No summary available.
ሕዳር 21 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ተኽላት ይመስል አመልካች፡- የማኀበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ - የቀረበ የለም ተጠሪ፡- አቶ ታዬ አበራ - ታልፏል **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ አንድ የጡረታ መብት ተጠቃሚ የሆነ ሰው በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ ደመወዝ መቀበሉ ሲረጋገጥ የጡረታ መብት ተጠቃሚ መሆኑ የሚቀጥል መሆን ያለመሆኑን ጥያቄውን የሚያቀርበው ወገን ክሱን ቀሪ የሚያደርገው የይርጋ ዘመን መኖር ያለመኖሩን የሚመለከት ነው። ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች ባሁኑ ተጠሪ ላይ በጉጂ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው። የክሱ ይዘትም ባጭሩ፡- ተጠሪ በጡረታ መለያ ቁጥር ወ/515371 በሆነው ከግንቦት 01 ቀን 1984 ዓ.ም. ጀምሮ በየወሩ የጡረታ አበል እየወሰዱ ባለበት ሁኔታ ከሰኔ 01 ቀን 1989 ዓ/ም ጀምሮ በጉጂ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተቀጥረው የመንግስት ደመወዝና የጡረታ አበል በመቀበል ላይ መሆናቸውን ገልፆ ይህ የተጠሪ ተግባር በመንግስት ሰራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 209/1955 አንቀጽ 30(2) እና በመንግስት ሰራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 345/1995 አንቀጽ 46(1) መሰረት ሕጋዊ ያለመሆኑን ጠቅሶ ከሰኔ 01 ቀን 1989 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 1995 ዓ.ም. ድረስ በየወሩ ብር 105.00 የወሰዱት ለሰባ አምስት ወራት ያህል ተባዝቶ የሚመጣውን ውጤት ብር በድምሩ ብር 7,575.00 (ሰባት ሺህ አምስት መቶ ሰባ አምስት ብር) እንዲሁም ከሐምል 01 ቀን 1996 ዓ.ም. እስከ ሀምል 30 ቀን 1998 ዓ.ም. ድረስ በየወሩ ብር 115.50 የወሰዱት ታስቦ የሚመጣውን ድምር ብር 4,045.50 (አራት ሺህ አርባ አምስት ብር ከሀምሳ ሳንቲም) ከወጪና ኪሳራ እንዲሁም ከሕጋዊ ወለዱ ጋር እንዲከፍሉ ይወሰንለት ዘንድ ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው። የአሁኑ ተጠሪ ለክሱ በሰጡት መልስም ከጉጂ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጋር የፈፀሙት የቅጥር ውል መኖሩን ሳይክዱ የአመልካች የዳኝነት ጥያቄ በይርጋ ቀሪ ላሆን እንደሚገባ፣ መብቱ ቀሪ የሚሆነውም በአዲስ መልክ ሲቀጠሩ የሚያገኙት ደመወዝ ከብር 200.00 በላይ ከሆነ መሆኑን ጠቅሰው ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል። ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የአመልካች ክስ ተጠሪ ከተቀጠሩበትና የጡረታ አበል መቋረጥ ከሚገባበት ጊዜ ጀምሮ ሲታሰብ ከአስራ ሁለት አመታት በላይ ቆይቶ የቀረበና ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1677 እና 1845 ድንጋጌዎች አኳያ ሲታይ ተገቢነት የልለው መሆኑን ጠቅሶ ክሱን ውድቅ አድርጎታል። በዚህ ብይን አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለኦሮሚያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ አመልካች ዳኝነት እየጠየቀ ያለው ያለአግባብ የተከፈለውና ተጠሪ የበለፀጉበትን ገንዘብ ነው የሚል ምክንያት ይዞ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው የይርጋ ዘመን በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2143(1) ስር የተመለከተው መሆኑን ገልጾ የአመልካችን ክስ በሁለት አመት ይርጋ ቀሪ ነው በማለት ወስኗል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ሲሆን የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ለጉዳዩ ይርጋ የልለው መሆኑን በመጥቀስ ተጠሪ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥረው ደመወዝ እየተቀበሉ ባሉበት ጊዜ የተቀበሉትን የጡረታ አበል ላመልሱ አይገባም ተብሎ መወሰኑ የአዋጅ ቁጥር 209/1955 አንቀጽ 30(2) እና አዋጅ ቁጥር 345/1995 አንቀጽ 46(1) ድንጋጌዎችን ባላገናዘበ መልኩ በመሆኑ ውሳኔው ላታረም የሚገባው ነው የሚል ነው።
አቤቱታው ተመርመሮም ተጠሪ ያላግባብ የተከፈለውን ገንዘብ ይመለስልኝ በማለት አመልካች ያቀረበው ክስ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2143(1) ድንጋጌ መሰረት በሁለት አመት ይርጋ ይታገዳል ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ባለመቅረባቸው በጽሑፍ መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፏል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የበታች ፍርድ ቤቶች የአመልካችን የዳኝነት ጥያቄ ውድቅ ለማድረግ መሰረት ያደረጉት የአዋጅ ቁጥር 345/1995 አንቀጽ 46/1/2/ የጡረታ አበል አመላለስን በተመለከተ የይርጋ ጊዜ የለውም በሚል መነሻ በልሎች ሕጐች ያሉትን የይርጋ ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ ነው። በእርግጥ የአዋጅ ቁጥር 209/1955 እና አዋጅ ቁጥር 345/1995 ስር ያሉት ድንጋጌዎች ከሕግ ውጪ የተከፈለ የጡረታ ገንዘብ ይመለስ ጥያቄ መቅረብ ያለበትን የጊዜ ገደብ አላስቀመጡም። ይህ ማለት ግን ጥያቄው የሚቀርብበት ጊዜ ገደብ የለውም ወደሚለው ድምዳሜ የማያደርስ ስለመሆኑ ከይርጋ ፅንሰ ሀሳብ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። ለጉዳዩ ቀጥተኛ ተፈጻሚነት ያለው ሕግ ስለ ይርጋ የጊዜ ገደብ በግልፅ ያስቀመጠው ድንጋጌ ከልለ በአገራችን የሕግ ስርአት የተዘረጋው መፍትሕ በውል ሕጉ የተመለከቱት ደንቦች የሚፈፀሙ መሆኑን የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1677(1) እና 1845 ድንጋጌዎች ያሳያሉ። ያላግባብ መበልፀግን በተመለከተ የሚደነግጉ ድንጋጌዎች የይርጋ ደንብ የይርጋ ጊዜን በተመለከተ ቀጥተኛ ተፈጻሚነት ያለው ሕግ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ከልለ ተፈፃሚ የሚሆንበትን አግባብ የሚያሳይ ድንጋጌ የለም። በመሆኑም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ክፍያው ያላግባብ ተወስዷል የሚል ነው በሚል ምክንያት የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2143(1) ድንጋጌን ለጉዳዩ ተፈጻሚነት አለው በማለት የስር ፍርድ ቤት ያስቀመጠውን ድንጋጌ መለወጡ የሕግ መሰረት ያለው ሁኖ አልተገኘም። የስር ፍርድ ቤት የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1677 እና 1845 ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ በአስር አመት የይርጋ ጊዜ ጉዳዩ መታየት እንደአለበት የሰጠው ምክንያት ተገቢ ሁኖ የተገኘ ቢሆንም የስር ፍርድ ቤት ይርጋው መቆጠር የሚጀመርበትን ጊዜ በተመለከተ ግን ተጠሪ ከተቀጠሩበት ከሰኔ 01 ቀን 1989 ዓ/ም ጀምሮ ነው በማለት የወሰደው ተገቢ ሁኖ አልተገኘም። ምክንያቱም ተጠሪ የጡረታ አበሉንና በቅጥር የሚያገኙትን ደመወዝ በአንድ ላይ መቀበሉን በተከታታይ ሲፈጸሙበት ቆይተው ገንዘቡን ከሕግ ውጪ ሲቀበሉ የቆዩ መሆኑን አመልካች በማረጋገጥ የጡረታ አበሉን ለተጠሪ መክፈል ያቆመው ከነሐሴ 30 ቀን 1998 ዓ/ም ጀምሮ ሲሆን ተጠሪ ከሕግ ውጪ የወሰዱትን የጡረታ አበል እንዲመልሱ ክስ ያቀረበው ጥቅምት 18 ቀን 2003 ዓ/ም ነው። ስለሆነም የይርጋ ጊዜው መቆጠር ያለበት ክሱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን አቆጣጠሩም መሆን ያለበት ወደኋላ ነው። እንዲህ ከሆነ ክሱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ኋላ ሲቆጠር አስር አመት ያላለፈበት የጡረታ ገንዘብ ክፍያ ለአመልካች ላመለስ የሚገባው ይሆናል። አመልካች የይርጋው መቆጠር ያለበት በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1847 መሰረት ነው በማለት ያቀረበው ክርክር በየጊዜው የሚከፈለውን ገንዘብ የሚቀበል ሰው ክፍያው ሲቋረጥ መብቱን ለማስከበር የሚችልበትን የይርጋ ጊዜ ለመቁጠር የሚያስችለውን አግባብ የሚያሳይ በመሆኑ በተያዘው ጉዳይ ላይ አመልካች ክፍያ ተቀባይ ሳይሆን ከሕግ ውጪ የከፈለውን ገንዘብ እንዲመለስለት የሚጠይቅ በመሆኑ ቀጥተኛ አግባብነት ያለው ሁኖ አላገኘነውም።
ክሱ ከተመሰረበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ኋላ አስር አመት ያላለፈውን የጡረታ ገንዘብ መኖር ያለመኖሩን ስንመለከት አመልካች ገንዘቡ እንዲመለስ የጠየቀው ከሰኔ 01 ቀን 1989 ዓ.ም.
ጀምሮ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 1995 ዓ/ም በብር 105 ሂሳብ ለሰባ ወራት ይህል፣ እንዲሁም ከሐምል 01 ቀን 1996 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሐምል 30 ቀን 1998 ዓ/ም ድረስ ደግሞ ለሰላሳ አምስት ወራት ያህል በየወሩ ብር 115.50 የተከፈለውን የጡረታ አበል ክፍያ ነው። ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ከጥቅምት 18 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ኋላ አስር አመት ሲቆጠር አስር አመት የማይልፍበት የጡረታ አበል ክፍያ ከጥቅምት 19 ቀን 1993 ዓ.ም. ወዲህ ያለው ነው። በመሆኑም ከጥቅምት 18 ቀን 1993 ዓ/ም ጀምሮ ወደ ኋላ ያለው ማለትም ከሰኔ 01 ቀን 1989 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 18 ቀን 1993 ዓ/ም ድረስ ያለው የጡረታ አበል አስር አመት ያለፈበት በመሆኑ የአመልካች ጥያቄ ውድቅ ላሆን የሚገባው ሁኖ አግኝተናል። የይርጋው ጊዜ ያላለፈ መሆኑ ከተረጋገጠ ደግሞ ፍሬ ነገሩ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለማድረግ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 341(1) በሚያዘው መሰረት ጉዳዩን ለስር ፍርድ ቤት መመለስ የሚቻል መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ይህንኑ ለመፈፀም ግን ተከሳሽ በስር ፍርድ ቤት በማስረጃ የሚነጥር የፍሬ ነገር ክርክር ማቅረባቸውን ያለማቅረባቸውን ከፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕጉ አይነተኛ አላማ ጋር አገናዝቦ ማየቱ ተገቢ ይሆናል። በመሆኑም ከዚህ አንፃር የተጠሪን ክርክር ስንመለከተው የፍሬ ነገር ክርክር ሳይሆን የሕግ ክርክር በመሆኑ ለዚህ ነጥብ ሲባል ጉዳዩን ለስር ፍርድ ቤት መመለሱ ከውጪ፣ ጊዜና ጉልበት አንፃር ተገቢ ሁኖ ስላልተገኘ የሕግ ጥያቄውን በዚህ ችሎት እልባት መስጠቱ ስነ ስርዓታዊ ሁኖ አግኝተናል።
ቀጥሎ መታየት ያለበት ጥያቄ ተጠሪ ለአመልካች ላመልሱት የሚገባው የጡረታ አበል ክፍያ መጠን ምን ያህል ነው? የሚል ነው።
በቅድሚያ ተጠሪ በቅጥር የሚያገኙት ደመወዝ ከ200.00 በታች በመሆኑ የጡረታ አበሉን ለመመለስ በሕግ እንደማይገደዱ ገልፀው ያቀረቡትን ክርክር ማየቱ ተገቢ ይሆናል።
በመሰረቱ በዚህ ጉዳይ ክስ የተመሰረተው ጥቅምት 18 ቀን 2003 ዓ.ም. በመሆኑ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው አዋጅ ቁጥር 345/1995 ከመሆኑም በላይ በአዋጅ ቁጥር 209/1955 እና 345/1995 የተፈጠሩ ህጋዊ ሁኔታዎች በአዋጅ ቁጥር 714/2003 መሰረት ጥበቃ ላደርግላቸው እንዲሚገባ በአዋጁ አንቀጽ 59(1) ስር ተመልክቷል። የአዋጅ ቁጥር 209/1995 አንቀጽ 30/2/ እና የአዋጅ ቁጥር 345/1995 አንቀፅ 52(1) ድንጋጌዎች አንድ ላይ ሲነበቡ ደግሞ አንድ የመንግሥት ሰራተኛ ጡረታ ከወጣ በኋላ መልሶ ደመወዝ በሚያስገኝ የመንግሥት ሥራ ከተቀጠረ ከደሞዙ እና ከጡረታ አበሉ አንዱን መምረጥ እንደሚኖርበት በግልጽ ደንግጎ ይገኛል። ይህ ድንጋጌ ሥራው ደሞዝ የሚያስገኝ የመንግሥት ሥራ መሆኑን እንጂ የቅጥሩ ሁኔታ በጊዜያዊነት ይሁን በቋሚነት እንዲሁም ደመወዙ ከጡረታ አበል ያነሰ ይሁን የበለጠ የሚል መስፈርት ከግምት ውስጥ አያስገባም። የአዋጅ ቁጥር 345/1995 አንቀጽ 46(1) ሲታይም የአገልግሎት የጡረታ አበል በመቀበል ላይ ያለ ባለመብት እንደገና በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ ደመወዝ ማግኘት ከጀመረ የጡረታ አበሉ ይቋረጣል በማለት በአስገዳጅነት ያስቀመጠ ሲሆን ሕጉ ቅጥሩ ቋሚ ይሁን ጊዜያዊ ወይም በኮንትራት ስራ እንዲሁም በቅጥር የተገኘው ደመወዝ መጠንን አነስተኛ መነሻ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም። የሕጉ ግልጽ አነጋገር የጡረታ ባለመብቱ እንደገና በልላ መንግስታዊ ስራ ተቀጥሮ ከጡረታ ገንዘብ በተጨማሪ ልላ ደመወዝ ካገኘ የጡረታ መብቱ የሚቆም መሆኑን ነው የሚያሳየው። በመሆኑም ደመወዝ የሚያስገኝ መንግስታዊ ቅጥር እስከተፈጸመ ድረስና ሕጉ ያስቀመጠው የቅጥር አይነትና የደመወዝ መጠን ልዩነት እስከልለ ድረስ ሕጉ ተግባራዊ ላደረግ የሚገባው ለማንኛውም የቅጥር ዓይነትና የደመወዝ መጠን እንጂ ለአነስተኛ ደመወዝ ላሆን አይገባም ላባል የሚችልበት አግባብ የለም። የሕጉ መንፈስ ይህ ስለመሆኑም ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ቤትን የሚያስገድድ የሕግ ትርጉም በመ/፣ በሰ/መ/ እና በልሎች በርካታ መዛግብት ሰጥቷል። በመሆኑም ይህ ጉዳይም በዚህ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መሰረት መታየት ያለበት በመሆኑ ተጠሪ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥረው ደመወዝ ማግኘታቸው እስከተረጋገጠ ድረስ ደመወዙ ከብር 200.00 በታች ነው በማለት በስር ፍርድ ቤት ያቀረቡት ክርክር ሕጋዊ መሰረት ያለው አይደለም። ይህ ውጤት የሚኖረው የጡረታ አበል ወይም ደመወዝ ከሁለት አንዱን በመመረጥ ለመመለስ ነው እንጂ በጠቅላላው አመልካች ጥያቄውን ለማቅረብ ለመከልከል አይደለም። ተጠሪ ከሰኔ 01 ቀን 1989 ዓ.ም. ጀምሮ ተቀጥረው ሲያገኙት የነበረው ደመወዝ ከጡረታ አበል ያነሰ ስለነበር ይህንኑ ለመመለስ የሚፈልጉ መሆኑን ገልጸው አልተከራከሩም። በመሆኑም ተጠሪ ላመልሱ የሚገባው የጡረታ አበሉን መሆኑን ከክርክሩ ሂደት ተገንዝበናል።
እንግዲህ ተጠሪ የጡረታ አበሉን መመለስ አለባቸው ከተባለ መጠኑ ላለይ የሚገባው ነው።
በዚህም መሰረት ከሐምል 01 ቀን 1996 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሐምል 30 ቀን 1998 ዓ.ም.
ድረስ ያለው የጡረታ አበል ገንዘብ መጠኑ ብር 4,042.50 ሲሆን ይህ ጊዜ ከላይ በተመለከተው የይርጋ ጊዜ አቆጣጠር የአስር አመት የማይልፈበትን ጊዜ በግልጽ ያካተተ በመሆኑ እንዳለ ላያዝ የሚገባው ሲሆን ከ1/10/1989 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 30/12/1995 ዓ.ም.
ባለው ጊዜ ተጠሪ የተቀበሉት ብር 7,575.00 ግን የአስር አመት ጊዜ የሚልፈበትን ጊዜ አካትቶ የተሰራ በመሆኑ ይሕው ጊዜ ላለይ የሚገባው ነው። በዚህም አግባብ ከ01/10/1989 እስከ ጥቅምት 1993 ዓ.ም. ድረስ ያለው የአርባ ወራት የጡረታ አበል መጠኑ በወርሃዊ የጡረታ አበል ብር 105.00 ሲታሰብ ብር 4,200.00 (አራት ሺህ ሁለት መቶ ብር) የሚመጣ በመሆኑ ይኼው ገንዘብ በአስር አመት ይርጋ ላታገድ የሚገባው ሁኖ ቀሪው ከሕዳር 01 ቀን 1993 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 1995 ዓ.ም. ድረስ ለሰላሳ ሶስት ወራት ለተጠሪ የተከፈለው ገንዘብ ብር በወር ብር 105 ሲታሰብ ብር 3,465.00 (ሶስት ሺህ አራት መቶ ስልሳ አምስት ብር) በይርጋ የሚታገድ ባለመሆኑ ለአመልካች ተጠሪ ላመለሱት የሚገባ ሁኖ ተገኝቷል።
ሲጠቃለልም ለጉዳዩ ተፈፃሚነት ያለው ይርጋ የአስር አመት ጊዜ በመሆኑና ይህ ጊዜ መሰረት ተደርጎ ሲሰላም አመልካች ከተጠሪ ላመለስለት የሚገባው የገንዘብ መጠን በድምሩ ብር 7,665.00 (ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ አምሰት ብር) ሁኖ ተገኝቷል። በመሆኑም በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተሰጠው ውሳኔ ሙሉ በሙሉ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሲሆን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ደግሞ የድምዳሜ ክፍሉ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስለአገኘን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
ው ሣ ኔ
ተሰጥቶ በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ ሰኔ 14 ቀን 2003 ዓ.ም. ምክንያቱ ተለውጦ የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል።
ለጉዳዩ አግባብነት ያለው የይርጋ ዘመን በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1677(1) እና 1845 ድንጋጌዎች መሰረት አስር አመት ነው ብለናል።
ተጠሪ ከክሱ ከተጠቀሰው ገንዘብ ውስጥ የአስር አመት ይርጋ ያላለፈውን ብር 7,665.00 (ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ አምስት ብር) ከሕግ ውጪ የወሰዱት በመሆኑ ለአመልካች ላመልሱ ይገባል ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር ግራ ቀኙ ወጪና ኪሣራ ይቻቻሉ ብለናል።
No topics extracted.