No summary available.
ታህሳስ 05 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሤ መኮንን ገ/ሕይወት ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- በደል ቢራ አክሲዮን ማህበር ነገረ ፈጅ አቶ ታዬ ይገዙ - ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ አልማው ቤዛ - ቀረበ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ በፍርድ ባለመብት በሆነው በአሁኑ ተጠሪና በፍርድ ባለ እዳ በሆነው በአሁኑ አመልካች መካከል በነበረው የአፈጻጸም ክስ ክርክር የፍ/የመ/ደ/ፍርድ ቤት የግራ ቀኙ ተከራካሪዎች በመ/ቁ/37192 ያቀረቡትን ክርክር በ29/06/2004 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በመመርመር የሰጠውን ትዕዛዝ የፍ/ከ/ፍርድ ቤት በማጽናቱ ነው።
የአፈጻጸም ትዕዛዙም የፍርድ ባለመብቱ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ቀደም ሲል የተወሰነ ከመሆኑም በላይ በመ/ቁ. 37299 የፍርድ ባለመብቱ በበደል በዕቅድና ምርታማነት አሰራር ማሻሻያ ቡድን አስተባባሪነት መመደቡ አግባብነት ያለው መሆኑን ፍርድ ቤቱ የወሰነ ስለሆነና ውሳኔውም በይግባኝ እስካልተለወጠ ድረስ የስራ መደቡን፣ ደመወዝ፣ የሥራ ቦታ እና የስራ መጀመሪያ ቀን በመጥቀስ የስራ ምደባ ደብዳቤ የፍርድ ባለዕዳው ላሰጥ ይገባል የሚል ይዘት ያለው ነው።
አመልካች በሥር ፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ ላይ ቅር በመሰኘት ለዚህ ችሎት ባቀረበው የሰበር አቤቱታ የፍ/የመ/ደ/ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 36405 በቀን 17/08/2003 ዓ.ም. ተጠሪው የ6 ወር ደመወዝ ተከፍሎአቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ የወሰነውን የፍ/ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም በ
ጥር 02/2004 ዓ.ም. በሰጠው ፍርድ ያጸናው ሲሆን ከዚሁ ውሳኔ ውጪ እንዲሁም ተጠሪው በመሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ በሁለት የሥራ መደቦች ተወዳድረው የተቀመጡትን መስፈርቶች ማለፍ አለመቻላቸው ተረጋግጦ እያለ በእቅድ ምርታማነትና አሰራር ማሻሻያ ቡድን አስተባባሪነት መደብ እንዲሰጣቸው የታዘዘው ህግን የሚጻረር ነው የሚል ነው።
ተጠሪው በበኩላቸው በሰጡት መልስ፡- አመልካች በፍርዱ መሰረት ምደባ ማድረጉን ገልጾ የሚከራከር ቢሆንም ምደባውን ያደረገው ከደረጃና ከደመወዜ ዝቅ በማድረግ ነው። ምደባው በመሰረታዊ ሥራ ሂደት ለውጥ የተሰጠ ነው በማለት ያቀረበው ክርክርም ቢሆን መጀመሪያውኑ ከሥራና ደመወዝ እንድገለል ወስኖ የነበረው አስቀድሞ አመልካች ያስጠናው የሰው ሀይል ምደባ እና ደመወዝ እስኬል በመዋቅር ተጠንቶ ሥራ ላይ ከዋለ ከ5 ወር በኋላ ነው። በመሆኑም በመሰረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ የተደረገ ምደባ ነው በማለት ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት የለውም ሲሉ ተከራክረዋል። አመልካችም በመልስ መልሱ ክርክሩን በማጠናከር አቅርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- አመልካች ቀደም ሲል የፍ/መ/ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/36405 በሰጠው ፍርድ እና ይህንኑ ፍርድ ይህ ችሎት በ
ባጸናው መሰረት ፈጽሟል? ወይስ አልፈጸመም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
የመ/ደ/ፍርድ ቤት ከዚህ በላይ በተጠቀሰው መዝገብ በሰጠው ፍርድ ላይ በአሁኑ የሰበር አመልካች አቤቱታ አቅራቢነት ይህ ችሎት የግራ ቀኙን ወገን በማከራከር በመ/ቁ. 69498 ጥር 02 ቀን 2004 ዓ.ም. የተሰጠው ፍርድ በማጽናት የስራ ውሉ የተቋረጠው በአመልካች ህገ ወጥ ድርጊት ነው በማለት የ6 ወራት ደመወዝ ተከፍሎአቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ መወሰኑን መዝገቡ ያመለክታል። ለዋናው ክስ መነሻ የነበረውም ተጠሪው ከሚሰሩበት ከአዲስ አበባ የሽያጭ ማስተባበሪያ ቢሮ በገበያ ጥናትና ማስታወቂያ ክፍል ሀላፊነት እንዲነሱ ተደርጎ በደል ሄደው በ29/02/2003 ዓ.ም. ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዘው በተባለው ጊዜ ሪፖርት ሳያደርጉ ዘግይተዋል በሚል በአመልካች በመሰናበታቸው ሲሆን ይህ በ23/02/2003 ዓ.ም.
የተጻፈው ደብዳቤ ይዘትም ደረጃቸውና ደመወዛቸው ሳይቀነስ በደል በሚገኘው የአመልካች ዋና መ/ቤት በእቅድና አሰራር ማሻሻያ ቡድን አስተባባሪነት መመደባቸውን የሚያሳይ መሆኑን ከመዝገቡ መረዳት የተቻለ ሲሆን ይህ ችሎትም ተጠሪውን አመልካች ያሰናበታቸው በህገ ወጥ መንገድ ነው በማለት የመ/ደ/ፍርድ ቤት የሰጠው ፍርድ የህግ ስህተት የለበትም በሚል ካጸናው በኋላ አመልካች እንደ ፍርዱ መፈጸሙን ለመግለጽ ሁለት ደብዳቤዎችን ለተጠሪው ስለመጻፉ ተረጋግጧል። ደብዳቤዎቹ የተጻፉት ጥር 12 ቀን 2004 ዓ.ም. እና መጋቢት 18 ቀን 2004 ዓ.ም. ሲሆን ጥር 12/2004 ዓ.ም. ከተጻፈው በሥር ፍርድ ቤት የተረጋገጠው ፍሬ ነገር ተጠሪው በሚመደቡበት የሥራ መደብ ሥራ እንዲጀምሩና የ6 ወራት የተጣራ ደመወዝም እንዲከፈላቸው የሚል መሆኑን ነው። መጋቢት 18 ቀን 2004 ዓ/ም ከተጻፈው ደብዳቤ የተረጋገጠው ደግሞ ቀደም ሲል ያገኙት በነበረው ያልተጣራ ደመወዝ ብር 3745 ላይ ብር 35 ተጨምሮ የደመወዝ ማስተካከያ ተደርጎላቸው ያልተጣራ ደመወዝ ብር 3780 እያገኙ በንብረት ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ የሥራ መደብ እንዲሰሩ ተመድበዋል የሚል መሆኑን ነው። ከእነዚህ አመልካች ከዋናው ፍርድ በኋላ እንደፍርዱ መፈጸሙን ለመግለጽ ከጻፋቸው ደብዳቤዎች የተረጋገጡ ፍሬ ነገሮች ደግሞ ከዋናው ፍርድ በፊት አመልካች ወደ በደል ተመድበው ሲላኩ እንዲሰሩ ከተደረገው የሥራ መደብ የሚለያዩ መሆናቸውን ነው። የፍርድ ባለ እዳው ፍርዱን ለመፈጸም የማያስችለው በቂ ምክንያት አለመኖሩን ፍርዱን የሚያስፈጽመው ፍርድ ቤት ያረጋገጠ እንደሆነ ፍርዱ እንዲፈጸም ማዘዝ የሚችል ስለመሆኑ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ 386(3) እና 392(1) ከተደነገገው መገንዘብ የሚቻል ነው። በመሆኑም አመልካች ያለ በቂ ምክንያት እንደፍርዱ አለመፈጸሙን ከጻፋቸው ደብዳቤዎችና በአፈጻጸም ወቅት ካቀረባቸው የቃል ክርክሮች የሥር ፍርድ ቤቶች በማረጋገጥ ተጠሪው ቀደም ሲል ከአዲስ አበባ ወደ በደል ሲላኩ በተሰጣቸው የስራ መደብና ደረጃ አመልካች እንዲመድባቸው በሰጡት ትእዛዝ ላይ የተፈጸመ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ባለማግኘታችን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍ/የመ/ደ/ፍርድ ቤት በመ/ቁ/37192 በቀን 29/06/2004 ዓ.ም. የሰጠውን ትዕዛዝና የፍ/ከ/ፍርድ ቤት በ/ቁ/116259 በቀን 01/08/2004 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት አጽንተናል።
አመልካች ተጠሪውን ቀድሞ በተመደቡበት በበደል ዋና መ/ቤት በዕቅድና ምርታማነት አሰራር ማሻሻያ የቡድን አስተባባሪነት የሥራ መደብ እንዲመልሳቸው ሲሉ የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ትእዛዝ ተገቢ ነው ብለናል።
ከዚህ በፊት በፍ/የመ/ደ/ፍርድ ቤት በአፈጻጻም መ/ቁ.37192 ተጀምሮ የነበረው የአፈጻጸም ክስ ታግዶ እንዲቆይ ተሰጥቶ የነበረው ትእዛዝ ተነስቷል። ይጻፍ።
የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ።
No topics extracted.