No summary available.
ጥር 02 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የአብጃታ ሶዳ አሽ አክሲዩን ማህበር ተጠሪ፡- ወ/ሮ ማርታ አበበ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996"ን” መሰረት ያደረገ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው። የክሱ ይዘትም ባጭሩ፡-በአመልካች ድርጅት ከግንቦት 16 ቀን 1996 ዓ.ም. ጀምሮ በወር ደመወዝ ብር 1560.00 (አንድ ሺህ አምስት መቶ ስልሳ ብር) እየተከፈላቸው ሲያገለግሎ እንደቆዩና ነሐሴ 27 ቀን 2002 ዓ.ም. በተጻፈ ደብደቤ ከነሐሴ 28 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ የስራ ውሉ ያተቋረጠ መሆኑን አመልካች ያሳወቃቸው መሆኑን ዘርዝረውና የአመልካች እርምጃ ሕገ ወጥ መሆኑን ጠቅሰው የሞራል ካሳ ተከፍሐቸው ወደ ስራ እንዲመለሱ፣ይህ የማይቻል ከሆነ ደግሞ የስራ ውልን መቋረጥን ተከትሎ የሚከፈሉ ክፍያዎች እንዲከፈሐቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መከላከያ መልስም ተጠሪ በሐኪም ውሳኔ መሰረት በእርሷ ጤናና ሙያ የሚመጥን የስራ መደብ ባለመኖሩ ድርጅቱ ባገኘው አማራጭ፤ክፍት የስራ መደብ ላይ መብታቸውን ሳይነካ እንዲሰሩ ቢደረጉም ቦታው ደረጃዬን አይመጥንም በማለት ስራቸውን ትተው ፍርድ ቤትና ህክምና በመመላለስ የስራ ጊዜአቸውን የሚያባክኑ ስለሆነ በአማራጭ የተመደቡበትን፣ልላ የስራ መደብም ላይ እየሰራች ለመቀጠል ፍቃደኛ እንዳልሆኑ በመዘርዘር እርምጃው የሕብረት ስምምነቱንና ህጉን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጾ ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል።ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ በመመርመር የአመልካች እርምጃ ሕጋዊ ነው በማለት የተጠሪን ክስ ውድቅ አድርጎታል።በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የአመልካች እርምጃ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ ተጠሪን የስድስት ወር ውዝፍ ደመወዝ በመክፈል ወደ ሰራቸው ላመልሳቸው ይገባል ተብሎ ተወስኗል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ተጠሪ በሐኪም አስተያየት ለጤናቸው የሚመጥናቸው የስራ መደብ ሲሰጣቸው ላሰሩ ፍቃደኛ ያለመሆናቸው በመረጋገጡ ስንብቱ የተከናወነ መሆኑን የሚያረጋግጥ የአመልካች ማስረጃ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውድቅ የተደረገው የማስረጃውን ይዘት ካለማገናዘብ የተነሳ መሆኑንና ተጠሪ ወደ ስራ ይመለሱ ቢባል እንኳን ከአመልካች ጋር ሰላማዊ የሆነ የስራ ግንኙነት የሚኖራቸው ባለመሆኑ ተገቢ ክፍያዎች ተከፍሐቸው እንዲሰናበቱ ያለመወሰኑ ያላግባብ ነው በማለት የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሻር ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ላታይ የሚገባው መሆኑ ተምኖበት እንዲቀርብ ከተደረገ በኋላ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ተጠሪ ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።፡ የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን መርምሮታል።እንደመረመረውም ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ የተደረገው ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 28(1(ለ)) አኳያ የተፈፀመው የስራ ውል ማቋረጥ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ ተጠሪን የስድስት ወር ውዝፍ ደመወዝ በመክፈል ወደ ስራ ይመልስ የመባሉን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ነው።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ ክሱን የመሰረቱት የስራ ስንብቱ የተከናወነው ከሕግ ውጪ ነው በሚል ምክንያት ሲሆን የአሁኑ አመልካች ስንብቱ በሕጉ አግባብ የተደረገ መሆኑን ገልፆ በመከራከሩ የስር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ማስረጃዎችን በመመርመር ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት የደመደመውን ድምዳሜ ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያለው የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ ስራ አልፈልግም በማለት ያስታወቁ መሆኑን አመልካች በማስረጃዎቹ ያለማረጋገጡን፣ይልቁንም ተጠሪ ለአመልካች በሰጡት መልስ በቀድሞው ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት እንዲፈጸምላቸው የገለጹ መሆኑ መረጋገጡንና በጤናቸው ላይ የደረሰው የስራ ጉዳትም የስራ ግድታቸውን ለዘለቄታው ለመፈጸም የማይችሉ መሆኑ ያለመረጋገጡ በክርክሩ ሂደት መታወቁን በውሳኔው ላይ አስፍሯል። ከዚህ የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በግልፅ መረዳት የሚቻለው ውሳኔው የግራ ቀኙን ማስረጃና ክርክር በመመዘን በፍሬ ነገር ደረጃ ያረጋገጠው ስንብቱ በአመልካች ከሕግ ውጪ መከናወኑን ወይም አመልካች ስንብቱን በሕጉ አግባብ ያከናወነ መሆኑን በማስረጃዎቹ ያላስረዳ መሆኑን ሲሆን ይህ የይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ድምዳሜ የተያዘው ማስረጃን በመመዘን መሆኑን ነው።ይኸው ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠው ነጥብ የመጨረሻ ነው።እንደሚታወቀው ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 መሰረት የተሰጠው ስልጣን በበታች ፍርድ ቤቶች ማናቸውም የመጨረሻ ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ሲፈጸም ማረም እንጂ በማስረጃ ምዘና ላይ የሚያተኩር ክርክር የመመርመርና ስህተቱን የማረም ስልጣን የለውም።በመሆኑም በተያዘው ጉዳይም የአመልካች ክርክር ማስረጃ ምዘናን መሰረት ያደረገ በመሆኑና አመልካች በስራ ላይ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ስራውን ለዘለቄታው መፈጸም የማይችሉ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀፅ 28(1(ለ)) ድንጋጌ አግባብ ያላረጋገጠ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ለማለት አይቻልም።
ልላው አመልካች አጥብቆ የሚከራከረው ከተጠሪ ጋር የመሰረተው የስራ ግንኙነት ከሕግ አግባብ ውጪ ተቋርጧል ቢባል እንኳን ከተጠሪ ጋር ለወደፊቱ መልካም ግንኙነት ላኖር ስለማይችል ተያያዥ ክፍያዎች ተከፍሐቸው ተጠሪ ላሰናበቱ ይገባ ነበር በማለት ነው።በእርግጥ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል መልካም ግንኙነት መኖር ለኢንዱስትሪው ሰላምና ምርትና ምርታማነትን ከፍ በማድረግ ለአገር ኢኮኖሚ ተገቢውን አስተዋጽኦ ለማበርከት አስፈላጊ በመሆኑ ሰላማዊ ግኙነት እንደማይኖር የሚያሳዩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ጉዳዩን ለመመልከት ስልጣን ያለው አካል የስራ ውሉ የተቋረጠው ከሕግ ውጪ ነው ወደሚለው ድምዳሜ ቢደርስ እንኳን ሰራተኛው ወደ ስራ እንዲመለስ ከማድረግ በምትኩ ሕጋዊ ክፍያዎች ተከፍሎት እንዲሰናበት ማድረግ እንደሚገባ የአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 43(3) ድንጋጌ ይዘት ያስገነዝባል።ይህ ድንጋጌ ተግባራዊ ሲደርግ ግን የስራ ዋስትና ዋጋ በማያጣበት አግባብ ላከናወን የሚገባ መሆኑ የድንጋጌው መንፈስ ከአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ሕግ አጠቃላይ ዓላማና በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ሕግ መንግስት አንቀጽ 42 ስር ከተቀመጠው ድንጋጌ አንጻር ጋር ተዳምሮ ሲታይ የሚያስገነዝበን ጉዳይ ነው። ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም ተጠሪ ከአመልካች ጋር በሕጉ አግባብ የቅጥር ውል መስርተው በስራ ላይ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ከጤናቸው ጋር በሚመጥን ቦታ አመልካች ተጠሪን መድቦ እንዲያስራ በፍርድ ቤት ተወስኖ የነበረ ስለመሆኑ የክርክሩ ሂደት የሚያሳይ ሲሆን በዚህ ውሳኔ መሰረት ሳይፈጸም ግን አመልካች ላሰሩ ፍቃደኛ አልሆኑም፣ስራውንም ለመፈጸም አይችሉም በሚሉ ምክንያቶች የስራ ውሉን ከነሐሴ 28 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ አቋርጧል።ይህ የሚያሳየው አመልካች በተጠሪ ላይ የደረሰውን የስራ ጉዳት ምክንያት በማድረግ ለጤናቸው ተስማሚ በሆነው የስራ መደብ ላይ ለማሰራት ፍቃደኛ ባለመሆን የፀና መሆኑን ነው።ይህ ደግሞ ሕገ ወጥነት ያለው ተግባር ከሚባል በስተቀር በአዋጅ ቁጥር 377/196 አንቀፅ 43(3) ድንጋጌ መንፈስ መሰረት አመልካችና ተጠሪ መልካም የሆነ ግንኙነት አይኖራቸውም ብሎ ለመደምደም እና የስራ ውሉ እንዲቋረጥ ለማድረግ የሚበቃ ሕጋዊ ምክንያት አይሆንም። አንድ ሰራተኛ መብቱን ለማስከበር ፍርድ ቤት መሄዱ ብቻውን ከአሰሪው ጋር ለወደፊትም የሻከረ ግንኙነት ይፈጥራል ተብሎ የሚገመትበት ህጋዊ አግባብ የለም።ይልቁንም በፍርድ ቤት ውሳኔ መብቱን በማረጋገጥ የሚሰራ ሰራተኛ ለኢንዲስትሪው ሰላም ችግር የማይፈጥር ሰላማዊና በሕግ ልዕልና ከፍተኛ እምነት ያለው ነው ተብሎ የሚገመት መሆኑ ይታመናል።በመሆኑም አመልካች ተጠሪ የተለያዩ ክፍያዎች ተከፍሐቸው ላሰናበቱ ይገባል በማለት የሚያቀርበው አማራጭ ዳኝነት በተጠሪ ላይ ደረሰ ከተባለው የስራ ጉዳትና ከሕጉ አጠቃላይ መንፈስ አንጻር ሲታይ ተቀባይነት የልለው ሁኖ ተገኝቷል።ሲጠቃለልም የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የልለበት ሁኖ ስለአገኘን ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348 (1) መሰረት ፀንቷል።
በዚህ ችሎት ጥቅምት 14 ቀን 2005 ዓ.ም. ተሰጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል።
ለሚመለከታቸው አካላት ይጻፍ።
No topics extracted.