No summary available.
ጥር 14 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ዝዋይ ሮዝ ድርጅት ተጠሪ፡- ወ/ሮ ፋንቱ ያሲን መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ የተጀመረው በአዳሚ ቱሉ በወረዳ ፍርድ ቤት ሲሆን የአሁን የሰበር ተጠሪ የአፈጻጸም ከሳሽ አመልካች ደርጅት ደግሞ የአፈጻጸም ተከሳሽ ነበር።
ክሱም፡- የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/28572 በቀን 24/01/2004 ዓ.ም.
በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ መሰረት የአፈጻጸም ተከሳሽ ወደ ሥራ እንዲመልሰኝ ይታዘዝልኝ የሚል ነው።
የወረዳው ፍርድ ቤትም፡- በ17/04/2004 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በሰጠው ትዕዛዝ ከከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ መረዳት የተቻለው የፍርድ ባለመብቷን የፍርድ ባለዕዳው ወደ ሥራ እንዲመልሳቸው መወሰኑን እንጂ ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፈላቸው ባለመሆኑ የፍርድ ባለዕዳው የፍርድ ባለመብቷን ወደ ሥራ መመለሱን በ17/04/2004 ዓ.ም. ለፍርድ ቤቱ ከጻፈው ደብዳቤ የተረጋገጠ በመሆኑ እንደፍርዱ ፈጽሟል በማለት መዝገቡን ዘግቷል።
የአፈጻጸም ከሳሽም በወረዳው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቅር በመሰኘት ለዞኑ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ባቀረቡት ቅሬታ፡- ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመ/ቁ/28527 በ24/01/2004 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የፍርድ ባለዕዳው ከ17/09/2003 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ እንዲመልሰኝ የወሰነ ሲሆን የወረዳው ፍርድ ቤትም ወደ ሥራ እንድመለስ ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ውዝፍ ደመወዝ በሞድል 85 መልስ ሰጪው እንዲያይዝ ካደረገ በኋላ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ከ17/09/2003 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ መልስ ሰጪው ይመልሳት ይላል እንጂ ስለ ክፍያው በግልጽ የሚለው ነገር የለም በማለት ገንዘቡ እንዲለቀቅ ማዘዙ ተገቢ ባለመሆኑ ወደ ሥራ እንዲመለስ ከተወሰነበት ቀን አንስቶ ያለውን ውዝፍ ደመወዝ መልስ ሰጪው እንዲከፍል ይወሰንልኝ ብለዋል።
መልስ ሰጪ ድርጅትም ቀርቦ ባለመከራከሩ መልስ የመስጠት መብቱ የታለፈ ሲሆን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ቀደም ሲል በመ/ቁ. 28527 በቀን 17/09/2003 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የተሰጠውን ውሳኔ ከመረመረ በኋላ በውሳኔው ይግባኝ ባይዋ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ከመባሉ በስተቀር ከሥራ ከታገዱበት ከ17/09/2003 ዓ.ም. ጀምሮ ያለው ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፈላቸው ያልተወሰነ በመሆኑ ላከፈላቸው አይገባም በማለት የወረዳው ፍርድ ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ አጽንቷል።
የፍርድ ባለመብትም በስር ፍርድ ቤቶች ትእዛዝ/ውሳኔ ላይ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን ችሎቱም የግራ ቀኙን ወገን በማከራከር እንዲሁም የከፍተኛውን ፍርድ ቤት የሆነውን መዝገብ አስቀርቦ በመመርመር በአብላጫ ድምጽ በሰጠው ውሳኔ በመ/ቁ/28527 ተደርጎ በነበረው ክርክር አመልካች ተጠሪዋን ከሥራ በህገ ወጥ መንገድ ስለማሰናበቱ ካለማስረዳታቸውም ልላ ተጠሪውም አመልካችን አለማሰናበታቸውን ጠቅሶ በመከራከሩ ፍርድ ቤቱ በ24/01/2004 ዓ.ም.
በሰጠው ውሳኔ ከ17/09/2003 ዓ.ም. ወደ ሥራ እንዲመለሱ ሲወስን ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፈላቸው በግልጽ የወሰነው ነገር ባይኖርም ከ17/09/2003 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ሲል ውሳኔ መስጠቱ ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንጽ 43(5) ጋር ተገናዝቦ ሲታይ አንድ በህገ ወጥ መንገድ ከሥራ ተሰናብቷል በሚል ወደ ሥራ እንዲመለስ የሚወሰን ሰራተኛ በመጀመሪያ የሥራ ክርክር ችሎት እስከ 6 ወር ደመወዝ፣በይግባኝ የታዬ እንደሆነ ደግሞ እስከ አንድ ዓመት ውዝፍ ደመወዝ ላወሰን እንደሚችል የተደነገገ ሲሆን በዚህ በተያዘውም ጉዳይ የፍርድ ባለመብት ወደ ሥራ ከ17/09/2003 ዓ.ም. ጀምሮ ይመለሱ ተብሎ መወሰኑ ከዚሁ ቀን ጀምሮ ውሳኔ እስከተሰጠበት ቀን ማለትም እስከ 24/01/2004 ያለው ደመወዝ ተከፍሎአቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ የተወሰነ መሆኑን ስለሚያስገነዝብ ከ17/09/2003- 24/01/2004 ያለው ውዝፍ ደመወዝ ታስቦ ላከፈላቸው ይገባል በሚል የወረዳው ፍርድ ቤትና ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጡትን የትዕዛዝ /የውሳኔ ክፍል ሽሯል።
አመልካችም በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል የሰበር አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበ ሲሆን በዋናነት የጠቀሰው የቅሬታ ነጥብም፡ተጠሪ የሥራ ውል በህገ ወጥ መንገድ ተቋርጧል በሚል ክስ ቢያቀርቡም ይህንኑ በማስረጃ ያላረጋገጡ በመሆናቸው በአመልካች ህገ ወጥ ድርጊት ውሉ አልተቋረጠም በማለት ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመ/ቁ/28527 የሰጠውን ውሳኔ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም የህግ ስህተት የለበትም በሚል ካጸናው በኋላ በአፈጻጸም ወቅት ግን በውሳኔ ያልተገለጸውን ውዝፍ ደመወዝ አመልካች ላከፍል ይገባል ሲል መወሰኑ ተቀባይነት የለውም የሚል ነው።
ተጠሪዋ በበኩላቸው በሰጡት መልስ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመ/ቁ/28527 በሰጠው ውሳኔ ውሳኔው ከተሰጠበት ቀን በፊት ያለውን ጊዜ በመጥቀስ ከዚሁ ከተጠቀሰው ጊዜ ጀምሮ አመልካች ወደ ሥራ እንዲመለስ የወሰነው ያልተከፈለውን ውዝፍ ደመወዝ አመልካቹ እንዲከፍል በሚል ስለሆነ ውዝፍ ደመወዝ ላለመክፈል ሲል ያቀረበው ክርክር ተገቢ ባለመሆኑ ውድቅ ላሆን ይገባል ብለዋል። ተጠሪዋ ላቀረቡት መልስ አመልካች የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክሯል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- አመልካች ለተጠሪዋ ውዝፍ ደመወዝ ላከፍል ይገባል? ወይስ አይገባም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
አመልካችና ተጠሪን በዋናነት እያከራከራቸው ያለው ለአፈጻጸም ክሱ መነሻ የሆነው ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመ/ቁ/28527 በቀን 24/01/2004 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የሰጠው ፍርድ ነው።
በዚህ ፍርድም ተጠሪዋ ከ17/09/2003 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ከመወሰኑ በስተቀር ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፈላቸው በግልጽ አለመጠቀሱን የሥር ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት ጉዳይ ነው። አንድ የአፈጻጸም ክስ የቀረበበት ሰው ደግሞ ላገደድ የሚችለው እንዲፈጸም በቀረበው ፍርድ መሰረት መሆኑን ከፍ/ሥ/ሥ/ህግ ቁጥር 378 እና ከተከታይ ድንጋጌዎች መገንዘብ የሚቻል ነው። እንዲሁም ፍርዱን የሚያስፈጽም ፍርድ ቤት በፍርዱ ወይም በውሳኔው መሰረት ከሚያስፈጽም ውጪ በአፈጻጸም ጊዜ ዋናውን ፍርድ ላለውጥ የሚችልበት የህግ መሰረት አለመኖሩን ይህ ችሎት በሰበር መ/ቁ/29344 እና በልሎችም በርካታ መዝገቦች አስገዳጅ የህግ ትርጉም ሰጥቷል።
በዚህ በተያዘው ጉዳይም በዋናው ፍርድ አመልካች ወደ ሥራ ተጠሪዋን እንዲመልሳቸው ከመወሰኑ በተጨማሪ ውዝፍ ደመወዛቸውን እንዲከፍል የተወሰነ መሆን ስላለመሆኑ መመርመር የሚገባ ሆኖ ተገኝቷል። በመ/ በቀን 24/01/2004 ዓ.ም. በተሰጠው ፍርድ ተጠሪዋ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የተወሰነው ከ17/09/2003 ጀምሮ ነው። ፍርድ ቤቱ ፍርዱ ከተሰጠበት ከ24/01/2004 ዓ.ም. ጀምሮ ተጠሪዋ ወደ ሥራ እንዲመለሱ መወሰን የሚችል ቢሆንም ወደ ኋላ ያለውን ጊዜ ወስዶ ከ17/09/2003 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የወሰነው በዚህ ችሎት እምነት ለተጠሪዋ ከዚሁ ከ17/09/2003 ዓ.ም. ጀምሮ ያለው ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፈላቸው በሚል ነው። ምክንያቱም ፍርድ ቤቱ ውዝፍ ደመወዝ ለተጠሪዋ እንዲከፈላቸው ለመወሰን የማይገባ መሆኑን ቢያምን ኖሮ በ24/01/2004 በተሰጠ ፍርድ ከ17/09/2003 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የሚልበት ምክንያት ስለማይኖር ነው። በዚህ መልኩ የተሰጠውን ፍርድ ደግሞ አመልካች ውዝፍ ደመወዙን ለመከፈል በቂ ምክንያት የለም የሚል ከሆነ በይግባኝ አቅርቦ ሳያስለውጥ ከቀረ በኋላ በአፈጻጸም ወቅት ውዝፍ ደመወዝ በዋና ፍርድ ላይ አልተወሰነም ሲል መከራከሩ የፍርዱን ይዘት መሰረት ያደረገ ሆኖ አልተገኘም።
በመሆኑም ከዚህ በላይ በተገለጹት ምክንያቶች የተነሳ አመልካች ለተጠሪዋ ከ17/09/2003 ዓ.ም.ጀምሮ ያለውን ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፍል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአብላጫ ድምጽ የወሰነው ተገቢ ሆኖ በማግኘታችን በአብላጫ ድምጽ በውሳኔው ላይ የተፈጸመ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የለም በሚል ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
በቀን 28/12/2004 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በአብላጫ ድምጽ የሰጠውን ውሳኔ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት በአብላጫ ድምጽ አጽንተናል።
ለተጠሪዋ አመልካች ከ17/09/2003 ዓ.ም. እስከ 24/01/2004 ዓ.ም. ያለውን ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፍላቸው የክልሉ ሰበር ሰሚው ችሎት የወሰነው በአግባቡ ነው ብለናል።
የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራቸውን ይቻሉ ብለናል።
የማነበብ የሶስት ዳኞች ፊርማ አለበት የልዩነት ሐሣብ የፍርድ አፈፃፀም ሥርዓትን አመራር አስመልክቶ ከላይ ከፍ ሲል የተገለፀውን ፍርድ ለመስጠት የአብላጫው ድምፅ በሰጠው የሕግ ትርጉም ባለመስማማት በፍርዱ ላይ ስማችን በተራ ቁጥር 1 እና 5 ላይ የተመለከተው ዳኞች የፍርዱ አፈፃፀም ላመራ የሚገባበትን የተለየ የትርጉም መስመር እንደሚከተለው አስፍረናል።
ለዚህ የሰበር ጉዳይ መነሻ የሆነውን የመጨረሻ ፍርድ የኦሮሚያ ብ/ክ/መንግሥት ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአብላጫ ድምፅ በሰጠው ውሣኔ እንደምርኩዝ አድርጎ የጠቀሰው በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 43/5/ ድንጋጌ ለተያዘው ጉዳይ አግባብነት ያለው አይደለም። በእራሱ ፍርድ የአማርኛ ትርጉም ገጽ 2 የመጀመሪያው ፖራግራፍ ላይ እንደገለፀው ለአፈፃፀሙ መነሻ የሆነውን ጉዳይ ይግባኝ ሰሚው የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በይግባኝ ተመልክቶ በመ/ቁ. 28527 መስከረም 24 ቀን 2004 ዓ.ም ፍርድ ሲሰጥ የአሁን አመልካች ተጠሪን ሕገ- ወጥ በሆነ መንገድ ከሥራ አሰናብቷታል የሚለውን መሰረት በማድረግ አይደለም ይልቁንም የአሁን ተጠሪ በአሁን አመልካች ሕገ- ወጥ ድርጊት የተሰናበተች ስለመሆኑ በማስረጃ አላረጋገጠችም፤ አሰሪውም እኔ ከሥራ አላናበትኳትም በማለት መከራከሩን ሁሉ መሰረት አድርጎ ወደ ሥራዋ ትመለስ በማለት ነው። ይህም በመሆኑ የተነሣ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የአሁን ተጠሪ ወደ ሥራ ትመለስ የተባለችበትን ምክንያት ከይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ፍርድ የተገለፀውን እና በማስረጃ የተረጋገጠውን የፍሬ ነገር ጉዳይ በውል ካለመገንዘብ ለጉዳዩ ተፈፃሚነት አለው የሚለውን የአዋጁን አንቀጽ 43/5/ በመመርኰዝ ምክንያት ከተሳሳተ መነሻ ተነስቶ ወደ ተሳሳተ የፍርድ መደምደሚያ ላደርስ እንደቻለ የጉዳዩ አመጣጥ አስረጂ ነው።
ምናልባት ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት መስከረም 24 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም በዋለው ችሎት እየወሰነ የአሁን ተጠሪ ከግንቦት 17/2ዐዐ3 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራዋ ትመለስ ማለት ምን ማለት ነው?
ለሚለው አከራካሪ ነጥብ ከላይ የተመለከተውን የአዋጁን አንቀጽ 43/5/ ድንጋጌ ከጉዳዩ ጋር በማመሳሰል ለጉዳዩ ተፈፃሚነት እንዲኖረው አድርጎ ነው ከተባለም ይኸው የሰበር ሰሚ ችሎት ደረጃውን ጠብቆ በቀረበለት የአፈፃፀም ጉዳይ ላይ በአፈፃፀሙ ምክንያት የሆነውን የፍርድ ይዘት አድማስ በማስፋት እና ለጥጦ ለመትርጎምና ይህንኑ የተለጠጠ ትርጉም ሁሉ ጨምሮ ፍርድን ለማስፈፀም የሚያስችል ሥልጣን በአገራችን የህግም ሆነ የዳኝነት አመጣጥ ሥርዓት አልተዘረጋም።
ይልቁንም የአንድ ፍርድ ይዘት አሻሚ ሆኖ እንደ አሁኑ ያለውን ክርክር እንዳያስነሳ ሙግት ተከናውኖ ካበቃ በኋላ ፍርድ እንድት ላሰጥ እንደሚገባው እና ምን ምን ሁኔታዎችን ማካተት እንዳለበት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 182 እና 183 በግልፅ ተደንግጓል። ይህም ፍርድ ላሰጡ የሚችሉት ፍ/ቤቶች ዋናውን ጉዳይ ተመልክተውና አከራክረው በጉዳዩ ላይ ዳኝነት በመስጠት በጎንዮሽም ሆነ ከታች ወደ ላይ በተዘረጋው የፍርድ ቤቶች አወቃቀር በቀጥታም ሆነ በይግባኝ ጉዳዩን ለማየት የሥረ ነገረ ሥልጣን ያላቸው ፍ/ቤቶች ናቸው።
በዚህ አኳኋን የተሰጠን ፍርድ በማስፈፀም ረገድ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 378 እና 372 መሰረት ሥልጣን ያላቸው የአፈፃፀም ችሎቶች ስለ ፍርድ አፈፃፀም የተዘረጉትን ሥርዓቶች በመከተል እንደ ፍርዱ ከመፈፀም በቀር የአንድ ፍርድ ይዘትን በመመልከት የፍርዱን ይዘት አድማስ በማጥበብም ሆነ በማስፋት ረገድ ፍርድን የመተርጎም ሥልጣን አልተሰጣቸውም።
በዚህ ረገድ በኦሮሚያ ክልል የአዳሜ ቱሉ ወረዳ ፍ/ቤት እና ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በቀረበላቸው ጉዳይ “ፍርዱ” የአሁን ተጠሪ ከግንቦት 17 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ አሰሪው ወደ ሥራዋ ይመልሣት በሚል በግልፅ ከመቀመጡ በቀር ከውዝፍ ደሞወዝ ጋር በሚል ስላልተወሰነ ከፍርዱ ይዘት አድማስ በመሻገር ለማስፈፀም የሚያስችል ሥልጣን የለንም በማለት የሰጡት ትርጉም የፍርድ አፃፃፍ ሥርዓት በየትኛው ፍ/ቤት እንደሚከናወንና የአፈፃፀም ችሎት ሥልጣን ውሉን እስከምን እንደሆነ ስለአፈፃፀም ሥርዓት አመራር የተመለከቱትን ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገ ሆኖ አግኝተነዋል።
በአኳያው የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በቀረበለት የአፈፃፀም መዝገብ ላይ ፍርዱ ከተሰጠበት ዕለት ወደ ኋላ በመመለስ ሰራተኛው ወደ ሥራ ትመለስ በማለት መወሰኑ /መፈረዱ ትመለስ ከተባለቺበት ዕለት ጀምሮ ውሣኔ እስከተሰጠበት ድረስ ያለው ውዝፍ ደመወዝ ይከፈላት ለማለት ካልሆነ በቀር የተለየ ትርጉም ላሰጠው አይችልም በማለት ለአፈፃፀሙ መነሻ የሆነውን የፍርድ ይዘት በማስፋት የሰጠው ትርጉም ከላይ በዝርዝር እንደተመለከተው በሕግ ባልተሰጠው ሥልጣን ከመሆኑም በላይ ይህ ዓይነት የአተረጓጎም መስመር ስለዋናው ጉዳይ ፍርድ አሰጠጣጥ እና ፍርዱን ስለማስፈፀም ሥርዓት አስመልክቶ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕጉ ጉዳዮች በሥርዓት እንዲመሩ በማድርግ በአፋጣኝ እና በአነስተኛ ጊዜና ወጭ እንዲቋጩ ማድረግን ታሳቢ አድርጐ የያዘውን ዋነኛ ዓላማ የሚንድ፤ ይህን ዓይነት የአተረጓጉም መስመር ከተከተልን ዳር ድንበር ለልለው ሙግት ተከራካሪ ወገኖችን የሚዳርግ የሙግት አመራር ሥርዓትን የሚያፋልስ የአገሪቱ የፍርድ አሰጣጥ እና የአፈፃፀም ሥርዓት ተገማች እንዳይሆን ላያደርግ የሚችል በመሆኑ ከህጉም ሆነ ከየትኛውም መመዘኛ አንፃር ከቶውንም ተቀባይነት ያለው አይደለም።
በተለይም በኢትዮጵያ ፍድራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብላክ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 8ዐ(3)(ሀ) እና ይህንኑ ሕገ መንግስትዊ ድንጋጌ ለመስፈፀም በወጣው ዝርዝር ሕግ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 1ዐ ስለፍድራል ሰበር ሰሚ ችሎት ሥልጣን መደንገግ ያስፈለገበት ዋነኛ የሕጎች መነሻ የአገሪቱን ሕጐች በማስፈፀምም ሆነ በመተረጐም ረገድ ወጥ የሆነ አሰራር እንዲሰፍን ለማድረግ በመሆኑ ይህም ስለመሆኑ እነዚህ ሕጐች ከወጡ በኋላ የፍድራል ሰበር ሰሚ ችሎት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት የሚሰጠው ትርጉም በየትኛውም ደረጃ በሚገኝ የዳኝነት አካል ላይ የአስገዳጅነት ባህሪ ይኖረዋል በሚል በአዋጅ ቁጥር 454/97 የተደነገገው አስረጅ ነው።
ከእነዚህ ሕጐች አንፃር የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንደ አሁኑ ያለ አጠቃላይ የፍርድን አመጣጥና የአፈፅፀም ሥርዓት የሚመለከት ጉዳይ በሁለት ተከራካሪ ወገኖች ክርክር መነሻ ሲቀርብለት በዚህ ዓይነት ጉዳይ በተሰጠ የመጨረሻ ፍርድ ላይ የተፈፀመን መሰረታዊ የሕግ ስህተት በማረም ለእነዚህ ተከራካሪ ወገኖች ሕጉን መሰረት ያደረገ ዳኝነት ከመስጠቱ ባሻገር ዐበይት ተግባሩ ወደ ፊት ይህን መሰል ክርክር ቢነሳ ሕጉን መሰረት ያደረገ ትርጉም በመስጠት ወደ ፊት ለሚነሱ ተመሳሳይ ጉዳዮች ትርጉሙ ተፈፃሚ እንዲሆን በማድረግ ወጥ የሆነ የአሰራር ሥርዓት ለማስፈን እንጂ የአፈፅፀም ጉዳይን እየተመለከተ ያለ ፍርድ የአፈፃፀም ፍ/ቤት እንደ አግባብነቱ ለፍርዱ ትክክለኛ ትርጉም በመስጠት ፍርዱን በተሟላ መንገድ የማስፈፀም ሥልጣን አለው የሚለው ትርጉም ሕጋዊ መሰረት የልለው ከመሆኑም በላይ ዋናውን ጉዳይ በሚመለከት አይተውና ሰምተው ፍርድ ለመስጠት የሚችሉትንና እንደፍርዱ የሚያስፈፅሙትን ችሎቶች ሥልጣን የሚቀላቅል፣ የሚተረጐም ፍርድ አለ የለም? የሚተረጐምስ ከሆነ እንድት ይተርጐም የሚሉትንና ለመሳሰሉት ወሰን ለልላቸው ክርክር የሚጋብዝ፤ የአፈፃፀምን ጉዳይ በዘፈቀደ እንዲመራ የሚያደርግ እንጅ የፍርድ አሰጣጥና የፍርድ አፈፃፀም በሥርዓት እንዲመራ በማድረግ ወጥ ለሆነ የሕግ አፈፃፀም እና አተረጓጐም እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑ ትርጉም ሕጉንና ሕጐችን ለማውጣት ያስፈለገበትን ግብና መነሻ ሐሳብ መሰረት ያደረገ አይደለም።
ስለሆነም በዚህ በተያዘው ጉዳይ ለአፈፃፀሙ ምክንያት የሆነውን ፍርድ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት መስከረም 24 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት የአሁን ተጠሪን አሰሪው ከግንቦት 17/2003 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራዋ ይመለሳት ሲል ፍርድ በመስጠቱ የተነሣ በአፈፃፀም ጊዜ ከግንቦት 17 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ፍርድ እስከተሰጠበት እስከ መስከረም 24 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም ያለውን ውዝፍ ደመወዝ ይጨምራል ወይስ አይጨምርም? ለሚለው ቀጥተኛ መልስ አይሰጥም፤ ፍርዱን ለማስፈፀም ያስቸግራል ውዝፍ ደመወዝ እንደተነፈገ ላቆጠርብኝ ይችላል? የሚለው በፍርድ ግልጽ አለመሆን የሚጐዳው ወገን ፍርዱንና ጠይቆት ከነበረው ዳኝነት ጋር በማነፃፀር በበላይ ፍ/ቤት እንዲታረም ከማድረግ በቀር።
እንዲሁም ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ከላይ በተገለፀው አኳኋን ፍርዱን ላሰጥ የቻለበትን ምክንያት በግራ ቀኙ ክርክርና ማስረጃ አንፃር እና ለጉዳዩ ተፈፅሚነት እና አግባብነት ካለው ሕግ ጋር በማገናዘብ ስለፍርዱ ይዘት አድማስ ተመልክቶ ተገቢውን ትርጉም ለመስጠት ሥልጣን ያላቸው ዋናውን ጉዳይ ሰሚው ከታች እስከ ላይ የተዋቀሩት ፍ/ቤቶች እንጂ ፍርዱን እንዲያስፈጽም የአፈፃፀም ክስ የቀረበለት ፍ/ቤት የፍርዱን ይዘት በማጥበብም ሆነ በማስፋት ረገድ ትርጉም ለመስጠት የሚያስችለው ሥልጣን ሰጭ ድንጋጌ እና ሥርዓት የለውም ከዚህ አንፃር የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ፍርድ መሰረታዊ የሕግ ስህተተ የተፈፀመበት ሆኖ ተገኝቷል በሚል ላተርጐም ይገባል የሚለውን የፍርድ ሐሳብ ሰጥተናል።
No topics extracted.