No summary available.
ጥቅምት 8 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- ወሰኔ የህክምና አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አልቀረቡም ተጠሪ፡- ዶ/ር ክብረወሰን አለማየሁ አልቀረቡም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት የቀረበውን አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ክርክር ነው።
የክርክሩ መነሻ ተጠሪ አመልካች ከህግ ውጭ የሥራ ውልን ያቋረጠ ስለሆነ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ መሰረት የተለያዩ ክፍያዎችን እንዲከፍል ይወሰንልኝ በማለት ስላመለከተ ነው።
አመልካች ተጠሪ በተደጋጋሚ ሰዓት የማያከበር፣ ከታካሚዎች ጋር ጠብ የሚፈጥር በመሆኑ ከሥራ ተሰናብቷል ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት ተከራክሯል። የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ምስክሮች ከሰማ በኃላ ተጠሪ የተካሚዎችን የግል ሚስጥር ለሶስኛ ወገኖች አላግባብ የሚገልጽና የሙያ ሚስጥር የማይጠበቅ መሆኑ፣ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ከሚመጡ ታካሚዎች ጋር ጠብ መፍጠሩና ሰዓት ስለማያከብር ታካሚዎች ለካርድ የከፈሉትን ገንዘብ አስመልሰው የሄዱ መሆናቸው ተመስክሮበታል። ተጠሪ ይህንን በመከላከያ ማስረጃ አላስተባበለም። ስለዚህ ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት ወስኗል። ተጠሪ በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል። የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ተጠሪ በተደጋጋሚ የሥራ ሰዓት ባለማክበሩ በሥራው ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሷል የሚለውን አተረጓጎም የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1) ሀ እና (ለ) አቀራረጽና ይዘት የተከተለ አይደለም። የህክምና ዲስፕላንን አለማክበር በሥር ውላቸው በግልጽ ካልተመለከተ በስተቀር የሥራ ውል ለማቋረጥ የሚያስችል ምክንያት አይደለም በማለት የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትን ውሣኔ ሽሮታል።
አመልካች የካቲት 9 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ የድርጅቱን መልካም ስምና ጥቅም ላይ ጉዳት ማድረሱ በማስረጃ ተረጋግጧል። ተጠሪ የሙያ ስነ ምግባር በማክበር ሥራውን የማከናወን ግድታ አለበት። ነገር ግን ከሙያ ሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ተግባራትን እንደፈፀመ ተረጋግጦ እያለ የሥራ ውልን ለማቋረጥ ህጋዊ ምክንያት አይሆንም በማለት የተሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት አመልክተዋል። ተጠሪ አመልካች ያቀረበቸው ምክንያቶች የሥራ ውልን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ በቂ አይደሉም የሚል ይዘት ያለው መልስ ሰኔ 20 ቀን 2004 ዓ.ም የተፃፈ መልስ አቀርበዋል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የተደረገው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠው የህግ ትርጉምና ውሣኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም?
የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል። ጉዳዩን እንደመረመርነው ተጠሪ የህክምና ሙያ ሥነ ምግባር ደንብን በመተላለፍ በአመልካች የህክምና ተቋም የህክምና አገልግሎት ያገኙ ታካሚዎችን ሚስጥር የሚገልጽ ስለመሆኑ አመልካች በሥር ፍርድ ቤት ባቀረበው የሰው ማስረጃ ተረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ለምርመራ የቀረቡለትን ተካሚዎች የተሳደበ መሆኑንና ከታካሚዎች ጋር ጠብ የፈጠረ መሆኑ በወቅቱ በታካሚነት ቀርበው የነበሩ ሰዎች የምስክርነት ቃላቸውን በሥር ፍርድ ቤት ሰጥተዋል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች ተጠሪ የህክምና ሙያ ሥነ ምግባር ደንብ በመተላለፍ በአመልካች መልካም ስምና ጥቅም ላይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን ለማስረዳት ያቀረበውን ማስረጃ ሲመዘን የሥር ፍርድ ቤት ስህተት ሰርቷል የሚል የፍሬ ጉዳይ የማስረጃ ምዘና ድምዳሜ የልለው መሆኑን ከይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሣኔ ተረድተናል።
በተለይም ተጠሪ የአመልካቹ ሰራተኛ ሆኖ ሲሰራ ያገኘውን የአመልችን ደንበኞች ምስጥር ለማይመለከታቸው ሶስተኛ ወገኖች የሚገልጽ መሆኑና የሥራ ውሉ ላቋረጥ አካባቢ የአመልካችን አንዲት ደንበኛ ስም በመግለጽ ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ አለባት ብሎ ለሶስተኛ ወገን ሲገልጽ የሰማች መሆኑን የአመልካች ምስክርና የተጠሪ የሥራ ባልደረባ አስረድታለች።
የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ አመልካች ሄደው ተጠሪ እንዲመረምራቸው ቀርበው የነበሩ ታካሚዎች ተጠሪ የሰደባቸውና በማበሳጨት ለጠብ ጋብዟቸው የነበረ መሆኑን በማረጋገጥ የመስከሩ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት ወደ አመልካች የህክምና አገልግሎት ለማግኘት መሄዳቸውን እንዳቆሙ መስክረዋል። ከላይ የተገለፀው ይዘት ያለውን የአመልካች ምክስሮች ቃል ታዓማኒነትና ክብደት ያለው መሆኑን ማስረጃ የመመርመርና የመመዘን ስልጣን ባለው የሥር ፍርድ ቤት ተረጋግጧል። ይግባኝ ሰሚው የከፍተኛው ፍርድ ቤትም የአመልካች ምስክሮች ቃል ታዓማኒነት እና ክብደት የልለው ነው የሚል ውሣኔ አልሰጠም። የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም በአመልካች ምስክሮች የተረጋገጠውን ፍሬ ጉዳይ እውነትነት ያላቸው ቢሆኑም የሥራ ውል ለማቋረጥ የሚያስችል አይደለም በሚል ምክንያት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ ለውጦታል።
ተጠሪ የአመልካች ደንበኞች ታካሚዎችን የግል ሚስጥር መግለፁና የህክምና አገልግሎት ለማግኘት የመጡ ታካሚዎችን መሣደቡ የአመልካች ምስክሮች የሰጡት ቃል ታዓማኒነትና ክብደት ያለው ማስረጃ መሆኑ አከራካሪ ባልሆነ፣ እነዚህ ተጠሪ በሥራ ሂደት ፈፀማቸው የተባሉ ጥፋቶች የሥራ ውልን ለማቋረጥ የሚያስችሉ ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለው ነጥብ አመልካች ከሚሰጠው የህክምና ግልጋሎት ባህሪና ካለበት ኃላፊነት፣ ተጠሪ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ህግና በሙያ ሥነ ምግባር ደንቡ ከተጣበለት ግድታና ኃላፊነት እንደዚሁም የተጠሪ አድራጐት በአመልካች ላይ ከሚያስከትለውን ጉዳት አንፃር መመዘን ያለበት ነው።
ማንኛውም ሰራተኛ በስራ ውሉ ላይ የተመለከተውን ሥራ ራሱ የመሥራትና በሥራ ውሉና በሥራ ደንቡ መሰረት በአሰሪው የሚሰጠውን ትእዛዝ የመፈፀም ግድታ እንዳለበት በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ (1) እና (2) በግልጽ ተደንግጓል። ይህም ተጠሪ የተመደበበትን የህክምና ሥራ ሲሰራ ለሙያ ሥነ ምግባር ደንቦች ተገዥ በመሆን፣ ህሙማኑን በአክብሮት ማነጋገርና የማስተናገድ እንደዚሁም የህሙማኑን የግል ሚስጥር የመጠበቅ ግድታ እንዳለበት ተጠሪ ይህንን የሙያ ሥነ ምግባርና ደንብ የማስከበርና በአመልካች ድርጅት ውስጥ በሰራተኝነት ከቀጠለ አመልካች የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ የተሰጠውን ፈቃድ ለማሣገድ ወይም ለማሰረዝ የሚችል ምክንያት ስለመሆኑ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 174/1986 ዓ.ም አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ ይዘት ለመረዳት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪ የአመልካችን ደንበኞች የግል ሚስጥር አለመጠበቁና ለማይገባቸው ሶስተኛ ወገኖች መግለፁ እንደቀላል ጥፋት የማይታይና በወንጀል ተጠያቂነት ላያስከትል የሚችል የወንጀል ድርጊት መሆኑን ከወንጀል ህጉ አንቀጽ 399 እና አንቀጽ 400 ድንጋጌዎች ይዘት ለመረዳት ይቻላል።
ተጠሪ የአመልካች ሰራተኛ ሆኖ ሲሰራ እንደፈፀማቸው የተረጋገጡት ድርጊቶች በውጤት ደረጃ የአመልካችን መልካም ስምና ዝና በማጉደል ፈቃድ ባገኘበት የህክምና አገልግሎት የመስጠት የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዳይሆን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ አመልካች ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ ካልወሰደ ለአመልካች ከመንግስት የተሰጠውን ፈቃድ ላያሣግድ ወይም ላያሰርዝ የሚችል ጥፋት መሆኑን ከላይ ከገለጽነው የደንብ ቁጥር 174/4986 ድንጋጌ ይዘት ለመረዳት ይቻላል። በመሆኑም ተጠሪ የፈፀማቸወ ጥፋቶች በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1(ረ) መሰረት በሚያክማቸው ህሙማንን የመሣደብና የጠብ ጫሪነት ተግባር የፈፀመ መሆኑ የሚያሣዩና፣ የህክምና ሙያ ሥነ ምግባር ደንብን በመጣስ፣ የአመልካችን መልካም ሥምና ዝና እንደዚሁም ጥቅምና ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራት ናቸው። የአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1(ሸ) ድንጋጌም አመልካች ከሚሰጠው የህክምና ግልጋሎት ልዩ ባህሪና ተጠሪ ከሚጠበቅበት ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ብቃት አንፃር ባለማክበሩ፣ በአመልካች ላይ የደረሰውን ወይም ላያደርስ የሚችለውን ጉዳት በማያሻማ ሁኔታ መተርጎም ያለበት መሆኑን ከአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ዓላማ ከድንጋጌው ይዘትና ስለህክምና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ የወጡ የህግ ማእቀፎችን ይዘት በመመርመር ለመገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም ተጠሪ የፈፀማቸው ጥፋቶች በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1(ረ) እና (ሸ) የሚሸፈኑና አመልካች የሥራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ የሚያስችል ሆኖ እያለ የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተጠሪ ጥፋቶች የሥራ ውሉን ለማቋረጥ የሚያስችሉ አይደለም በማለት በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 1(ረ) እና (ሸ) ድንጋጌዎች በተመሣሣይ መንገድ በመተርጎም የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ተሽሯል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ፀንቷል።
አመልካች ተጠሪን ከሥራ ያሰናበተው በህግ አግባብ ነው በማለት ወስነናል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሣቸው ይቻሉ።
No topics extracted.