ተጠሪዎች የተቀጠርነው በዋና ቱቦ ማምረቻ ምርት ክፍል ሲሆን ሥራው በጋ እና ክረምት ሣይል ሁል የሚሰራበት ነው። አመልካች ተጠሪዎች የቀጠርኳቸው ለበጋ ጊዜ መንገድ ሥራ ነው ያለ ቢሆንም በየትኛው የአስፋልት ሥራ ለመሆኑ አልጠቀሰም።
ደሞዝን በተመለከተ አመልካች ይከፍለን የነበረው በወርሃዊ የሂሣብ ክፍያ ሲሆን ቅዳሜ እና እሁድ እናርፍ የነበረው በዓላት በመሆናቸው ነው።
ስለሆነም የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጠው ውሣኔ በአግባቡ ስለሆነ የተፈፀመ የሕግ ሥህተት የለም በማለት ውሣኔውን በማጽናት ያሰናብተን የሚል ነው።
አመልካች ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም ጽፎ ባቀረበው የመልስ መልስ የአመልካች መሥሪያ ቤት ከተቋቋመበት እስከ ተጠሪዎች ስንብት ድረስ 12 ዓመት ከ3 ወር የሚሆነው ሲሆን፤
ተጠሪዎቹ እስከ 14 ዓመት ድረስ የአገልግሎት ጊዜ ነበረን ማለታቸው እውነታ የልለው ነው።
የምስክር ወረቀትን በተመለከተ ከ2ኛ እና 4ኛ ተጠሪዎች በስተቀር ምስክር ወረቀት ያቀረበ የለም። ምስክር ወረቀቱም ቢሆን በየዓመቱ ለሰራተኛ የሚሰጥ እንጂ ቋሚ ሥራን የሚመለከት አይደለም።
ተጠሪዎች በጊዜያዊነት የተቀጠሩት በቱቦ ሥራ ፕሮጀክት ቢሆንም ቅጥራቸው ለበጋ ወራት አስፋልት ሥራ ፕሮጀክት ነው የሚል ነው።
ችሎቱም የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ተጠሪዎቹ ላልተወሰነ ጊዜ የተቀጠሩ ቋሚ ሰራተኞች ናቸው ሲል በመወሰኑ፣ የፈፀመው መሰረታዊ የሕግ ሥህተት አለ ወይስ የለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ የግራ ቀኙን ክርክር መርምሯል።
ፍ/ቤቱ አመልካች ተጠሪዎችን ለተወሰነ ጊዜ ቀጥሯቸዋል ያለበት ምክንያት አመልካች የሥራ ቅጥር ውል አላቀረበም በሚል ነው። ግራ ቀኙ የሥራ ቅጥር ውል ያላቸው ለመሆኑ አልተካካዱም። አመልካች የሥራ ቅጥር ውል ካላቀረበ ቅጥሩ ላልተወሰነ ጊዜ የተደረገ ነው ላባል የሚችልበት ሁኔታ የለም።
የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ተጠሪዎች ላልተወሰነ ጊዜ ተቀጣሪዎች ናቸው ያለበት ልላው ምክንያት አመልካች ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎች በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ለውስጥ የተፃፃፈባቸው ናቸው በሚል ነው። አመልካች ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎች ለቀረበው ክስ እና ለተያዘው ጭብጥ አግባብነት አላቸውን? በሚለውን ጥያቄ ዙሪያ መታየት ያለበት የሥራ ቅጥሩ ለተወሰነ ጊዜ ነው ወይስ ላልተወሰነ ጊዜ የሚለውን ጭብጥ ከማስረዳት አንፃር ታይቶ መወሰን ሲገባው ሰነዶቹ አመልካች ራሱ የተፃፃፈባቸው ናቸው በሚል ምክንያት ብቻ ውድቅ የሚደረጉበት አግባብ የለም።
በሥር ፍ/ቤትም ቢሆን አመልካች ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎች በማስረጃነት የተቀበላቸው ማስረጃዎቹ የሥራ ቅጥሩ ለፕሮጀክት ሥራ ሆኖ የበጋ ወራት የአስፋልት ሥራ መሆኑን እና ሥራውን ማብቃቱ የሚያመላክቱ በመሆናቸው ሲሆን እነዚህ ማስረጃዎች ለተያዘው ጭብጥ አግባብነት የልላቸው ስለመሆኑ ያስተባበሉት ነገር የለም።
የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ተጠሪዎቹ ከስድስት እስከ አስራ አራት ዓመት የሥራ አገልግሎት አላቸው ሲል የደመደመው ተጠሪዎቹ በክስ ማመልከቻዎቻቸው ጠቅሰውታል በሚል እንጂ ተጠሪዎቹ ይህን ያህል የአገልግሎት ዘመን ያላቸው ባለመሆኑ ያመለከቱበት ደጋፊ ማስረጃ የለም።
2ኛ እና 4ኛ ተጠሪዎች በ1999 ዓ.ም እና 2ዐዐዐ ዓ.ም ተሰጠን የሚሉት የመልካም ሥራ አፈፃፀም የምስክር ወረቀትም ቢሆን አመልካች ይህ የመልካም ሥራ አፈፃፀም ምስክር ወረቀት ለሁሉም በየዓመቱ የሚሰጥ ነው በማለት የተከራከረ ሲሆን ማስረጃው ሁለቱ ተጠሪዎች በተጠቀሱት ሁለት ዓመት የምስክር ወረቀቶቹ የተሰጣቸው ለመሆኑ ከሚያሣይ በስተቀር ተጠሪዎቹ ላልተወሰነ ጊዜ የተቀጠሩ ለመሆኑ የሚያሣይ አይደለም። አመልካች ተጠሪዎች የተቀጠሩት ላልተወሰነ ጊዜ ነው በማለት የተከራከረ ሲሆን ተጠሪዎቹ አላስተባበሉም።
ተጠሪዎቹ የተቀጠርንበት የቱቦ ሥራ ቀጣይነት ያለው ነው ያሉ ቢሆንም ተጠሪዎቹ ቀጣይነት ባለው የቱቦ ሥራ ለተወሰነ የሥራ ጊዜ የተቀጠሩ ከሆነ ሥራው ቀጣይነት ስላለው ብቻ ቅጥሩ ላልተወሰነ ጊዜ ነው በማለት ፍ/ቤቱ መወሰኑ የሕግ ሥህተት ነው። በመሆኑም የሚከተለውን ውሣኔ ሰጥተናል።
ው ሣ ኔ
የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመዝገብ ሚያዝያ 1ዐ ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ በፍ.ሥ.ሥ.ሕግ ቁጥር 348/1 መሰረት ተሽሯል።
የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመዝገብ ቀጥር 191ዐ1 ጥር 14 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 348/1 መሰረት ፀንቷል።
ተጠሪዎቹ ለተወሰነ የሥራ ጊዜ የተቀጠሩ ናቸው።
ግራ ቀኙ ወጪና ኪሣራቸውን የየራሣቸው ይቻሉ። መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.