No summary available.
ጥር 28 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የኢትዮጵያ የእህል ንግድ ድርጅት ተጠሪዎች፡-
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ሆኖ በአሁን የሰበር ተጠሪዎች ከሳሽነት የተጀመረው በፍ/የመ/ደ/ፍርድ ቤት ሲሆን አመልካች ድርጅት ደግሞ ተከሳሽ ነበር። ክሱም፡- ተከሳሽ ድርጅት ባካሄደው የመሰረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ መሰረት በተጠናው የደመወዝ እስኬል ለእያንዳንዱ የሥራ መደብ መነሻ ደመወዝ ሲወሰን ከሳሾች በተመደብንበት የሥራ መደብ ማግኘት የሚገባንን ሲወስን ቀደም ሲል ስናገኝ የነበረውን ደመወዛችንን የቀነሰብን ስለሆነ ያለአግባብ የቀነሰብንን ደመወዝ መልሶ እንዲያስተካክልልን ይወሰንልን የሚል ነው።
ተከሳሽም ለክሱ ባቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ፤-በተከሳሽ ድርጅት መሰረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ ተደርጎ በመንግስት ከጸደቀ በኋላ በአማካሪ ድርጅት የተጠናውን አዲስ የደመወዝ እስኬል መነሻ በማድረግ ከሳሾች ክሱን ያቀረቡ ስለሆነና የደመወዝ ጭማሪን የሚመለከት ክስ የወል የሥራ ክርክር ስለሚሆን መቅረብ ያለበት ለአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በቀጥታ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን የለውም ብሐል።
ፍርድ ቤቱም በመ/ደ/መቃወሚያ ላይ በሰጠው ብይን፡- ከሳሾች ባቀረቡት ክስ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ ጠቅላላ የደመወዝ እስኬል አሰራርን የሚነካ በመሆኑና ውጤቱም በልሎች ሰራተኞች ላይ አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ተጽዕኖ ላያስከትል ስለሚችል በወል የሥራ ክርክር የሚሸፈን በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ክሱን ተቀብሎ ለመወሰን ሥልጣን የለውም በሚል የክሱን መዝገብ ዘግቷል።
የስር ከሳሾችም የመ/ደ/ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ወገን በማከራከር በሰጠው ፍርድ ይግባኝ ባዮች ባቀረቡት ክስ ላይ የሚወሰነው ጭብጥ ተቋረጠብን የሚሉት የደመወዝ ጭማሪ ነው? ወይስ ድጎማ ነው? የሚለው ሲሆን በዚሁ ጭብጥ ላይ የሚሰጠው ውሳኔም ከይግባኝ ባዮች አልፎ የሁሉንም ሰራተኞች መብትና ጥቅም የሚነካ ባለመሆኑ ጉዳዩ በግል የሥራ ክርክር የሚታይ ነው በማለት የመ/ደ/ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን በመሻር በፍሬ ጉዳዩ ላይ አከራክሮ እንዲወስን ክርክሩን መልሶለታል።
አመልካችም የሰበር አቤቱታ ያቀረበው በከፍተኛው ፍርድ ቤት ፍርድ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል ሲሆን በዋናነት የጠቀሰው የቅሬታ ነጥብም፡- ተጠሪዎች ያቀረቡት ክስ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 147(2) መሰረት በወል ሥራ ክርክር የሚሸፈን ሆኖ እያለ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በግል የሥራ ክርክር የሚሸፈን ነው በማለት ጉዳዩን የሥራ ክርክር ችሎት እንዲወስነው የመለሰው ያለአግባብ ነው የሚል ነው።
ተጠሪዎቸ በበኩላቸው በሰጡት መልስ፡- ክሱ የቀረበው አመልካች ድርጅት ሲከፈለን በነበረው ደመወዝ ላይ መዋቅሩን መሥራት ሲገባው ደመወዛችንን በመቀነስ መዋቅሩን የሰራ በመሆኑ የቀነሰብንን ደመወዝ መልሶ እንዲያስተካክል ዳኝነት የጠየቅንበት እንጂ ክርክራችን በተሰራው መዋቅር ላይ ባለመሆኑ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ክሱ በግል ሥራ ክርክር ችሎት የሚታይ ነው ሲል የሰጠው ፍርድ የሚነቀፍበት ምክንያት ስለልለው ላጸና ይገባል በሚል ተከራክረዋል።
አመልካች ድርጅትም ለተጠሪዎች መልስ የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክሯል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- ተጠሪዎች ያቀረቡት ክስ በወል የሥራ ክርክር የሚሸፈን ነው? ወይስ በግል ሥራ ክርክር የሚሸፈን ነው? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
የግል የስራ ክርክሮች በመደበኛ ፍርድ ቤት የሥራ ክርክር ችሎት የሚታዩ ስለመሆናቸው ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 138 መገንዘብ የሚቻል ሲሆን የወል ሥራ ክርክር ደግሞ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሣኝ ቦርድ የሚታይ መሆኑን በአዋጁ አንቀጽ 142(1)፣147(1)(ሀ) ተመልክቷል። እዚህ ላይ ዋናው ምላሽ የሚሻው ጉዳይ ግን አንድ ጉዳይ የግል ወይም የወል የሥራ ክርክር ላባል የሚችልበት አግባብ ነው። ይህን በተመለከተ ይህ ችሎት በሰበር መ/ቁ/18180 በቀን 29/11/1997 ዓ/ም በዋለው ችሎት አስገዳጅ የህግ ትርጉም የሰጠበት ሲሆን በዚሁ የህግ ትርጉም መሰረትም አንድ ጉዳይ የወል የሚያሰኘው የጋራ በሆነ የሰራተኞች መብትና ጥቅም ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ውጤት የሚያስከትል ሆኖ ሲገኝ ሲሆን ክርክሩ የግል ነው የሚባለው ደግሞ ዉጤቱ በተከራካሪ ሰራተኛ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሲሆን ነው። በዚህ በተያዘው ጉዳይ ተጠሪዎች ቀደም ሲል ሲናገኝ የነበረውን ደመወዝ አመልካች ያለአግባብ በመቀነስ በተሰራው መዋቅር ላይ ያስቀመጠው ስለሆነ የቀነሰብንን ደመወዝ መልሶ እንዲያስተካክል ይወሰንልን በሚል ክስ ያቀረቡ ሲሆን አመልካችም ቀደም ሲል በድጎማ መልክ ከደመወዛቸው ጋር ሲከፈላቸው የነበረው ገንዘብ ከደመወዛቸው ተቀንሶ በተሰራው መዋቅር ላይ ከመቀመጡ በስተቀር በደመወዛቸው እስኬል መሰረት ማግኘት የሚገባቸው ገንዘብ አልተቀነሰም በሚል ተከራክሯል። ይህ ከሆነ ደግሞ ቀደም ሲል መዋቅሩ ከመሰራቱ በፊት ሲከፈላቸው የነበረው የደመወዝ መጠን የድጎማ ክፍያ ተጨምሮ ነው? ወይስ ሳይጨመር ነው? ድጎማው ተቀናሽ ተደርጎ በተሰራው መዋቅር መሰረት የደመወዝ እስኬል ሲቀመጥ ተጠሪዎቹ ማግኘት ከሚገባቸው የደመወዝ መጠን ቀንሷል? ወይስ አልቀነሰም? የሚሉ ነጥቦች ከተጣሩ በኋላ የሚሰጠው ውሳኔ ደግሞ ከተጠሪዎች አልፎ የልሎች የድርጅቱን ሰራተኞች መብትና ጥቅም በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መንገድ ላነካ የሚችልበት ምክንያት የለም። በመሆኑም ተጠሪዎች መዋቅሩ ሲሰራ ቀደም ሲል ስናገኝ የነበረው የደመወዛችን እስኬል ተቀንሶብናል በማለታቸው ብቻ ጉዳዩ የወል ሥራ ክርክር ነው ላባል የሚችልበት ምክንያት ባለመኖሩ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተጠሪዎቹ ያቀረቡት ክስ በግል የሥራ ክርክር ችሎት የሚታይ ነው ሲል በሰጠው ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያልተፈጸመበት ሆኖ በማግኘታችን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍ/ከ/ፍርድ ቤት በመ/ቁ/115821 በቀን 10/7/2004 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የሰጠውን ፍርድ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት አጽንተናል።
ተጠሪዎች ያቀረቡት ክስ በግል የስራ ክርክር የሚሸፈን በመሆኑ ላቀርብ የሚገባው ለመደበኛ ፍርድ ቤት የሥራ ክርክር ችሎት ነው በሚል ከፍተኛው ፍርድ ቤት መወሰኑ ተገቢ ነው ብለናል።
የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ተከራካሪዎች የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.