No summary available.
ህዳር 19 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ተኽላት ይመስል አመልካች፡- የመቶ አለቃ ጥላሁን ታችበል - ቀረቡ ተጠሪ፡- ግሎባል ሆቴል ኃ/የተ/የግል ማህበር - አልቀረቡም **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
አቤቱታው ለሰበር ችሎት ላቀርብ የቻለው አመልካች ከሥራ በጡረታ ምክንያት በአሰሪ መሰናበታቸው እና ተፈፃሚነት ያለው ሕግ የሕብረት ስምምነት ነው ወይስ የጡረታ አዋጅ ነው የሚለው የሕግን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ጉዳዩን ለመመርመር ነው። አመልካች በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት ያቀረቡት ክስ በተጠሪ ድርጅት በጥበቃ ሰራተኝነት ተቀጥረው እስከ ታህሣሥ 23 ቀን 2003 ዓ.ም ድረስ ማገልገላቸውና ተጠሪ ድርጅት ጡረታን ምክንያት አድርጎ መብታቸውን ሳይጠብቅ ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውላቸውን ያቋረጠ በመሆኑና ስንብቱ ሕገወጥ በመሆኑ ሕጉ በሚፈቅደው ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ጠይቋል። ተጠሪ ድርጅት በሰጠው መልስ በድርጅቱ የሕብረት ስምምነት አንቀጽ 32.5 መሰረት ተጠሪ የሰራተኞችን የጡረታ መውጫ ጊዜ ለመወሰን ሥልጣን የተሰጠው መሆኑ አመልካችም ዕድሜያቸው 55 ዓመት የሞላቸው በመሆኑ በሕብረት ስምምነቱ መሰረት የፕሮቨደንት ፈንዳቸው ተከፍሐቸው በልዩ ሁኔታም የሁለት ወር ደመወዝ ተከፍሐቸው ተሰናብቷል። ስንብቱም በአግባቡ የተከናወነ ነው በማለት መልስ ሰጥቷል። የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የሥር ፍርድ ቤት ስንብቱ በሥራ ላይ ባለው የሕብረት ስምምነት የተፈፀመ በመሆኑ ሕጋዊ ነው። ምንም ክፍያ መጠየቅ አይችሉም በማለት ወስኗል። በይግባኝ ሥልጣኑ የተመለከተው ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348/1/ መሰረት የይግባኝ ባይ ቅሬታን የሥር ፍርድ ቤት ውሣኔን አፅንቷል።
አመልካች የሥር ፍርድ ቤቱ ፈጽሞታል ያሉትን የሕግ ስህተት በመዘርዘር ቅሬታቸውን አቅርበዋል። በአመልካች አቤቱታ ከተዘረዘሩት የቅሬታ ነጥቦች የጡረታ ዕድሜ በሕግ እንጂ በሕብረት ስምምነት ላወሰን እንደማይገባ፤ አሰሪው /ተጠሪ/ ተቋም ሕገወጥ ስንብት የፈፀመ በመሆኑ የ6 ወር ደመወዝ በካሣ መልክ እንዲከፍላቸው እንዲወሰንላቸው አመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ምድብ 1ኛ የሥራ ክርክር ችሎት በተመሣሣይ ጉዳይ በመ/ ህዳር 11 ቀን 2004 ችሎት የጡረታ ዕድሜ አግባብ ባለው ሕግ እንጂ በሕብረት ስምምነት የሚወሰን አይደለም በማለት የሰጠው ውሣኔ እንዲታይላቸው አያይዘው አቅርበዋል።
ተጠሪ በሰጠው መልስ አመልካች ከሥራ የተሰናበቱት በተጠሪና በሰራተኞች ማህበር መካከል በተፈረመው የሕብረት ስምምነት አንቀጽ 32.5 መሰረት ነው፤ ተዋዋይ ወገኖችም የጡረታ ዕድሜን ላወሰኑ እንደሚችሉ የሕብረት ስምምነቱን የፈረሙት ተዋዋይ ወገኖች የተስማሙ በመሆኑና አመልካች በዚህ አግባብ በሕጋዊ መንገድ የተሰናበተ በመሆኑ ስንብቱ ሕጋዊ ነው እንዲባልለት አመልክቷል። የአመልካች የመልስ መልስ ቅሬታቸውን የሚያጠናክር ነው።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው የጽሑፍ ክርክር ከላይ የተገለጸ ሲሆን ችሎቱም ጉዳዩን መርምሯል። ጉዳዩን እንደመረመርነው በአዋጅ ቁጥር 377/1996 የሚገዙ ሰራተኞች የጡረታ ዕድሜ የሚወሰነው አግባብ ባለው ሕግ ነው ወይስ በሕብረት ስምምነት? የሚለው ጭብጥ መታየት ያለበት ሆኖ ተገኝቷል።
አመልካች በግሎባል ሆቴል ኃ/የተ/የግል ማህበር በጥበቃ ሰራተኛነት ሲሰሩ እንደነበረ፤
በሕብረት ስምምነቱ አንቀጽ 32.5 መሰረት 55 ዓመት የሞላቸው በመሆኑ በጡረታ ከሥራ እንዲሰናበቱ ተጠሪ መወሰኑ ከሥር ፍርድ ቤቶች መዝገብ መገንዘብ ተችሐል። አመልካች የጡረታ ጉዳይ መታየት ያለበት በሕግ እንጂ በሕብረት ስምምነት አለመሆኑን አጥብቀው ሲከራከሩ ተጠሪ በበኩሉ የሕብረት ስምምነቱ በተጠሪ ድርጅት እና በሰራተኛ ማኀበር የተፈረመና ተግባራዊ መሆኑ ከሕግ እንደማይቃረን አመልክቷል። በአሰሪና ሰራተኛ መካከል የነበረው የሥራ ውል ግንኙነት ከሚቋረጥባቸው መንገዶች አንዱ ሰራተኛው በጡረታ ሲገለል ነው። በዚህ ጉዳይ አከራካሪው ጭብጥ የጡረታ መውጫ ጣሪያ ዕድሜ ስንት ነው? በሕግ ነው የሚወሰን ወይስ በሕብረት ስምምነት የሚለው ነው። የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 የጡረታ ዕድሜ ጣሪያ በግልጽ አልደነገገም። ይሁንና አዋጁ በአንቀጽ 24/3/ “ሰራተኛው አግባብ ባለው ሕግ መሰረት በጡረታ ሲገለል” የሥራ ግንኙነቱ በሕግ አግባብ የተቋረጠ መሆኑ ተመልክቷል።
በአሰሪና ሰራተኛ ማህበር የሚፈረመው የሕብረት ስምምነት በተመሣሣይ ጉዳይ ለሰራተኛው በሕግ ከተደነገገው ይልቅ የሕብረት ስምምነቱ የበለጠ ጥቅም የሚሰጠው ከሆነ ተፈፃሚነት እንደሚኖረው በአንቀጽ 134/2/ ተመልክቷል። አመልካች ያለፈቃዳቸው በጡረታ ከሥራ እንዲሰናበቱ የተደረገ መሆኑ በሥር ፍርድ ቤት ካቀረቡት ክርክር መገንዘብ ይቻላል። ተጠሪም የስንብት ድርጊቱ የተፈፀመው ለሰራተኛው የተሻለ ጥቅም የሚሰጥ ስለመሆኑ አላስረዳም።
በመሆኑም ተጠሪ በስንብት ስርዓቱ የሕብረት ስምምነት የተፈፀመ ነው ይበል እንጂ የሕብረት ስምምነቱ አግባብነት ካለው ሕግ በተሻለ መንገድ ለሰራተኛው የጠቀመ ስለመሆኑ በሥር ፍርድ ቤት ክርክር አልተረጋገጠም። ስለሆነም የሕብረት ስምምነቱ የጡረታ ዕድሜን ከመወሰን አኳያ የተፈፃሚነት ወሰን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ሆኖ ተገኝቷል።
ከዚህም በቀር የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሁለት የተለያዩ ምድብ ችሎቶች በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 24/3/ አተረጓጐም ላይ የተለያየ አቋም ወስደዋል። ይህ ደግሞ አዋጁን ወጥ በሆነ አግባብ ከመተርጎም አንፃር የራሱ የሆነ ውስንነት እንዳለው እንዲሁም የተከራካሪ ወገኖችን በሕግ ፊት እኩል የመዳኘት መብት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው። አንደኛው ምድብ ችሎት በሕብረት ስምምነት የተወሰነውን የጡረታ ዕድሜ ጣሪያ ሲቀበል ልላኛው ምድብ ችሎት አግባብነት ያለው ሕግ ማለት የሕብረት ስምምነት አለመሆኑን በመጥቀስ ውድቅ አድርጐታል።
አከራካሪው ጉዳይ አግባብነት ያለው ሕግ የምንለው የትኛው ነው የሚለው ነው። ከፍ ሲል እንደተገለጸው የሕብረት ስምምነቱ በአንቀጽ 24/3/ የተመለከተውን ትርጓሜ የማይካተት መሆኑ ግልጽ ነው። ሕግ የምንለው ሥልጣን ባለው አካል የወጣ ሕግ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የሕግ አወጣጥ ሥርዓት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም በአስፈፃሚው አካል የሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎችን የሚያካትት መሆኑን መረዳት ይቻላል። የጡረታ ዕድሜ መውጫን በተመለከተ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተለያየ የዕድሜ ጣሪያ የተቀመጠ ቢሆንም በሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች አዋጅ እንዲሁም የግል ሰራተኞች የጡረታ አዋጅ ቁጥር 715/2003 አንቀጽ 17/1/ የሰራተኛው የጡረታ መውጫ ዕድሜ 60 ዓመት መሆኑን ደንግጓል።
በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤቶች ለዚህ ጉዳይ ተፈፃሚነት ያለው ሕግ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች አዋጅ እንደ አግባብነቱ ወይም የግል ሰራተኞች የጡረታ አዋጅ ሆኖ ሳለ የሕብረት ስምምነቱን መውሰዳቸው መሰረታዊ የሕግ አተረጓጐም ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ተገኝቷል።
በመሆኑም ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በ27/02/2004 ዓ.ም እንዲሁም የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ በ02/8/2004 ዓ.ም የሰጡት ውሣኔ ተሽረዋል።
ግሎባል ሆቴል ኃላ.የተ.የግል ማህበር እና የተቋሙ ሰራተኞች ማህበር የፈረሙት የሕብረት ስምምነት የጡረታ መውጫ ዕድሜን በተመለከተ በዚህ ጉዳይ ተፈፃሚነት የለውም ብለናል።
ፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በፍሬ ጉዳዩ ላይ ግራ ቀኙን በማከራከር በተነሱት የክፍያና ተያያዥነት ያላቸው የመብት ጥያቄዎችን እንዲወስን ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 341/1 መሰረት መልሰን ልከንለታል።
ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሳቸው ይቻሉ ብለናል።
መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.